ምዕራፍ 1
1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን በሲና ምድረ በዳ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፥ በሁለተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን፥ ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በሁለተኛው ዓመት እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2፤ የእስራኤልን ልጆች ማኅበር ሁሉ ድምር፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ በየስማቸው ቍጥር፥ ወንዱን በየራሱ፥ ውሰዱ።
3፤ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን፥ ከእስራኤል ወደ ሰልፍ የሚወጡትን ሁሉ፥ አንተና አሮን በየሠራዊቶቻቸው ቍጠሩአቸው።
4፤ ከየነገዱም አንድ ሰው የአባቶቹ ቤት አለቃ ከእናንተ ጋር ይሁን።
5፤ ከእናንተም ጋር የሚቆሙት ሰዎች ስሞቻቸው እነዚህ ናቸው፤ ከሮቤል የሰዲዮር ልጅ
6፤ ኤሊሱር፥ ከስምዖን የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል፥
7፤ ከይሁዳ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን፥
8፤ ከይሳኮር የሶገር ልጅ ናትናኤል፥
9፤
10፤ ከዛብሎን የኬሎን ልጅ ኤልያብ፥ ከዮሴፍ ልጆች ከኤፍሬም የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ፥ ከምናሴ የፍዳሱ ልጅ ገማልኤል፥
11፤
12፤ ከብንያም የጋዴዮን ልጅ አቢዳን፥ ከዳን የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር፥
13፤ ከአሴር የኤክራን ልጅ ፋግኤል፥
14፤ ከጋድ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ፥
15፤ ከንፍታሌም የዔናን ልጅ አኪሬ።
16፤ ከማኅበሩ የተመረጡ የእስራኤል አእላፍ ታላላቆች፥ የአባቶቻቸው ነገድ አለቆች እነዚህ ናቸው።
17፤ ሙሴና አሮንም እነዚህን በስማቸው የተጠሩትን ሰዎች ወሰዱአቸው፤
18፤ በሁለተኛውም ወር በመጀመሪያው ቀን ማኅበሩን ሁሉ ሰበሰቡአቸው፤ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን በየራሱ በየወገኑም በየአባቶቻቸውም ቤቶች በየስማቸው ቍጥር ትውልዳቸውን ተናገሩ።
19፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ እንዲሁ በሲና ምድረ በዳ ቈጠራቸው።
20፤ የእስራኤል በኵር የሮቤል ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
21፤ ከሮቤል ነገድ የተቈጠሩ አርባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
22፤ የስምዖን ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች የተቈጠሩ፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
23፤ ከስምዖን ነገድ የተቈጠሩት አምሳ ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ ነበሩ።
24፤ የጋድ ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
25፤ ከጋድ ነገድ የተቈጠሩት አርባ አምስት ሺህ ስድስት መቶ አምሳ ነበሩ።
26፤ የይሁዳ ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
27፤ ከይሁዳ ነገድ የተቈጠሩት ሰባ አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ።
28፤ የይሳኮር ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
29፤ ከይሳኮር ነገድ የተቈጠሩት አምሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
30፤ የዛብሎን ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
31፤ ከዛብሎን ነገድ የተቈጠሩት አምሳ ሰባት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
32፤ ከዮሴፍ ልጆች፥ የኤፍሬም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
33፤ ከኤፍሬም ነገድ የተቈጠሩት አርባ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
34፤ የምናሴ ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
35፤ ከምናሴ ነገድ የተቈጠሩት ሠላሳ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ።
36፤ የብንያም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
37፤ ከብንያም ነገድ የተቈጠሩት ሠላሳ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
38፤ የዳን ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
39፤ ከዳን ነገድ የተቈጠሩት ስድሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ።
40፤ የአሴር ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
41፤ ከአሴር ነገድ የተቈጠሩት አርባ አንድ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
42፤ የንፍታሌም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
43፤ ከንፍታሌም ነገድ የተቈጠሩት አምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
44፤ የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን አሥራ ሁለቱም የእስራኤል አለቆች የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው፤ እያንዳንዱ የአባቶቹ ቤት አለቃ ነበረ።
45፤ ከእስራኤልም ልጆች የተቈጠሩት ሁሉ፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥
46፤ የተቈጠሩት ሁሉ ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ አምሳ ነበሩ።
47፤ ሌዋውያን ግን በየአባቶቻቸው ነገድ ከእነርሱ ጋር አልተቈጠሩም።
48፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። የሌዊን ነገድ አትቍጠረው፥
49፤ ቍጥራቸውንም ከእስራኤል ልጆች ጋር አታድርግ፤
50፤ ነገር ግን በምስክሩ ማደሪያና በዕቃዎች ሁሉ ለእርሱም በሚሆነው ነገር ሁሉ ላይ ሌዋውያንን አቁማቸው። ማደሪያውንና ዕቃዎችን ሁሉ ይሸከሙ፥ ያገልግሉትም፥ በማደሪያውም ዙሪያ ይስፈሩ።
51፤ ማደሪያውም ሲነሣ ሌዋውያን ይንቀሉት፤ ማደሪያውም በሰፈረ ጊዜ ሌዋውያን ይትከሉት፤ ሌላ ሰው ግን ቢቀርብ ይገደል።
52፤ የእስራኤልም ልጆች እያንዳንዱ በየሰፈሩ፥ በየዓላማውም፥ በየጭፍራውም ይሰፍራሉ።
53፤ ነገር ግን በእስራኤል ልጆች ላይ ቍጣ እንዳይወርድ ሌዋውያን በምስክሩ ማደሪያ ዙሪያ ይስፈሩ፤ ሌዋውያንም የምስክሩን ማደሪያ ይጠብቁ።
54፤ የእስራኤል ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረጉ።
ምዕራፍ 2
1፤ እግዚአብሔርም ለሙሴና ለአሮን እንዲህ ብሎ ተናገረ።
2፤ የእስራኤል ልጆች እያንዳንዱ በየዓላማው በየአባቶቻቸው ቤቶች ምልክት ይስፈሩ፤ በመገናኛው ድንኳን አፋዛዥ ዙሪያ ይስፈሩ።
3፤ በምሥራቅ በኩል ወደ ፀሐይ መውጫ የሚሰፍሩት እንደ ሠራዊቶቻቸው የይሁዳ ሰፈር ዓላማ ሰዎች ይሆናሉ፤ የይሁዳ ልጆችም አለቃ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነበረ።
4፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ሰባ አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ።
5፤ በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩ የይሳኮር ነገድ ይሆናሉ፤ የይሳኮርም ልጆች አለቃ የሶገር ልጅ ናትናኤል ነበረ።
6፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አምሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
7፤ በእነርሱም አጠገብ የዛብሎን ነገድ ነበረ፤ የዛብሎንም ልጆች አለቃ የኬሎን ልጅ ኤልያብ ነበረ።
8፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አምሳ ሰባት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
9፤ ከይሁዳ ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ በየሠራዊቶቻቸው መቶ ሰማንያ ስድስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። እነዚህም አስቀድመው ይጓዛሉ።
10፤ በደቡብ በኩል በየሠራዊቶቻቸው የሮቤል ሰፈር ዓላማ ይሆናል፤ የሮቤልም ልጆች አለቃ የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር ነበረ።
11፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
12፤ በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩ የስምዖን ነገድ ናቸው፤ የስምዖንም ልጆች አለቃ የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል ነበረ።
13፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አምሳ ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ ነበሩ።
14፤ በእነርሱም አጠገብ የጋድ ነገድ ነበረ፤ የጋድም ልጆች አለቃ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ ነበረ።
15፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ አምስት ሺህ ስድስት መቶ አምሳ ነበሩ።
16፤ ከሮቤል ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ በየሠራዊቶቻቸው መቶ አምሳ አንድ ሺህ አራት መቶ አምሳ ነበሩ። እነርሱም ቀጥለው ይጓዛሉ።
17፤ ከዚያም በኋላ የመገናኛው ድንኳን በሰፈሮቹም መካከል የሌዋውያን ሰፈር ይጓዛል፤ እንደ ሰፈራቸው ሰው ሁሉ በየስፍራው በየዓላማውም ይጓዛሉ።
18፤ በምዕራብ በኩል እንደ ሠራዊቶቻቸው የኤፍሬም ሰፈር ዓላማ ይሆናል፤ የኤፍሬም ልጆች አለቃ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ ነበረ።
19፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
20፤ በእነርሱም አጠገብ የምናሴ ነገድ ይሆናል፤ የምናሴም ልጆች አለቃ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል ነበረ።
21፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ሠላሳ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ።
22፤ በእነርሱም አጠገብ የብንያም ነገድ ይሆናል፤ ይብንያምም ልጆች አለቃ የጋዴዮን ልጅ አቢዳን ነበረ።
23፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ሠላሳ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
24፤ ከኤፍሬም ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ በየሠራዊቶቻቸው መቶ ስምንት ሺህ አንድ መቶ ነበሩ። እነርሱም ሦስተኛ ሆነው ይጓዛሉ።
25፤ በሰሜን በኩል እንደ ሠራዊቶቻቸው የዳን ሰፈር ዓላማ ይሆናል፤ የዳንም ልጆች አለቃ የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር ነበረ።
26፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ስድሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ።
27፤ በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩ የአሴር ነገድ ይሆናሉ፤ የአሴርም ልጆች አለቃ የኤክራን ልጅ ፋግኤል ነበረ።
28፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ አንድ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
29፤ በእነርሱም አጠገብ የንፍታሌም ነገድ ይሆናል፤ የንፍታሌምም ልጆች አለቃ የዔናን ልጅ አኪሬ ነበረ።
30፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
31፤ ከዳን ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ መቶ አምሳ ሰባት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። እነርሱም በየዓላሞቻቸው በመጨረሻ ይጓዛሉ።
32፤ ከእስራኤል ልጆች በየአባቶቻቸው ቤቶች የተቈጠሩ እነዚህ ናቸው፤ ከየሰፈሩ በየሠራዊቶቻቸው የተቈጠሩ ሁሉ ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ አምሳ ነበሩ።
33፤ ሌዋውያን ግን እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ ከእስራኤል ልጆች ጋር አልተቈጠሩም።
34፤ የእስራኤል ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ በዓላሞቻቸው አጠገብ ሰፈሩ፥ እንዲሁም በየወገኖቻቸው በየአባቶቻቸው ቤቶች ተጓዙ።
ምዕራፍ 3
1፤ እግዚአብሔርም በሲና ተራራ ላይ ሙሴን በተናገረበት ቀን የአሮንና የሙሴ ትውልድ ይህ ነበረ።
2፤ የአሮን ልጆች ስም ይህ ነው፤ በኵሩ ናዳብ፥ አብዩድ፥ አልዓዛር፥ ኢታምር።
3፤ የተቀቡ ካህናት በክህነትም ያገለግሉ ዘንድ የቀደሳቸው የአሮን ልጆች ስም ይህ ነው።
4፤ ናዳብና አብዩድ በሲና ምድረ በዳ በእግዚአብሔር ፊት ልዩ እሳት ባቀረቡ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ሞቱ፤ ልጆችም አልነበሩአቸውም። አልዓዛርና ኢታምር በአባታቸው በአሮን ፊት በክህነት ያገለግሉ ነበር።
5፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
6፤ የሌዊን ነገድ አቅርበህ ያገለግሉት ዘንድ በካህኑ በአሮን ፊት አቁማቸው።
7፤ የማደሪያውንም ሥራ ይሠሩ ዘንድ፥ እርሱንና ማኅበሩን ሁሉ ለማገልገል የሚያስፈልገውን ነገር በመገናኛው ድንኳን ፊት ይጠብቁ።
8፤ የማደሪያውንም ሥራ ይሠሩ ዘንድ፥ የመገናኛውን ድንኳን ዕቃ ሁሉ ይጠብቁ፥ የእስራኤልን ልጆች ለማገልገል የሚያስፈልገውንም ነገር ይጠብቁ።
9፤ ሌዋውያንንም ለአሮንና ለልጆቹ ትሰጣለህ፤ ከእስራኤል ልጆች ለእርሱ ፈጽመው ተሰጡ።
10፤ አሮንንና ልጆቹን አቁማቸው፥ ክህነታቸውንም ይጠብቁ፤ ሌላ ሰውም ቢቀርብ ይገደል።
11፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
12፤ እነሆ፥ እኔ በእስራኤል ልጆች ዘንድ ማኅፀን በሚከፍተው በበኵሩ ሁሉ ፋንታ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ወስጄአለሁ፤
13፤ በኵር ሁሉ ለእኔ ነውና ሌዋውያን ለእኔ ይሁኑ፤ በግብፅ ምድር በኵርን ሁሉ በመታሁ ቀን፥ ከእስራኤል ዘንድ በኵርን ሁሉ፥ ሰውንና እንስሳን፥ ለእኔ ለይቼአለሁ፤ ለእኔ ይሁኑ። እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
14፤ እግዚአብሔርም ሙሴን በሲና ምድረ በዳ እንዲህ ብሎ ተናገረው።
15፤ የሌዊን ልጆች በየአባቶቻቸው ቤቶች በየወገናቸውም ቍጠር፤ ወንዱን ሁሉ ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን ቍጠራቸው።
16፤ ሙሴም እንደ እግዚአብሔር ቃል እንዳዘዘው ቈጠራቸው።
17፤ የሌዊ ልጆች በየስማቸው እነዚህ ናቸው፤ ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ።
18፤ የጌድሶንም ልጆች ስሞች በየወገናቸው እነዚህ ናቸው፤ ሎቤኒ፥ ሰሜኢ።
19፤ የቀዓትም ልጆች በየወገናቸው እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል።
20፤ የሜራሪም ልጆች በየወገናቸው፤ ሞሖሊ፥ ሙሲ። የሌዋውያን ወገኖች በየአባቶቻቸው ቤቶች እነዚህ ናቸው።
21፤ ለጌድሶን የሎቤናውያን ወገን የሰሜአውያንም ወገን ነበሩት፤ የጌድሶናውያን ወገኖች እነዚህ ናቸው።
22፤ ከእነርሱ የተቈጠሩት የወንዶች ሁሉ ቍጥር ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ የተቈጠሩት ሰባት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
23፤ የጌድሶናውያን ወገኖች ከማደሪያው በኋላ በምዕራብ ብኩል ይሰፍራሉ።
24፤ የጌድሶናውያንም አባቶች ቤት አለቃ የዳኤል ልጅ ኤሊሳፍ ይሆናል።
25፤ ጌድሶናውያንም በመገናኛው ድንኳን የሚጠብቁት ማደሪያው፥ ድንኳኑም፥ መደረቢያውም፥ የመገናኛው ድንኳን ደጃፍ መጋረጃ፥
26፤ በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ ያለው የአደባባዩ መጋረጆች፥ የአደባባዩም ደጃፍ መጋረጃ፥ ለማገልገሉም ያሉት ገመዶች ሁሉ ይሆናል።
27፤ ከቀዓትም የእንበረማውያን ወገን፥ የይስዓራውያንም ወገን፥ የኬብሮናውያንም ወገን፥ የዑዝኤላውያንም ወገን ነበሩ፤ የቀዓታውያን ወገኖች እነዚህ ናቸው።
28፤ ወንዶች ሁሉ እንደ ቍጥራቸው ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ፤ መቅደሱንም ይጠብቁ ነበር።
29፤ የቀዓት ልጆች ወገኖች በማደሪያው አጠገብ በደቡብ በኩል ይሰፍራሉ።
30፤ የቀዓታውያንም ወገኖች አባቶች ቤት አለቃ የዑዝኤል ልጅ ኤሊሳፈን ይሆናል።
31፤ ታቦቱንም፥ ገበታውንም፥ መቅረዙንም፥ መሠዊያዎቹንም፥ የሚያገለግሉበትንም የመቅደሱን ዕቃ፥ መጋረጃውንም፥ ማገልገያውንም ሁሉ ይጠብቃሉ።
32፤ የሌዋውያንም አለቆች አለቃ የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር ይሆናል፤ እርሱም መቅደሱን በሚጠብቁት ላይ ይሆናል።
33፤ ከሜራሪ የሞሖላውያን ወገን የሙሳያውያንም ወገን ነበሩ፤ የሜራሪ ወገኖች እነዚህ ናቸው።
34፤ ከእነርሱም ወንዶች ሁሉ እንደ ቍጥራቸው ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ የተቈጠሩት ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ።
35፤ የሜራሪም ወገኖች አባቶች ቤት አለቃ የአቢካኢል ልጅ ሱሪኤል ነበረ፤ በማደሪያው አጠገብ በሰሜን በኩል ይሰፍራሉ።
36፤ የሜራሪም ልጆች የሚጠብቁት የማደሪያው ሳንቆች፥ መወርወሪያዎችም፥ ተራዳዎችም፥ እግሮቹም፥ ዕቃውም ሁሉ፥
37፤ ማገልገያውም ሁሉ፥ በዙሪያውም የሚቆሙ የአደባባይ ምሰሶች፥ እግሮቹም፥ ካስማዎቹም፥ አውታሮቹም ይሆናሉ።
38፤ በማደሪያውም ፊት በምሥራቅ በኩል በመገናኛው ድንኳን ፊት በስተ ፀሐይ መውጫ የሚሰፍሩት ሙሴና አሮን ልጆቹም ይሆናሉ፥ መቅደሱንም ለእስራኤል ልጆች ይጠብቃሉ፤ ልዩም ሰው ቢቀርብ ይገደል።
39፤ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ ከሌዋውያን ወንዶች ሁሉ ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ በየወገናቸው የተቈጠሩት ሁሉ ሀያ ሁለት ሺህ ነበሩ።
40፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። የእስራኤልን ልጆች ወንዱን በኵር ሁሉ ቍጠር፤ ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉትን የስማቸውን ቍጥር ውሰድ፤
41፤ ሌዋውያንንም በእስራኤል ልጆች በኵር ሁሉ ፋንታ፥ የሌዋውያንንም እንስሶች በእስራኤል ልጆች እንስሶች በኵር ሁሉ ፋንታ ለእኔ ለእግዚአብሔር ውሰድ አለው።
42፤ ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው የእስራኤልን ልጆች በኵር ሁሉ ቈጠረ።
43፤ ከእነርሱም የተቈጠሩ ወንዶች በኵሮች ሁሉ የበስማቸው ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ሀያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ነበሩ።
44፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
45፤ ሌዋውያንን በእስራኤል ልጆች በኵር ሁሉ ፋንታ፥ የሌዋውያንንም እንስሶች በእንስሶቻቸው ፋንታ ውሰድ፤ ሌዋውያንም ለእኔ ይሁኑ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
46፤ በሌዋውያን ላይ ከእስራኤል ልጆች በኵር ስለ ተረፉት ስለ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ቤዛ፥ በየራሱ አምስት ሰቅል ውሰድ፤
47፤ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ትወስዳለህ፤ ሰቅሉም ሀያ አቦሊ ነው።
48፤ ስለ ተረፉትም የመቤዣውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ።
49፤ ሙሴም በሌዋውያን ከተቤዡት በላይ ከተረፉት ዘንድ የመቤዣውን ገንዘብ ወሰደ።
50፤ ከእስራኤል ልጆች በኵሮች ገንዘቡን ሺህ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ወሰደ።
51፤ እንደ እግዚአብሔርም ቃል፥ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው፥ ሙሴ የመቤዣውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጠ።
ምዕራፍ 4
1፤ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
2፤ ከሌዊ ልጆች መካከል በየወገናቸው በየአባቶቻቸው ቤቶች የቀዓትን ልጆች ድምር ውሰድ፤
3፤ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ በመገናኛው ድንኳን ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የሚገቡበትን ሁሉ ትደምራለህ።
4፤ በመገናኛው ድንኳን በንዋየ ቅድሳቱ ዘንድ የቀዓት ልጆች ሥራ ይህ ነው፤
5፤ ከሰፈሩ በተነሡ ጊዜ አሮንና ልጆቹ ገብተው የሚሸፍነውን መጋረጃ ያውርዱ፥ የምስክሩንም ታቦት ይጠቅልሉበት፤
6፤ በላዩም የአቆስጣውን ቁርበት መሸፈኛ ያድርጉበት፥ ከእርሱም በላይ ሁለንተናው ሰማያዊ የሆነ መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ።
7፤ በገጽ ኅብስት ገበታ ላይ ሰማያዊውን መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፤ በእርሱም ላይ ወጭቶቹን፥ ጭልፋዎቹንም፥ ጽዋዎቹንም፥ ለማፍሰስም መቅጃዎቹን ያድርጉ፤ ሁልጊዜም የሚኖር እንጀራ በእርሱ ላይ ይሁን።
8፤ በእነርሱም ላይ ቀይ መጐናጸፊያ ይዘርጉ፥ በአቆስጣውም ቁርበት መሸፈኛ ይሸፍኑት፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ።
9፤ ሰማያዊውንም መጐናጸፊያ ይውሰዱ፥ የሚያበራውንም መቅረዝ፥ ቀንዲሎቹንም፥ መኰስተሪያዎቹንም፥ የኩስታሪ ማድረጊያዎቹንም፥ እርሱንም ለማገልገል የዘይቱን ዕቃዎች ሁሉ ይሸፍኑ፤
10፤ እርሱንና ዕቃዎቹን ሁሉ በአቆስጣ ቁርበት መሸፈኛ ውስጥ ያድርጉ፥ በመሸከሚያውም ላይ ያድርጉት።
11፤ በወርቁም መሠዊያ ላይ ሰማያዊውን መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፥ በአቆስጣም ቁርበት መሸፈኛ ይሸፍኑት፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ።
12፤ በመቅደስም ውስጥ የሚያገልግሉበትን የማገልገያውን ዕቃ ሁሉ ይውሰዱ፥ በሰማያዊውም መጐናጸፊያ ውስጥ ያስቀምጡት፥ በአቆስጣም ቁርበት መሸፈኛ ይሸፍኑት፥ በመሸከሚያውም ላይ ያድርጉት።
13፤ አመዱንም ከመሠዊያው ላይ ያስወግዱ፥ ሐምራዊውንም መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፤
14፤ የሚያገለግሉበትን ዕቃውን ሁሉም ማንደጃዎቹን ሜንጦቹንም መጫሪያዎቹንም ድስቶቹንም፥ የመሠዊያውን ዕቃ ሁሉ ያስቀምጡበት፤ በእርሱም የአቆስጣን ቁርበት መሸፈኛ ይዘርጉ፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ።
15፤ ከሰፈሩም ሲነሡ፥ አሮንና ልጆቹ መቅደሱንና የመቅደሱን ዕቃ ሁሉ ከሸፈኑ በኋላ፥ በዚያን ጊዜ የቀዓት ልጆች ሊሸከሙት ይመጣሉ፤ እንዳይሞቱ ግን ንዋየ ቅድሳቱን አይንኩ። በመገናኛው ድንኳን ዘንድ የቀዓት ልጆች ሸክም ይህ ነው።
16፤ የካህኑም የአሮን ልጅ አልዓዛር በመብራቱ ዘይት በጣፋጩም ዕጣን ላይ፥ ሁልጊዜም በሚቀርበው በእህሉ ቍርባንና በቅባቱ ዘይት ላይ ይሾም፤ ማደሪያውን ሁሉ፥ በእርሱም ውስጥ ያለውን ሁሉ፥ መቅደሱንና ዕቃውን ይጠብቃል።
17፤ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
18፤ የቀዓትን ወገኖች ነገድ ከሌዋውያን መካከል አታጥፉአቸው፤
19፤ ነገር ግን ወደ ቅድስተ ቅዱሳን በቀረቡ ጊዜ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ እንጂ እንዳይሞቱ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ አሮንና ልጆቹ ይግቡ፥ ለሰውም ሁሉ ሥራውንና ሸክሙን ይዘዙ፤
20፤ ነገር ግን እንዳይሞቱ ንዋየ ቅድሳቱን ለድንገት እንኳ ለማየት አይግቡ።
21፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
22፤ የጌድሶንን ልጆች ድምር ደግሞ በየአባቶቻቸው ቤቶች በየወገኖቻቸውም ውሰድ።
23፤ የመገናኛውን ድንኳን ሥራ ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የሚገቡትን ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ቍጠራቸው።
24፤ የጌድሶናውያን ወገኖች ሥራ በማገልገልና በመሸከም ይህ ነው፤
25፤ የማደሪያውን መጋረጆች፥ የመገናኛውንም ድንኳን፥ መደረቢያውን፥ በላዩም ያለውን የአቆስጣውን ቁርበት መደረቢያ፥ የመገናኛውንም ድንኳን ደጃፍ መጋረጃ፥
26፤ በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ ያለውን የአደባባዩን መጋረጃ፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ፥ አውታሮቻቸውንም፥ ለማገልገልም የሚሠሩበትን ዕቃ ሁሉ ይሸከሙ፤ በዚህ ያገልግሉ።
27፤ የጌድሶናውያን አገልግሎት ሁሉ፥ ሸክማቸውም ሁሉ፥ ሥራቸውም ሁሉ በአሮንና በልጆቹ ትእዛዝ ይሁን፤ የሚደርስባቸውንም ሸክም ሁሉ ትነግሩአቸዋላችሁ።
28፤ የጌድሶናውያን ወገኖች አገልግሎት በመገናኛው ድንኳን ዘንድ ይህ ነው፤ ከካህኑ ከአሮን ልጅ ከኢታምር እጅ በታች ይሆናሉ።
29፤ የሜራሪንም ልጆች በየወገናቸው በየአባቶቻቸውም ቤቶች ቍጠራቸው።
30፤ የመገናኛውን ድንኳን ሥራ ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የሚገቡትን ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ቍጠራቸው።
31፤ በመገናኛው ድንኳን ዘንድ ባለው አገልግሎታቸው ሁሉ፥ የማደሪያው ሳንቆች፥ መወርወሪያዎቹም፥ ተራዳዎቹም፥ እግሮቹም፥
32፤ በዙሪያውም የሚቆሙት የአደባባዩ ምሰሶች፥ እግሮቹም፥ ካስማዎቹም፥ አውታሮቹም፥ ዕቃዎቹና ማገልገያዎቹ ሸክማቸው ነው፤ የሚጠብቁትንም የሸክማቸውን ዕቃ ሁሉ በስማቸው ቍጠሩ።
33፤ የሜራሪ ልጆች ወገኖች አገልግሎት በመገናኛው ድንኳን ዘንድ ከካህኑ ክአሮን ልጅ ከኢታምር እጅ በታች በየአገልግሎታቸው ሁሉ ይህ ነው።
34፤ ሙሴና አሮንም የሕቡም አለቆች የቀዓትን ልጆች በየወገናቸው በየአባቶቻቸውም ቤቶች ቈጠሩአቸው።
35፤ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ወደ አገግሎት የገቡትን ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ያሉትን ቈጠሩአቸው፤
36፤ በየወገናቸውም ከእነርሱ የተቈጠሩት ሁለት ሺህ ሰባት መቶ አምሳ ነበሩ።
37፤ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለገሉት ሁሉ፥ ከቀዓታውያን ወገኖች የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው።
38፤ በየወገናቸውም በየአባቶቻቸውም ቤቶች የተቈጠሩት የጌድሶን ልጆች፥
39፤ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የገቡት፥ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ያሉት፥
40፤ በየወገናቸውም በየአባቶቻቸውም ቤቶች የተቈጠሩት ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሠላሳ ነበሩ።
41፤ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለገሉት ሁሉ፥ ከጌድሶን ልጆች ወገኖች የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው።
42፤ በየወገናቸውም በየአባቶቻቸውም ቤቶች ከሜራሪ ልጆች ወገኖች የተቈጠሩት፥
43፤ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ወደ አገልግሎት የገቡት ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ያሉት፥
44፤ በየወገናቸው የተቈጠሩት ሦስት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ።
45፤ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ፥ ከሜራሪ ልጆች ወገኖች የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው።
46፤ በየወገናቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች ከሌዋውያን የተቈጠሩት ሁሉ፥ ሙሴና አሮን የእስራኤልም አለቆች የቈጠሩአቸው፥
47፤ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሥራውን ለመሥራትና ዕቃውን ለመሸከም የገቡት ሁሉ፥ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ያሉት፥
48፤ ከእነርሱ የተቈጠሩት ስምንት ሺህ እምስት መቶ ሰማንያ ነበሩ።
49፤ እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ እያንዳንዳቸው በየአገልግሎታቸውና በየሸክማቸው በሙሴ እጅ ተቈጠሩ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ እንዲሁ በእርሱ ተቈጠሩ።
ምዕራፍ 5
1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2፤ የእስራኤል ልጆች ለምጻሙን ሁሉ፥ ፈሳሽ ነገርም ያለበትን ሁሉ፥ በሬሳም የረከሰውን ሁሉ ከሰፈሩ እንዲያወጡ እዘዛቸው፤
3፤ ወንዱንና ሴቱን አውጡ፤ እኔ በመካከሉ የማድርበትን ሰፈራቸውን እንዳያረክሱ ከሰፈሩ አውጡአቸው።
4፤ የእስራኤልም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፥ ከሰፈሩ አወጡአቸው፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው፥ የእስራኤል ልጆች እንዲሁ አደረጉ።
5፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
6፤ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው። ወንድ ወይም ሴት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይተላለፍ ዘንድ ሰው የሚሠራውን ኃጢአት ቢሠራ፥ በዚያም ሰው ላይ በደል ቢሆን፥ በሠራው ኃጢአት ይናዘዝ፤
7፤ የወሰደውንም በሙሉ ይመልስ አምስተኛውንም ይጨምርበት፥ ለበደለውም ሰው ይስጠው።
8፤ ነገር ግን ይመልስለት ዘንድ ሰውዮው ዘመድ ባይኖረው፥ ስለ በደል ለእግዚአብሔር የሚመልሰው ነገር ለካህኑ ይሁን፥ ይህም ስለ እርሱ ማስተሰረያ ከሚደረግበት አውራ በግ በላይ ይጨመር።
9፤ የእስራኤልም ልጆች ለካህኑ የሚያቀርቡት የተቀደሰ የማንሣት ቍርባን ሁሉ ለእርሱ ይሁን።
10፤ የተቀደሰ የሰው ነገር ሁሉ፥ ሰውም ለካህኑ የሚሰጠው ሁሉ ለእርሱ ይሁን።
11፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
12፤ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው። የማንኛውም ሰው ሚስት ከእርሱ ፈቀቅ ብትል፥ በእርሱም ላይ ብትበድል፥
13፤ ከሌላም ሰው ጋር ብትተኛ፥ ከባልዋም ዓይን ቢሸሸግ፥ እርስዋም ተሰውራ ብትረክስ፥ ምስክርም ባይኖርባት፥ በምንዝርም ባትገኝ፥
14፤ በባልዋም ላይ የቅንዓት መንፈስ ቢመጣበት፥ እርስዋም ስትረክስ ስለ ሚስቱ ቢቀና፤ ወይም እርስዋ ሳትረክስ የቅንዓት መንፈስ ቢመጣበት፥ ስለ ሚስቱም ቢቀና፤
15፤ ያ ሰው ሚስቱን ወደ ካህኑ ያምጣት፥ የኢፍ መስፈሪያም አሥረኛ እጅ ገብስ ዱቄት ቍርባን ስለ እርስዋ ያምጣ፤ የቅንዓት ቍርባን ነውና፥ ኃጢአትንም የሚያሳስብ የመታሰቢያ ቍርባን ነውና ዘይት አያፍስስበት፥ ዕጣንም አይጨምርበት።
16፤ ካህኑም ያቀርባታል በእግዚአብሔርም ፊት ያቆማታል፤
17፤ ካህኑም የተቀደሰ ውኃ በሸክላ ዕቃ ይወስዳል፤ ካህኑም በማደሪያው ውስጥ ካለው ትቢያ ወስዶ በውኃ ላይ ይረጨዋል፤
18፤ ካህኑም ሴቲቱን በእግዚአብሔር ፊት ያቆማታል፥ የሴቲቱንም ራስ ይገልጣል፥ በእጅዋም ለመታሰቢያ የሚሆነውን የእህል ቍርባን፥ ለቅንዓት ቍርባን፥ ያኖራል፤ በካህኑም እጅ እርግማንን የሚያመጣው መራራ ውኃ ይሆናል።
19፤ ካህኑም ያምላታል፥ ሴቲቱንም እንዲህ ይላታል። ሌላ ወንድ አልተኛሽ፥ ባልሽንም አልተውሽ፥ ራስሽንም አላረከስሽ እንደ ሆነ፥ እርግማንን ከሚያመጣ ከዚህ መራራ ውኃ ንጹሕ ሁኚ፤
20፤ ነገር ግን ባልሽን ትተሽ ረክሰሽ እንደ ሆነ፥ ከባልሽም ሌላ ከወንድ ጋር ተኝተሽ እንደሆነ፤
21፤ ካህኑም ሴቲቱን በመርገም መሐላ ያምላታል፥ ካህኑም ሴቲቱን። እግዚአብሔር ጭንሽን እያሰለሰለ ሆድሽንም እየነፋ፥ እግዚአብሔር ለመርገምና ለመሐላ በሕዝብሽ መካከል ያድርግሽ፤
22፤ እርግማንንም የሚያመጣ ይህ ውኃ ወደ ሆድሽ ይግባ፥ ሆድሽንም ይንፋው፥ ጭንሽንም ያበስብሰው ይላታል፤ ሴቲቱም። አሜን አሜን ትላለች።
23፤ ካህኑም እነዚህን መርገሞች በሰሌዳ ይጽፈዋል፥ በመራራውም ውኃ ይደመስሰዋል፤
24፤ እርግማን የሚያመጣውንም መራራ ውኃ ለሴቲቱ ይጠጣታል፤ የእርግማኑም ውኃ በገባባት ጊዜ መራራ ይሆናል።
25፤ ካህኑም የቅንዓቱን የእህል ቍርባን ከሴቲቱ እጅ ይወስዳል፥ የእህሉንም ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዘዋል፥ ወደ መሠዊያውም ያመጣዋል፤
26፤ ካህኑም ከእህሉ ቍርባን አንድ እፍኝ ሙሉ ለመታሰቢያው ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፥ ከዚያም በኋላ ለሴቲቱ ውኃውን ያጠጣታል።
27፤ ውኃውን ካጠጣት በኋላ እንዲህ ይሆናል፤ ረክሳና በባልዋ ላይ አመንዝራ እንደ ሆነች፥ እርግማንን የሚያመጣው ውኃ ገብቶ መራራ ይሆንባታል፥ ሆድዋም ይነፋል፥ ጭንዋም ይሰለስላል፤ ሴቲቱም በሕዝብዋ መካከል ለመርገም ትሆናለች።
28፤ ያልረከሰች ያለ ነውርም እንደ ሆነች፥ ንጹሕ ትሆናለች፥ ልጆችንም ታረግዛለች።
29፤
30፤ ሴት ባልዋን ትታ በረከሰች ጊዜ፥ ወይም በሰው ላይ የቅንዓት መንፈስ በመጣበት ጊዜ፥ ስለ ሚስቱም በቀና ጊዜ፥ የቅንዓት ሕግ ይህ ነው፤ ሴቲቱንም በእግዚአብሔር ፊት ያቁማት፥ ካህኑም እንደዚህ ሕግ ሁሉ ያድርግባት።
31፤ ሰውዮውም ከኃጢአት ንጹሕ ይሆናል፥ ሴቲቱም ኃጢአትዋን ትሸከማለች።
ምዕራፍ 6
1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2፤ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው። ሰው ወይም ሴት ለእግዚአብሔር ራሱን የተለየ ያደርግ ዘንድ የናዝራዊነት ስእለት ቢሳል፥
3፤ ከወይን ጠጅና ከሚያሰክር መጠጥ ራሱን የተለየ ያድርግ፤ ከወይን ወይም ከሌላ ነገር የሚገኘውን ሆምጣጤ አይጠጣ፥ የወይንም ጭማቂ አይጠጣ፤ የወይን እሸት ወይም ዘቢብ አይብላ።
4፤ ራሱን የተለየ ባደረገበት ወራት ሁሉ ከወይን የሆነውን ነገር ሁሉ ከውስጡ ፍሬ ጀምሮ እስከ ገፈፎው ድረስ አይብላ።
5፤ ራሱን ለመለየት ስእለት ባደረገበት ወራት ሁሉ በራሱ ላይ ምላጭ አይደርስም፤ ለእግዚአብሔር የተለየበት ወራት እስኪፈጸም ድረስ የተቀደሰ ይሆናል፥ የራሱንም ጠጕር ያሳድጋል።
6፤ ለእግዚአብሔር ራሱን የተለየ ባደረገበት ወራት ሁሉ ወደ ሬሳ አይቅረብ።
7፤ ለአምላኩ ያደረገው እስለት በራሱ ላይ ነውና አባቱ ወይም እናቱ ወይም ወንድሙ ወይም እኅቱ ሲሞቱ ሰውነቱን አያርክስባቸው።
8፤ ራሱን የተለየ ባደረገበት ወራት ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነው።
9፤ ሰውም በአጠገቡ ድንገት ቢሞት የተለየውንም ራሱን ቢያረክስ፥ እርሱ በሚነጻበት ቀን ራሱን ይላጭ፤ በሰባተኛው ቀን ይላጨው።
10፤ በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደ ካህኑ ያምጣ፤
11፤ ካህኑም አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት ሁለተኛውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርበዋል፤ በሬሳም የተነሣ ኃጢአት ሠርቶአልና ያስተሰርይለታል፥ በዚያም ቀን ራሱን ይቀድሰዋል።
12፤ ራሱን የተለየ ያደረገበትን ወራትም ለእግዚአብሔር ይቀድሳል፥ የአንድ ዓመትም ተባት ጠቦት ለበደል መሥዋዕት ያምጣ፤ ናዝራዊነቱ ግን ረክሶአልና ያለፈው ወራት ሁሉ ከንቱ ይሆናል።
13፤ የመለየቱ ወራት በተፈጸመ ጊዜ የናዝራዊው ሕግ ይህ ነው፤ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይቅረብ፤
14፤ ቍርባኑንም ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ነውርም የሌለባትን የአንድ ዓመት እንስት ጠቦት ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ነውርም የሌለበትን አውራ በግ ለደኅንነት መሥዋዕት፥
15፤ አንድ ሌማትም ቂጣ እንጀራ፥ በዘይት የተለወሰ ከመልካም ዱቄትም የተሠሩ እንጐቻዎች፥ በዘይትም የተቀባ ስስ ቂጣ፥ የእህሉንም ቍርባን፥ የመጠጡንም ቍርባን ያቅርብ።
16፤ ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያቀርባቸዋል፥ የኃጢአቱንም መሥዋዕት የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ያሳርግለታል።
17፤ አውራውንም በግ ለደኅንነት መሥዋዕት ከሌማቱ ቂጣ እንጀራ ጋር ወደ እግዚአብሔር ያቀርባል፤ ካህኑም ደግሞ የእህሉን ቍርባንና የመጠጡን ቍርባን ያቀርባል።
18፤ ናዝራዊውም የተለየውን የራሱን ጠጕር በመገናኛው ድንኳን አጠገብ ይላጫል፥ የመለየቱንም ራስ ጠጕር ወስዶ ከደኅንነት መሥዋዕት በታች ወዳለው እሳት ይጥለዋል።
19፤ ካህኑም የተቀቀለውን የአውራውን በግ ወርች፥ ከሌማቱም አንድ ቂጣ እንጐቻ አንድም ስስ ቂጣ ይወስዳል፥ የተለየውንም የራስ ጠጕር ከተላጨ በኋላ በናዝራዊው እጆች ላይ ያኖራቸዋል፤
20፤ ካህኑም እነዚህን ለመወዝወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዛቸዋል፤ ይህም ከሚወዘወዘው ፍርምባና ከሚነሣው ወርች ጋር ለካህኑ የተቀደሰ ነው። ከዚያም በኋላ ናዝራዊው ወይን ይጠጣ ዘንድ ይችላል።
21፤ ስእለቱን የተሳለው የናዝራዊ፥ እጁም ከሚያገኘው ሌላ ስለ ናዝራዊነቱ ለእግዚአብሔር የሚያቀርበው የቍርባኑ ሕግ ይህ ነው፤ ስእለቱን እንደ ተሳለ እንደ ናዝራዊነቱ ሕግ እንዲሁ ያደርጋል።
22፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
23፤ ለአሮንና ለልጆቹ ንገራቸው። የእስራኤልን ልጆች ስትባርኩአቸው እንዲህ በሉአቸው።
24፤ እግዚአብሔር ይባርክህ፥ ይጠብቅህም፤
25፤ እግዚአብሔር ፊቱን ያብራልህ፥ ይራራልህም፤
26፤ እግዚአብሔር ፊቱን ወደ አንተ ያንሣ፥ ሰላምንም ይስጥህ።
27፤ እንዲሁ ስሜን በእስራኤል ልጆች ላይ ያደርጋሉ፤ እኔም እባርካቸዋለሁ።
ምዕራፍ 7
1፤ እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ ማደሪያውን ፈጽሞ ከተከለ በኋላ፥ እርሱንና ዕቃውን ሁሉ ከቀባና ከቀደሰ በኋላ፥ መሠዊያውንና ዕቃውንም ሁሉ ከቀባና ከቀደሰ በኋላ፤
2፤ የእስራኤል አለቆች፥ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች ቍርባናቸውን አቀረቡ፤ እነዚህም ከተቈጠሩት በላይ የተሾሙ የነገዶች አለቆች ነበሩ።
3፤ መባቸውንም በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ፥ የተከደኑ ስድስት ሰረገሎች አሥራ ሁለትም በሬዎች፤ በየሁለቱም አለቆች አንድ ሰረገላ አቀረቡ፥ ሁሉም እያንዳንዱ አንድ በሬ በማደሪያው ፊት አቀረቡ።
4፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
5፤ ለመገናኛው ድንኳን ማገልገል ይሆን ዘንድ ከእነርሱ ተቀብለህ ለሌዋውያን ለእያንዳንዱ እንደ አገልግሎታቸው ስጣቸው።
6፤ ሙሴም ሰረገሎችንና በሬዎችን ተቀብሎ ለሌዋውያን ሰጣቸው።
7፤ ለጌድሶን ልጆች እንደ አገልግሎታቸው ሁለት ሰረገሎችንና አራት በሬዎችን ሰጣቸው።
8፤ ከካህኑም ከአሮን ልጅ ከኢታምር እጅ በታች ላሉት ለሜራሪ ልጆች እንደ አገልግሎታቸው አራት ሰረገሎችንና ስምንት በሬዎችን ሰጣቸው።
9፤ ለቀዓት ልጆች ግን መቅደሱን ማገልገል የእነርሱ ነውና፥ በትከሻቸውም ይሸከሙት ነበርና ምንም አልሰጣቸውም።
10፤ መሠዊያውም በተቀባ ቀን አለቆቹ መሠዊያውን ለመቀደስ ቍርባንን አቀረቡ፤ አለቆችም መባቸውን በመሠዊያው ፊት አቀረቡ።
11፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። አለቆቹ መሠዊያውን ለመቀደስ መባቸውን እያንዳንዱ በቀን በቀኑ ያቅርቡ አለው።
12፤ በመጀመሪያውም ቀን መባውን ያቀረበ ከይሁዳ ነገድ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነበረ።
13፤ መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤
14፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
15፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤
16፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
17፤ ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የአሚናዳብ ልጅ የነአሶን መባ ይህ ነበረ።
18፤ በሁለተኛውም ቀን የይሳኮር አለቃ የሶገር ልጅ ናትናኤል አቀረበ።
19፤ ለመባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉትን፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነውን አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነውን አንድ የብር ድስት፤
20፤ ዕጣንም የተሞላውን ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነውን አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
21፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤
22፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
23፤ ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች አቀረበ፤ የሶገር ልጅ የናትናኤ መባ ይህ ነበረ።
18፤ በሁለተኛውም ቀን የይሳኮር አለቃ የሶገር ልጅ ናትናኤል አቀረበ።
19፤ ለመባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉትን፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነውን አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆvንውንአንድ የብር ድስት፤
20፤ ዕጣንም የተሞላውን ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነውን አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
21፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤
22፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
23፤ ለደኅነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች አቀረበ የሶገር ልጅ የናትናኤል መባ ይህ ነበረ።
24፤ በሦስተኛውም ቀን የዛብሎን ልጆች አለቃ የኬሎን ልጅ ኤልያብ፤
25፤ መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤
26፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
27፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤
28፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
29፤ ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የኬሎን ልጅ የኤልያብ መባ ይህ ነበረ።
30፤ በአራተኛውም ቀን የሮቤል ልጆች አለቃ የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር፤
31፤ መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤
32፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
33፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤
34፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
35፤ ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የሰዲዮር ልጅ የኤሊሱር መባ ይህ ነበረ።
36፤ በአምስተኛውም ቀን የስምዖን ልጆች አለቃ የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል፤
37፤ መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤
38፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
39፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤
40፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
41፤ ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የሱሪሰዳይ ልጅ የሰለሚኤል መባ ይህ ነበረ።
42፤ በስድስተኛውም ቀን የጋድ ልጆች አለቃ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ፤
43፤ መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ማዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤
44፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
45፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤
46፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
47፤ ለደኅነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የራጉኤል ልጅ የኤሊሳፍ መባ ይህ ነበረ።
48፤ በሰባተኛውም ቀን የኤፍሬም ልጆች አለቃ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ፤
49፤ መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑ ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤
50፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
51፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤
52፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
53፤ ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የዓሚሁድ ልጅ የኤሊሳማ መባ ይህ ነበረ።
54፤ በስምንተኛውም ቀን የምናሴ ልጆች አለቃ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል፤
55፤ መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤
56፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
57፤ ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤
58፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
59፤ ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የፍዳሱር ልጅ የገማልኤል መባ ነበረ።
60፤ በዘጠነኛውም ቀን የብንያም ልጆች አለቃ የጋዴዮን ልጅ አቢዳን፤
61፤ መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤
62፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
63፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤
64፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
65፤ ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የጋዴዮን ልጅ የአቢዳን መባ ይህ ነበረ።
66፤ በአሥረኛውም ቀን የዳን ልጆች አለቃ የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር፤
67፤ መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤
68፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
69፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤
70፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
71፤ ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የአሚሳዳይ ልጅ የአኪዔዘር መባ ይህ ነበረ።
72፤ በአሥራ አንደኛውም ቀን የአሴር ልጆች አለቃ የኤክራን ልጅ ፋግኤል፤
73፤ መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤
74፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
75፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤
76፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
77፤ ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የኤክራን ልጅ የፋግኤል መባ ይህ ነበረ።
78፤ በአሥራ ሁለተኛውም ቀን የንፍታሌም ልጆች አለቃ የዔናን ልጅ አኪሬ፤
79፤ መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤
80፤ ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤
81፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥
82፤ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤
83፤ ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የዔናን ልጅ የአኪሬ መባ ይህ ነበረ።
84፤ መሠዊያው በተቀባ ቀን የእስራኤል አለቆች ለመቀደሻው ያቀረቡት ቍርባን ይህ ነበረ፤ አሥራ ሁለት የብር ወጭቶች፥ አሥራ ሁለት የብር ድስቶች፥ አሥራ ሁለት የወርቅ ጭልፋዎች፤
85፤ እያንዳንዱም የብር ወጭት መቶ ሠላሳ ሰቅል፥ እያንዳንዱም ድስት ሰባ ሰቅል ነበረ፤ የዚህም ዕቃ ሁሉ ብር በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን ሁለት ሺህ አራት መቶ ሰቅል ነበረ።
86፤ ዕጣንም የተሞሉ አሥራ ሁለቱ የወርቅ ጭልፋዎች፥ እያንዳንዱ በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን አሥር አሥር ሰቅል ነበረ፤ የጭልፋዎቹ ወርቅ ሁሉ መቶ ሀያ ሰቅል ነበረ።
87፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት ከብት ሁሉ ከእህሉ ቍርባን ጋር አሥራ ሁለት ወይፈኖች፥ አሥራ ሁለትም አውራ በጎች፥ አሥራ ሁለትም የአንድ ዓመት ተባት ጠቦቶች ነበሩ፤ የኃጢአትም መሥዋዕት አውራ ፍየሎች አሥራ ሁለት ነበሩ።
88፤ የደኅንነትም መሥዋዕት ከብት ሁሉ ሀያ አራት በሬዎች፥ ስድሳም አውራ በጎች፥ ስድሳም አውራ ፍየሎች፥ ስድሳም የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበሩ። መሠዊያው ከተቀባ በኋላ ለመቀደሻው የቀረበ ቍርባን ይህ ነበረ።
89፤ ሙሴም ወደ መገናኛው ድንኳን እርሱን ለመነጋገር በገባ ጊዜ በምስክሩ ታቦት ላይ ካለው ከስርየት መክደኛ በላይ ከኪሩቤልም መካከል ድምፁ ሲናገረው ይሰማ ነበር፤ እርሱም ይናገረው ነበር።
ምዕራፍ 8
1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2፤ መብራቶቹን ስትለኵስ ሰባቱ መብራቶች በመቅረዙ ፊት ያበራሉ ብለህ ለአሮን ንገረው።
3፤ አሮንም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ በመቅረዙ ፊት መብራቶቹን ለኰሰ።
4፤ መቅረዙም እንዲህ ሆኖ ተሠርቶ ነበር፤ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ተሠራ፤ እስከ አገዳውና እስከ አበቦቹ ድረስ ከተቀጠቀጠ ሥራ ነበረ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳሳየው ምሳሌ መቅረዙን እንዲሁ አደረገ።
5፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
6፤ ከእስራኤል ልጆች መካከል ሌዋውያንን ወስደህ አንጻቸው።
7፤ ታነጻቸው ዘንድ እንዲህ ታደርግላቸዋለህ፤ ኃጢአትን የሚያነጻውን ውኃ እርጫቸው፥ በገላቸውም ሁሉ ምላጭ ያሳልፉ፥ ልብሳቸውንም ይጠቡ፥ ይታጠቡም።
8፤ ወይፈንን፥ ለእህሉም ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄትን ይውሰዱ፥ ሌላውንም ወይፈን ለኃጢአት መሥዋዕት ውሰድ።
9፤ ሌዋውያንንም በመገናኛው ድንኳን ፊት አቅርብ፤ የእስራኤልንም ልጆች ማኅበር ሁሉ ሰብስብ።
10፤ ሌዋውያንንም በእግዚአብሔር ፊት አቅርባቸው፤ የእስራኤልም ልጆች በሌዋውያን ላይ እጃቸውን ይጫኑባቸው።
11፤ አሮንም ሌዋውያን እግዚአብሔርን ያገለግሉ ዘንድ ከእስራኤል ልጆች መካከል ስጦታ አድርጎ፥ ሌዋውያንን በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ።
12፤ ሌዋውያኑም በወይፈኖቹ ራሶች ላይ እጆቻቸውን ይጫኑ፤ ለሌዋውያንም ስለ ማስተስረያ አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሁለተኛውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርብ።
13፤ ሌዋውያንንም በአሮንና በልጆቹ ፊት አቁማቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት ስጦታ አድርገህ አቅርባቸው።
14፤ እንዲሁ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይ፤ ሌዋውያንም ለእኔ ይሁኑ።
15፤ ከዚያም በኋላ ሌዋውያን የመገናኛውን ድንኳን አገልግሎት ያገለግሉ ዘንድ ይገባሉ፤ ታነጻቸውማለህ፥ ስጦታም አድርገህ ታቀርባቸዋለህ።
16፤ እነርሱም ከእስራኤል ልጆች መካከል ፈጽሞ ለእኔ ተሰጥተዋልና፤ በእስራኤል ልጆች በኵራት ሁሉ፥ ማኅፀን በሚከፍት ሁሉ ፋንታ ለእኔ ወስጄአቸዋለሁ።
17፤ በግብፅ ምድር ያለውን በኵር ሁሉ በገደልሁበት ቀን የእስራኤልን ልጆች በኵራት ሁሉ፥ ሰው ወይም እንስሳ፥ ለእኔ ቀድሼአቸዋለሁና የእኔ ናቸው።
18፤ በእስራኤልም ልጆች በኵራት ሁሉ ፋንታ ሌዋውያንን ወስጄአለሁ።
19፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ መቅደሱ በቀረቡ ጊዜ መቅሠፍት እንዳያገኛቸው፥ ለእስራኤል ልጆች ያስተሰርዩላቸው ዘንድ፥ የእስራኤልንም ልጆች አገልግሎት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለአሮንና ለልጆቹ ስጦታ አድርጌ ሰጥቼአቸዋለሁ።
20፤ ሙሴና አሮን የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲሁ በሌዋውያን ላይ አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ስለ ሌዋውያን እንዳዘዘው እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉላቸው።
21፤ ሌዋውያንም ከኃጢአት ተጣጠቡ፥ ልብሳቸውንም አጠቡ፤ አሮንም ስጦታ አድርጎ በእግዚአብሔር ፊት አቀረባቸው፥ አሮንም ያነጻቸው ዘንድ አስተሰረየላቸው።
22፤ ከዚያም በኋላ ሌዋውያን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በአሮንና በልጆቹ ፊት አገልግሎታቸውን ይሠሩ ዘንድ ገቡ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ስለ ሌዋውያን እንዳዘዘው እንዲሁ አደረጉላቸው።
23፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
24፤ የሌዋውያን ሕግ ይህ ነው፤ ከሀያ አምስት ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት በመገናኛው ድንኳን ሥራ ያገለግሉ ዘንድ ይገባሉ።
25፤ ዕድሜአቸውም አምሳ ዓመት ሲሞላ የአገልግሎታቸውን ሥራ ይተዋሉ፥ ከዚያም በኋላ አይሠሩም፤
26፤ የተሰጣቸውን ይጠብቁ ዘንድ ወንድሞቻቸውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለግላሉ፤ የድንኳኑን አገልግሎት አይሠሩም። እንዲሁ ስለ ሥራቸው በሌዋውያን ላይ ታደርጋለህ።
ምዕራፍ 9
1፤ ከግብፅ ምድር በወጡ በሁለተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር በሲና ምድረ በዳ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2፤ የእስራኤል ልጆች በጊዜው ፋሲካውን ያድርጉ፤
3፤ በዚህ ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በጊዜው አድርጉት፤ እንደ ሥርዓቱ ሁሉ እንደ ፍርዱም ሁሉ አድርጉት።
4፤ ሙሴም ፋሲካን ያደርጉ ዘንድ የእስራኤልን ልጆች ተናገራቸው።
5፤ በመጀመሪያውም ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በሲና ምድረ በዳ ፋሲካን አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉ።
6፤ በሞተ ሰው ሬሳ የረከሱ ሰዎችም ነበሩ፥ ስለዚህም በዚያ ቀን ፋሲካን ያደርጉ ዘንድ አልቻሉም። በዚያም ቀን ወደ ሙሴና ወደ አሮን ቀረቡ።
7፤ እነዚያም ሰዎች። በሞተ ሰው ሬሳ ረክሰናል፤ በእስራኤል ልጆች መካከል በጊዜው ቍርባን ለእግዚአብሔር እንዳናቀርብ ስለ ምን እንከለከላለን? አሉት።
8፤ ሙሴም። እግዚአብሔር ስለ እናንተ የሚያዝዘውን እስክሰማ ድረስ ቈዩ አላቸው።
9፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
10፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ከእናንተ ወይም ከትውልዶቻችሁ ዘንድ ሰው በሬሳ ቢረክስ፥ ወይም ሩቅ መንገድ ቢሄድ፥ እርሱ ደግሞ ለእግዚአብሔር ፋሲካን ያድርግ።
11፤ በሁለተኛው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ ያድርጉት፤ ከቂጣ እንጀራና ከመራራ ቅጠል ጋር ይብሉት።
12፤ ከእርሱም እስከ ነገ ምንም አያስቀሩ፥ ከእርሱም አጥንትን አይስበሩ፤ እንደ ፋሲካ ሥርዓት ሁሉ ያድርጉት።
13፤ ነገር ግን ንጹሕ የሆነ ሰው በመንገድም ላይ ያልሆነ ፋሲካን ባያደርግ፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ዘንድ ተለይቶ ይጠፋል፤ የእግዚአብሔርን ቍርባን በጊዜው አላቀረበምና ያ ሰው ኃጢአቱን ይሸከማል።
14፤ በመካከላችሁም መጻተኛ ቢኖር፥ ለእግዚአብሔር ፋሲካን ያደርግ ዘንድ ቢወድድ፥ እንደ ፋሲካ ሥርዓት እንደ ፍርዱም እንዲሁ ያድርግ፤ ለመጻተኛና ለአገር ልጅ አንድ ሥርዓት ይሁንላችሁ።
15፤ ማደሪያውም በተተከለ ቀን ደመናው የምስክሩን ድንኳን ሸፈነው፤ ከማታም ጀምሮ እስከ ጥዋት ድረስ በማደሪያው ላይ እንደ እሳት ይመስል ነበር።
16፤ እንዲሁ ሁልጊዜ ነበረ፤ በቀን ደመና በሌሊትም የእሳት አምሳል ይሸፍነው ነበር።
17፤ ደመናውም ከድንኳኑ ላይ በተነሣ ጊዜ በዚያን ጊዜ የእስራኤል ልጆች ይጓዙ ነበር፤ ደመናውም በቆመበት ስፍራ በዚያ የእስራኤል ልጆች ይሰፍሩ ነበር።
18፤ በእግዚአብሔር ትእዛዝ የእስራኤል ልጆች ይጓዙ ነበር፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ይሰፍሩ ነበር። ደመናው በማደሪያው ላይ በተቀመጠበት ዘመን ሁሉ በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር።
19፤ ደመናውም በማደሪያው ላይ ብዙ ቀን በተቀመጠ ጊዜ የእስራኤል ልጆች የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር፥ አይጓዙምም ነበር።
20፤ አንዳንድ ጊዜ ደመናው ጥቂት ቀን በማደሪያው ላይ ይሆን ነበር፤ በዚያን ጊዜ እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር፤ እንደ እግዚአብሔርም ትእዛዝ ይጓዙ ነበር።
21፤ አንዳንድ ጊዜም ደመናው ከማታ ጀምሮ እስከ ጥዋት ድረስ ይቀመጥ ነበር፤ በጥዋትም ደመናው በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር፤ በቀንም በሌሊትም ቢሆን፥ ደመናው በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር።
22፤ ደመናውም ሁለት ቀን ወይም አንድ ወር ወይም አንድ ዓመት ቆይቶ በማደሪያው ላይ ቢቀመጥ የእስራኤል ልጆች በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር፥ አይጓዙምም ነበር፤ ነገር ግን በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር።
23፤ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ይሰፍሩ ነበር፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ይጓዙ ነበር፥ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር።
ምዕራፍ 10
1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2፤ ሁለት የብር መለከቶች አጠፍጥፈህ ለአንተ አድርግ፤ ማኅበሩን ለመጥራት ከሰፈራቸውም ለማስጓዝ ይሁኑልህ።
3፤ ሁለቱም መለከቶች በተነፉ ጊዜ ማኅበሩ ሁሉ ወደ አንተ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይሰብሰቡ።
4፤ አንድ መለከት ሲነፋ ታላላቆቹ የእስራኤል አእላፍ አለቆች ወደ አንተ ይሰብሰቡ።
5፤ መለከትንም ከፍ ባለ ድምፅ ስትነፉ በምሥራቅ በኩል የሰፈሩት ይጓዙ።
6፤ ሁለተኛውንም ከፍ ባለ ድምፅ ስትነፉ በደቡብ በኩል የሰፈሩት ይጓዙ፤ ለማስጓዝ መለከትን ይነፋሉ።
7፤ ጉባኤውም በሚሰበሰብበት ጊዜ ንፉ፥ ነገር ግን ድምፁን ከፍ አታድርጉት።
8፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ መለከቶቹን ይንፉ፤ እነርሱም ለልጅ ልጃችሁ ለዘላለም ሥርዓት ይሁኑ።
9፤ በሚገፋችሁም ጠላት ላይ በምድራችሁ ወደ ሰልፍ ስትወጡ ከፍ ባለ ድምፅ መለከቶቹን ንፉ፤ በእግዚአብሔርም በአምላካችሁ ፊት ትታሰባላችሁ፥ ከጠላቶቻችሁም ትድናላችሁ።
10፤ ደግሞ በደስታችሁ ቀን፥ በበዓላታችሁም ዘመን፥ በወርም መባቻ፥ በሚቃጠል መሥዋዕታችሁና በደኅንነት መሥዋዕታችሁ ላይ መለከቶቹን ንፉ፤ እነርሱም በአምላካችሁ ፊት ለመታሰቢያ ይሆኑላችኋል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
11፤ በሁለተኛውም ዓመት በሁለተኛው ወር ከወሩም በሀያኛው ቀን እንዲህ ሆነ፤ ደመናው ከምስክሩ ማደሪያ ላይ ተነሣ።
12፤ የእስራኤልም ልጆች ከሲና ምድረ በዳ በየጕዞአቸው ተጓዙ፤ ደመናውም በፋራን ምድረ በዳ ቆመ።
13፤ በመጀመሪያም እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ ተጓዙ።
14፤ በመጀመሪያም የይሁዳ ልጆች ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን አለቃ ነበረ።
15፤ በይሳኮርም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የሶገር ልጅ ናትናኤል አለቃ ነበረ።
16፤ በዛብሎንም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የኬሎን ልጅ ኤልያብ አለቃ ነበረ።
17፤ ማደሪያውም ተነቀለ፤ ማደሪያውንም የተሸከሙ የጌድሶን ልጆችና የሜራሪ ልጆች ተጓዙ።
18፤ የሮቤልም ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር አለቃ ነበረ።
19፤ በስምዖንም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል አለቃ ነበረ።
20፤ በጋድም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ አለቃ ነበረ።
21፤ ቀዓታውያንም መቅደሱን ተሸክመው ተጓዙ፤ እነዚህም እስኪመጡ ድረስ እነዚያ ማደሪያውን ተከሉ።
22፤ የኤፍሬምም ልጆች ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ አለቃ ነበረ።
23፤ በምናሴም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል አለቃ ነበረ።
24፤ በብንያምም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የጋዴዮን ልጅ አቢዳን አለቃ ነበረ።
25፤ ከሰፈሮቹ ሁሉ በኋላ የሆነ የዳን ልጆች ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር አለቃ ነበረ።
26፤ በአሴርም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የኤክራን ልጅ ፋግኤል አለቃ ነበረ።
27፤ በንፍታሌምም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የዔናን ልጅ አኪሬ አለቃ ነበረ።
28፤ እንዲሁ የእስራኤል ልጆች ጕዞ በየሠራዊታቸው ነበረ፤ እነርሱም ተጓዙ።
29፤ ሙሴም የሚስቱን አባት የምድያማዊውን የራጉኤልን ልጅ ኦባብን። እግዚአብሔር። ለእናንተ እሰጠዋለሁ ወዳለው ስፍራ እንሄዳለን፤ እግዚአብሔር ስለ እስራኤል መልካምን ነገር ተናግሮአልና አንተ ከእኛ ጋር ና፥ መልካምን እናደርግልሃለን አለው።
30፤ እርሱም። አልሄድም፥ ነገር ግን ወደ አገሬና ወደ ዘመዶቼ እሄዳለሁ አለው።
31፤ እርሱም። እባክህ፥ በምድረ በዳ የምንሰፍርበትን አንተ ታውቃለህና፥ እንደ ዓይኖቻችንም ትሆንልናለህና አትተወን፤
32፤ ከእኛም ጋር ብትሄድ እግዚአብሔር ከሚያደርግልን መልካም ነገር ሁሉ እኛ ለአንተ እናደርጋለን አለ።
33፤ ከእግዚአብሔርም ተራራ የሦስት ቀን መንገድ ያህል ተጓዙ፤ የእግዚአብሔርም የኪዳኑ ታቦት የሚያድርበትን ስፍራ ይፈልግላቸው ዘንድ የሦስት ቀን መንገድ ቀደማቸው።
34፤ ከሰፈራቸውም በተጓዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ደመና ቀን ቀን በላያቸው ነበረ።
35፤ ሙሴም ታቦቱ በተጓዘ ጊዜ። አቤቱ፥ ተነሣ፥ ጠላቶችህም ይበተኑ፥ የሚጠሉህም ከፊትህ ይሽሹ ይል ነበር።
36፤ ባረፈም ጊዜ። አቤቱ፥ ወደ እስራኤል እልፍ አእላፋት ተመለስ ይል ነበር።
ምዕራፍ 11
1፤ ሕዝቡም ክፉ ሆነው በእግዚአብሔር ላይ አጕረመረሙ፤ እግዚአብሔርም ሰምቶ ተቈጣ፤ የእግዚአብሔርም እሳት በመካከላቸው ነደደች፥ የሰፈሩንም ዳር በላች።
2፤ ሕዝቡም ወደ ሙሴ ጮኹ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፥ እሳቲቱም ጠፋች።
3፤ የእግዚአብሔርም እሳት በመካከላቸው ስለነደደች የዚያን ስፍራ ስም ተቤራ ብሎ ጠራው።
4፤ በመካከላቸውም የነበሩ ልዩ ልዩ ሕዝብ እጅግ ጐመጁ፤ የእስራኤል ልጆች ደግሞ ያለቅሱ ነበር። የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል?
5፤ በግብፅ ያለ ዋጋ እንበላው የነበረውን ዓሣ፥ ዱባውንም፥ በጢኹንም፥ ኩራቱንም፥ ቀዩንም ሽንኩርት፥ ነጩንም ሽንኩርት እናስባለን፤
6፤ አሁን ግን ሰውነታችን ደረቀች፤ ዓይናችንም ከዚህ መና በቀር ምንም አታይም አሉ።
7፤ መናውም እንደ ድንብላል ዘር ነበረ፥ መልኩም ሙጫ ይመስል ነበር።
8፤ ሕዝቡም እየዞሩ ይለቅሙ ነበር፥ በወፍጮም ይፈጩት፥ ወይም በሙቀጫ ይወቅጡት፥ በምንቸትም ይቀቅሉት ነበር፥ እንጐቻም ያደርጉት ነበር፤ ጣዕሙም በዘይት እንደ ተለወሰ እንጐቻ ነበረ።
9፤ ሌሊትም ጠል በሰፈሩ ላይ በወረደ ጊዜ መናው በላዩ ይወርድ ነበር።
10፤ ሙሴም ሕዝቡ በወገኖቻቸው፥ ሰው ሁሉ በድንኳኑ ደጃፍ፥ ሲያለቅሱ ሰማ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ እጅግ ነደደ፤ ሙሴም ተቈጣ።
11፤ ሙሴም እግዚአብሔርን አለው። ለምን በባሪያህ ላይ ክፉ አደረግህ? ለምንስ በፊትህ ሞገስ አላገኘሁም? ለምንስ የዚህን ሕዝብ ሁሉ ሸክም በእኔ ላይ አደረግህ?
12፤ አንተ ለአባቶቻቸው ወደ ማልህላቸው ምድር አደርሳቸው ዘንድ። ሞግዚት የሚጠባውን ልጅ እንድታቀፍ በብብትህ እቀፋቸው የምትለኝ፥ በውኑ ይህን ሕዝብ ሁሉ እኔ ፀነስሁትን? ወለድሁትንስ?
13፤ በፊቴ ያለቅሳሉና። የምንበላውን ሥጋ ስጠን ይላሉና ለዚህ ሕዝብ ሁሉ የምሰጠው ሥጋ ከወዴት እወስዳለሁ?
14፤ እጅግ ከብዶኛልና ይህን ሁሉ ሕዝብ ልሸከም አልችልም።
15፤ እንዲህስ ከምታደርግብኝ፥ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፥ በእኔ ላይ የሚሆነውን መከራ እንዳላይ፥ እባክህ፥ ፈጽሞ ግደለኝ።
16፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ከእስራኤል ሽማግሌዎች፥ በሕዝቡ ላይ ሽማግሌዎችና አለቆች ይሆኑ ዘንድ የምታውቃቸውን፥ ሰባ ሰዎች ሰብስብልኝ፥ ወደ መገናኛውም ድንኳን አምጣቸው፥ በዚያም ከአንተ ጋር አቁማቸው።
17፤ እኔም እወርዳለሁ፥ በዚያም እነጋገርሃለሁ፥ በአንተ ካለውም መንፈስ ወስጄ በእነርሱ ላይ አደርገዋለሁ፤ አንተም ብቻ እንዳትሸከም የሕዝቡን ሸክም ከአንተ ጋር ይሸከማሉ።
18፤ ሕዝቡንም በላቸው። የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል? በግብፅ ደኅና ነበረልን እያላችሁ ያለቀሳችሁት ወደ እግዚአብሔር ጆሮ ደርሶአልና ለነገ ተቀደሱ፥ ሥጋንም ትበላላችሁ፤ እግዚአብሔርም ሥጋን ይሰጣችኋል፥ ትበሉማላችሁ።
19፤ አንድ ቀን ወይም ሁለት ቀን ወይም አምስት ቀን ወይም አሥር ቀን ወይም ሀያ ቀን አትበሉም፤
20፤ ነገር ግን በመካከላችሁ ያለውን እግዚአብሔርን ንቃችኋልና፥ በፊቱም። ለምን ከግብፅ ወጣን? ብላችሁ አልቅሳችኋልና በአፍንጫችሁ እስኪወጣ እስኪሰለቻችሁም ድረስ ወር ሙሉ ትበሉታላችሁ።
21፤ ሙሴም። እኔ በመካከላቸው ያለሁ ሕዝብ ስድስት መቶ ሺህ እግረኛ ናቸው፤ አንተም። ወር ሙሉ የሚበሉትን ሥጋ እኔ እሰጣቸዋለሁ አልህ።
22፤ እነርሱን የሚያጠግብ የበሬና የበግ መንጋ ይታረድን? ወይስ የባሕርን ዓሣ ሁሉ ያጠግባቸው ዘንድ ይሰበሰብላቸዋልን? አለ።
23፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። በውኑ የእግዚአብሔር እጅ አጭር ሆነ? አሁን ቃሌ ይፈጸም ወይስ አይፈጸም እንደ ሆነ አንተ ታያለህ አለው።
24፤ ሙሴም ወጣ የእግዚአብሔርንም ቃሎች ለሕዝቡ ነገረ፤ ከሕዝቡ ሽማግሌዎችም ሰባውን ሰዎች ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ አቆማቸው።
25፤ እግዚአብሔር በደመናው ወረደ፥ ተናገረውም፥ በእርሱም ላይ ከነበረው መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አደረገ፤ መንፈሱም በላያቸው ባደረ ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋል ግን አልተናገሩም።
26፤ ከእነርሱም ሁለት ሰዎች በሰፈር ቀርተው ነበር፥ የአንዱም ስም ኤልዳድ የሁለተኛውም ሞዳድ ነበረ፤ መንፈስም ወረደባቸው፤ እነርሱም ከተጻፉት ጋር ነበሩ ወደ ድንኳኑ ግን አልወጡም ነበር፤ በሰፈሩም ውስጥ ሳሉ ትንቢት ተናገሩ።
27፤ አንድ ጐበዝ ሰው እየሮጠ መጥቶ። ኤልዳድና ሞዳድ በሰፈር ትንቢት ይናገራሉ ብሎ ለሙሴ ነገረው።
28፤ ከልጅነቱ ጀምሮ የሙሴ አገልጋይ የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ። ጌታዬ ሙሴ ሆይ፥ ከልክላቸው አለው።
29፤ ሙሴም። የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፥ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ መንፈሱን ቢያወርድ፤ አንተ ስለእኔ ትቀናለህን? አለው።
30፤ ሙሴም ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ወደ ሰፈር ተመለሰ።
31፤ ነፋስም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጣ፥ ከባሕርም ድርጭቶችን አመጣ፥ የአንድ ቀንም መንገድ ያህል በዚህ፥ የአንድ ቀንም መንገድ ያህል በዚያ በሰፈሩ ላይ በተናቸው፤ በዚያም በሰፈሩ ዙሪያ ከፍታው ከምድር ወደ ላይ ሁለት ክንድ ነበረ።
32፤ በዚያም ቀን ሁሉ በሌሊትም ሁሉ በነጋውም ሁሉ ሕዝቡ ተነሥተው ድርጭትን ሰበሰቡ፤ ከሁሉ ጥቂት የሰበሰበ አሥር የቆሮስ መስፈሪያ የሚያህል ሰበሰበ፤ በሰፈሩም ዙሪያ ሁሉ አሰጡት።
33፤ ሥጋውም ገና በጥርሳቸው መካከል ሳለ ሳያኝኩትም፥ የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ መቅሠፍት እጅግ መታ።
34፤ የጐመጁ ሕዝብ በዚያ ተቀብረዋልና የዚያ ስፍራ ስም የምኞት መቃብር ተብሎ ተጠራ።
35፤ ሕዝቡም ከምኞት መቃብር ወደ ሐጼሮት ተጓዙ በሐጼሮትም ተቀመጡ።
ምዕራፍ 12
1፤ ሙሴም ኢትዮጵያይቱን አግብቶአልና ባገባት በኢትዮጵያይቱ ምክንያት ማርያምና አሮን በእርሱ ላይ ተናገሩ።
2፤ እነርሱም። በውኑ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻ ተናግሮአልን? በእኛስ ደግሞ የተናገረ አይደለምን? አሉ፤ እግዚአብሔርም ሰማ።
3፤ ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበረ።
4፤ እግዚአብሔርም ወዲያው ሙሴንና አሮንን ማርያምንም። ሦስታችሁ ወደ መገኛኛው ድንኳን ውጡ ብሎ ተናገረ፤ ሦስቱም ወጡ።
5፤ እግዚአብሔርም በደመና ዓምድ ወረደ፥ በድንኳኑም ደጃፍ ቆመ፤ አሮንንና ማርያምን ጠራ፥ ሁለቱም ወጡ።
6፤ እርሱም። ቃሌን ስሙ፤ በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር፥ እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ፥ ወይም በሕልም እናገረዋለሁ።
7፤ ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፤ እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው።
8፤ እኔ አፍ ለአፍ በግልጥ እናገረዋለሁ፥ በምሳሌ አይደለም፤ የእግዚአብሔርንም መልክ ያያል፤ በባሪያዬ በሙሴ ላይ ትናገሩ ዘንድ ስለ ምን አልፈራችሁም? አለ።
9፤ እግዚአብሔርም ተቈጥቶባቸው ሄደ።
10፤ ደመናውም ከድንኳኑ ተነሣ፤ እነሆም፥ ማርያም ለምጻም ሆነች፥ እንደ አመዳይም ነጭ ሆነች፤ አሮንም ማርያምን ተመለከተ፥ እነሆም፥ ለምጻም ሆና ነበር።
11፤ አሮንም ሙሴን። ጌታዬ ሆይ፥ ስንፍና አድርገናልና፥ በድለንማልና እባክህ፥ ኃጢአት አታድርግብን።
12፤ ከእናቱ ሆድ በወጣ ጊዜ ግማሽ ሥጋው ተበልቶ እንደ ሞተ እርስዋ አትሁን።
13፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር እየጮኸ። አቤቱ፥ እባክህ፥ አድናት አለው።
14፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። አባትዋ ምራቁን በፊትዋ ቢተፋባት ስንኳ ሰባት ቀን ታፍር ዘንድ ይገባት ነበር፤ ሰባት ቀን ከሰፈር ውጭ ተዘግታ ትቀመጥ፥ ከዚያም በኋላ ትመለስ አለው።
15፤ ማርያምም ከሰፈር ውጭ ሰባት ቀን ተዘግታ ተቀመጠች፤ ማርያምም እስክትመለስ ድረስ ሕዝቡ አልተጓዙም።
16፤ ከዚያም በኋላ ሕዝቡ ከሐጼሮት ተጓዙ፥ በፋራንም ምድረ በዳ ሰፈሩ።
ምዕራፍ 13
1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2፤ ለእስራኤል ልጆች የምሰጣትን የከንዓንን ምድር ይሰልሉ ዘንድ ሰዎችን ላክ፤ ከአባቶች ነገድ ሁሉ እያንዳንዱ በመካከላቸው አለቃ የሆነ አንድ ሰው ትልካላችሁ።
3፤ ሙሴም እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ ከፋራን ምድረ በዳ ላካቸው፤ እነርሱም ሁሉ የእስራኤል ልጆች አለቆች ነበሩ።
4፤ ስማቸውም ይህ ነበረ፤ ከሮቤል ነገድ የዘኩር ልጅ ሰሙኤል፤
5፤ ከስምዖን ነገድ የሱሬ ልጅ ሰፈጥ፤
6፤ ከይሁዳ ነገድ የዮፎኒ ልጅ ካሌብ፤
7፤ ከይሳኮር ነገድ የዮሴፍ ልጅ ይግአል፤
8፤ ከኤፍሬም ነገድ የነዌ ልጅ አውሴ፤
9፤
10፤ ከብንያም ነገድ የራፉ ልጅ ፈልጢ፤ ከዛብሎን ነገድ የሰዲ ልጅ ጉዲኤል፤
11፤ ከዮሴፍ ነገድ እርሱም የምናሴ ነገድ የሱሲ ልጅ ጋዲ፤
12፤ ከዳን ነገድ የገማሊ ልጅ ዓሚኤል፤
13፤ ከአሴር ነገድ የሚካኤል ልጅ ሰቱር፤
14፤ ከንፍታሌም ነገድ የያቢ ልጅ ናቢ፤
15፤ ከጋድ ነገድ የማኪ ልጅ ጉዲኤል።
16፤ ምድሪቱን ይሰልሉ ዘንድ ሙሴ የላካቸው ሰዎች ስም ይህ ነው። ሙሴም የነዌን ልጅ አውሴን ኢያሱ ብሎ ጠራው።
17፤ ሙሴም የከነዓንን ምድር ይሰልሉ ዘንድ ላካቸው፥ አላቸውም። ከዚህ በደቡብ በኩል ውጡ፥ ወደ ተራሮችም ሂዱ፤
18፤ ምድሪቱንም እንዴት እንደ ሆነች፥ በእርስዋም የሚኖሩ ሰዎች ብርቱዎች ወይም ደካሞች፥
19፤ ጥቂቶች ወይም ብዙዎች እንደ ሆኑ፥ የሚኖሩባትም ምድር መልካም ወይም ክፉ፥ የሚኖሩባቸውም ከተሞች ሰፈሮች ወይም አምቦች እንደ ሆኑ፥
20፤ ምድሪቱም ወፍራም ወይም ስስ ዛፍ ያለባት ወይም የሌለባት እንደ ሆነች እዩ፤ ከምድሪቱ ፍሬ አምጡ፤ አይዞአችሁ። በዚያን ጊዜም ወይኑ አስቀድሞ ፍሬ የሚያፈራበት ወራት ነበረ።
21፤ ወጡም ምድሪቱንም ከጺን ምድረ በዳ በሐማት ዳር እስካለችው እስከ ረአብ ድረስ ሰለሉ።
22፤ በደቡብም በኩል ውጡ፥ ወደ ኬብሮንም ደረሱ፤ በዚያም የዔናቅ ልጆች አኪመን፥ ሴሲ፥ ተላሚ ነበሩ። ኬብሮንም በግብፅ ካለችው ከጣኔዎስ በፊት ሰባት ዓመት ተሠርታ ነበር።
23፤ ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ መጡ፥ ከዚያም ከወይኑ አንድ ዘለላ የነበረበትን አረግ ቈረጡ፥ ሁለቱም ሰዎች በመሎጊያ ተሸከሙት፤ ደግሞም ከሮማኑ ከበለሱም አመጡ።
24፤ የእስራኤል ልጆች ከዚያ ስለ ቈረጡት ዘለላ የዚያን ስፍራ ስም የኤሽኮል ሸለቆ ብለው ጠሩት።
25፤ ምድሪቱንም ሰልለው ከአርባ ቀን በኋላ ተመለሱ።
26፤ በፋራን ምድረ በዳና በቃዴስ ወዳሉት ወደ ሙሴና ወደ አሮን ወደ እስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ሄደው ደረሱ፤ ወሬውንም ለእነርሱና ለማኅበሩ ሁሉ ነገሩአቸው፥ የምድሪቱንም ፍሬ አሳዩአቸው።
27፤ እንዲህም ብለው ነገሩት። ወደ ላክኸን ምድር ደረስን፥ እርስዋም ወተትና ማር ታፈስሳለች፥ ፍሬዋም ይህ ነው።
28፤ ነገር ግን በምድሪቱ የሚኖሩ ሰዎች ኃያላን ናቸው። ከተሞቻቸውም የተመሸጉ እጅግም የጸኑ ናቸው፤ ደግሞም በዚያ የዔናቅን ልጆች አየን።
29፤ በደቡብም ምድር አማሌቅ ተቀምጦአል፤ በተራሮቹም ኬጢያዊና ኢያቡሳዊ አሞራዊም ተቀምጠዋል፤ ከነዓናዊም በባሕር ዳርና በዮርዳኖስ አጠገብ ተቀምጦአል።
30፤ ካሌብም ሕዝቡን በሙሴ ፊት ዝም አሰኘና። ማሸነፍ እንችላለንንና እንውጣ፥ እንውረሰው አለ።
31፤ ከእርሱ ጋር የወጡ ሰዎች ግን። በኃይል ከእኛ ይበረታሉና በዚህ ሕዝብ ላይ መውጣት አንችልም አሉ።
32፤ ስለ ሰለሉአትም ምድር ክፉ ወሬ ለእስራኤል ልጆች እያወሩ። እኛ ዞረን የሰለልናት ምድር የሚኖሩባትን ሰዎች የምትበላ ምድር ናት፤ በእርስዋም ዘንድ ያየናቸው ሰዎች ሁሉ ረጃጅም ሰዎች ናቸው።
33፤ በዚያም ከኔፊሊም ወገን የሆኑትን ኔፊሊም፥ የዔናቅን ልጆች፥ አየን፤ እኛም በዓይናችን ግምት እንደ አንበጣዎች ነበርን፥ ደግሞም እኛ በዓይናቸው ዘንድ እንዲሁ ነበርን አሉ።
ምዕራፍ 14
1፤ ማኅበሩም ሁሉ ድምፃቸውን አንሥተው ጮኹ፤ ሕዝቡም በዚያ ሌሊት አለቀሱ።
2፤ የእስራኤልም ልጆች ሁሉ በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ፤ ማኅበሩም ሁሉ። በግብፅ ምድር ሳለን ምነው በሞትን ኖሮ! ወይም በዚህ ምድረ በዳ ምነው በሞትን ኖሮ!
3፤ እግዚአብሔርም በሰይፍ እንሞት ዘንድ ወደዚች ምድር ለምን ያገባናል? ሴቶቻችንና ልጆቻችን ምርኮ ይሆናሉ፤ ወደ ግብፅ መመለስ አይሻለንምን? አሉአቸው።
4፤ እርስ በርሳቸውም። ኑ፥ አለቃ ሾመን ወደ ግብፅ እንመለስ ተባባሉ።
5፤ ሙሴና አሮንም በእስራኤል ልጆች ጉባኤ ፊት በግምባራቸው ወደቁ።
6፤ ምድርን ከሰለሉት ጋር የነበሩት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ ልብሳቸውን ቀደዱ፤
7፤ ለእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ። ዞረን የሰለልናት ምድር እጅግ መልካም ናት።
8፤ እግዚአብሔርስ ከወደደን ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ወደዚች ምድር ያገባናል እርስዋንም ይሰጠናል።
9፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ አታምፁ፤ እንደ እንጀራ ይሆኑልናልና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩ፤ ጥላቸው ከላያቸው ተገፍፎአል፥ እግዚአብሔርም ከእኛ ጋር ነው፤ አትፍሩአቸው ብለው ተናገሩአቸው።
10፤ ማኅበሩ ሁሉ ግን በድንጋይ ይወግሩአቸው ዘንድ ተማከሩ። የእግዚአብሔርም ክብር ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ተገለጠ።
11፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። ይህ ሕዝብ እስከ መቼ ይንቀኛል? በፊቱስ ባደረግሁት ተአምራት ሁሉ እስከ መቼ አያምንብኝም?
12፤ ከርስታቸው አጠፋቸው ዘንድ በቸነፈር እመታቸዋለሁ፤ አንተም ከእነርሱ ለሚበዛና ለሚጠነክር ሕዝብ አደርግሃለሁ አለው።
13፤ ሙሴም እግዚአብሔርን አለው። ግብፃውያን ይሰማሉ፤ ይህን ሕዝብ ከመካከላቸው በኃይልህ አውጥተኸዋልና፤
14፤ ለዚችም ምድር ሰዎች ይናገራሉ። አንተ እግዚአብሔር በዚህ ሕዝብ መካከል እንደ ሆንህ ሰምተዋል፤ አንተም፥ አቤቱ፥ ፊት ለፊት ተገልጠሃል፥ ደመናህም በላያቸው ቆሞአል፥ በቀንም በደመና ዓምድ፥ በሌሊትም በእሳት ዓምድ በፊታቸው ትሄዳለህ።
15፤ ይህን ሕዝብ እንደ አንድ ሰው ብትገድል ዝናህን የሰሙ አሕዛብ።
16፤ እግዚአብሔር ይህን ሕዝብ ወደ ማለላቸው ምድር ያገባቸው ዘንድ አልቻለምና በምድረ በዳ ገደላቸው ብለው ይናገራሉ።
17፤
18፤ አሁንም፥ እባክህ። እግዚአብሔር ታጋሽና ምሕረቱ የበዛ፥ አበሳንና መተላለፍን ይቅር የሚል፥ ኃጢአተኞችንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችን ኃጢአት እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ ድረስ በልጆች ላይ የሚያመጣ ነው ብለህ እንደ ተናገርህ፥ የጌታ ኃይል ታላቅ ይሁን።
19፤ ይህን ሕዝብ ከግብፅ ምድር ካወጣህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይቅር እንዳልሃቸው፥ እባክህ፥ እንደ ምሕረትህ ብዛት የዚህን ሕዝብ ኃጢአት ይቅር በል።
20፤ እግዚአብሔርም አለ። እንደ ቃልህ ይቅር አልሁ፤
21፤ ነገር ግን እኔ ሕያው ነኛ በእውነት የእግዚአብሔር ክብር ምድርን ሁሉ ይሞላል።
22፤ በግብፅ ምድርና በምድረ በዳ ያደረግሁትን ተአምራቴንና ክብሬን ያዩ እነዚህ ሰዎች ሁሉ አሥር ጊዜ ስለ ተፈታተኑኝ፥
23፤ ነገሬንም ስላልሰሙ፥ በእውነት ለአባቶቻቸው የማልሁላቸውን ምድር አያዩም፤ ከእነርሱም የናቀኝ ሰው ሁሉ አያያትም፤
24፤ ባሪያዬ ካሌብ ግን ሌላ መንፈስ ከእርሱ ጋር ስለ ሆነ ፈጽሞም ስለተከተለኝ እርሱ ወደ ገባባት ምድር አገባዋለሁ፤ ዘሩም ይወርሳታል።
25፤ አማሌቅና ከነዓናዊውም በሸለቆው ውስጥ ተቀምጦአል፤ በነጋው ተመልሳችሁ በኤርትራ ባሕር መንገድ ወደ ምድረ በዳ ሂዱ።
26፤ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
27፤ የሚያጕረመርምብኝን ይህን ክፉ ሕዝብ እስከ መቼ እታገሠዋለሁ? በእኔ ላይ የሚያጕረመርሙትን የእስራኤልን ልጆች ማጕረምረም ሰማሁ።
28፤ እንዲህ በላቸው። እኔ ሕያው ነኝና በጆሮዬ እንደ ተናገራችሁት እንዲሁ በእውነት አደርግባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤
29፤ በድኖቻችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃሉ፤ የተቆጠራችሁ ሁሉ፥ እንደቁጥራችሁ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ የሆነ ሁሉ፥ እናንተ ያጕረመረማችሁብኝ፥
30፤ ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር በእርስዋ አስቀምጣችሁ ዘንድ እጄን ዘርግቼ ወደ ማልሁላችሁ ምድር በእውነት እናንተ አትገቡም።
31፤ ምርኮኛ ይሆናሉ ያላችኋቸውን ልጆቻችሁን እነርሱን አገባቸዋለሁ፥ እናንተም የናቃችኋትን ምድር ያውቃሉ።
32፤ እናንተ ግን በድኖቻችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃሉ።
33፤ ልጆቻችሁም በምድረ በዳ አርባ ዓመት ይቅበዘበዛሉ፥ በድኖቻችሁም በምድረ በዳ እስኪጠፉ ድረስ ግልሙትናችሁን ይሸከማሉ።
34፤ ምድሪቱን በሰላለችሁባት ቀን ቍጥር፥ አርባ ቀን፥ ስለ አንድ ቀንም አንድ ዓመት፥ ኃጢአታችሁን አርባ ዓመት ትሸከማላችሁ፥ ቍጣዬንም ታውቃላችሁ።
35፤ እኔ እግዚአብሔር። በእኔ ላይ በተሰበሰበ በዚህ ክፉ ማኅበር ሁሉ ላይ እንዲህ አደርጋለሁ ብዬ ተናገርሁ፤ በዚህ ምድረ በዳ ያልቃሉ፥ በዚያም ይሞታሉ።
36፤ ምድሪቱንም ሊሰልሉ ሙሴ ልኮአቸው የተመለሱት ሰዎች ክፉ ወሬም ስለ ምድሪቱ እያወሩ በእርሱ ላይ ማኅበሩ ሁሉ እንዲያጕረመርሙ ያደረጉ፥
37፤ ክፉ ወሬ ያወሩ እነዚያ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት በመቅሠፍት ሞቱ።
38፤ ነገር ግን ምድሪቱን ሊሰልሉ ከሄዱ ሰዎች የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ በሕይወት ተቀመጡ።
39፤ ሙሴም ይህን ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ነገረ፥ ሕዝቡም እጅግ አዘኑ።
40፤ በነጋውም ማልደው ተነሡ፥ ወደ ተራራውም ራስ መጥተው። እነሆ፥ መጣን፤ እኛ በድለናልና እግዚአብሔር ወዳለው ስፍራ እንወጣለን አሉ።
41፤ ሙሴም አለ። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? አይጠቅማችሁም።
42፤ እግዚአብሔር በእናንተ መካከል አይደለምና በጠላቶቻችሁ ፊት እንዳትወድቁ አትውጡ።
43፤ አማሌቃዊና ከነዓናዊ በፊታችሁ ናቸውና በሰይፍ ትወድቃላችሁ፤ እግዚአብሔርን ከመከተል ተመልሳችኋልና እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር አይሆንም።
44፤ እነርሱ ግን ወደ ተራራው ራስ ሊወጡ ደፈሩ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦትና ሙሴ ከሰፈሩ አልተነሡም።
45፤ በዚያም ተራራ ላይ የተቀመጡ አማሌቃዊና ከነዓናዊ ወረዱ፥ መትተዋቸውም እስከ ሔርማ ድረስ አሳደዱአቸው።
ምዕራፍ 15
1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ወደምሰጣችሁ ወደ መኖሪያችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ፥
3፤ ስእለታችሁን ልትፈጽሙ፥ ወይም በፈቃዳችሁ፥ ወይም በበዓላችሁ፥ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ ታደርጉ ዘንድ ከበሬ ወይም ከበግ መንጋ የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም መሥዋዕት የሚሆን የእሳት ቍርባን ለእግዚአብሔር ብታቀርቡ፥
4፤
5፤ ቍርባኑን ለእግዚአብሔር የሚያቀርብ ከሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ከሌላ መሥዋዕት ጋር ለእያንዳንዱ ጠቦት የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ በሆነ ዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ አንድ እጅ የሆነ መልካም ዱቄት ለእህል ቍርባን፥ የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን ያዘጋጃል።
6፤
7፤ ለአንዱም አውራ በግ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የኢን መስፈሪያ ሢሶ በሆነ ዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ መልካም ዱቄት ለእህል ቍርባን ታዘጋጃለህ፤ የኢን መስፈሪያ ሢሶም የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን ታቀርባለህ።
8፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት ወይም ለሌላ መሥዋዕት ወይም ስእለትን ለመፈጸም ወይም ለደኅንነት መሥዋዕት ወይፈንን ለእግዚአብሔር ብታዘጋጅ፥
9፤ ከወይፈኑ ጋር የኢን መስፈሪያ ግማሽ በሆነ ዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ መልካም ዱቄት ለእህል ቍርባን ታቀርባለህ።
10፤ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በእሳት ለተደረገ ቍርባን፥ የኢን መስፈሪያ ግማሽ የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን ታቀርባለ።
11፤ እንዲሁ ለእያንዳንዱ ወይፈን ወይም ለእያንዳንዱ አውራ በግ ወይም ለእያንዳንዱ ተባት የበግ ወይም የፍየል ጠቦት ይደረጋል።
12፤ እንዳዘጋጃችሁት ቍጥር፥ እንዲሁ እንደ ቍጥራቸው ለእያንዳንዱ ታደርጋላችሁ።
13፤ የአገር ልጅ ሁሉ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ቍርባን በእሳት ባቀረበ ጊዜ እንዲሁ ያደርጋል።
14፤ መጻተኛም ከእናንተ ጋር ቢቀመጥ፥ ወይም በትውልዳችሁ መካከል ማንም ሰው ቢኖር፥ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ቍርባን በእሳት ቢያቀርብ፥ እናንተ የምታደርጉትን እርሱ እንዲሁ ያደርጋል።
15፤ ለእናንተ በጉባኤው ላላችሁ በእናንተም መካከል ለሚቀመጥ መጻተኛ አንድ ሥርዓት ይሆናል፥ ለልጅ ልጃችሁም የዘላለም ሥርዓት ይሆናል፤ እናንተ እንደ ሆናችሁ እንዲሁ በእግዚአብሔር ፊት መጻተኛ ይሆናል።
16፤ ለእናንተና ከእናንተ ጋር ለሚቀመጥ መጻተኛ አንድ ሕግና አንድ ፍርድ ይሆናል።
17፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
18፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ወደማመጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ፥
19፤ እናንተ የምድሪቱን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ለእግዚአብሔር የማንሣት ቍርባን ታደርጋላችሁ።
20፤ መጀመሪያ ከምታደርጉት ሊጥ አንድ እንጐቻ ለማንሣት ቍርባን ታቀርባላችሁ፤ ከአውድማም እንደምታነሡት ቍርባን እንዲሁ ታነሣላችሁ።
21፤ መጀመሪያ ከምታደርጉት ሊጥ የማንሣት ቍርባን እስከ ልጅ ልጃችሁ ለእግዚአብሔር ትሰጣላችሁ።
22፤ ብትስቱም፥ እግዚአብሔርም ለሙሴ ያዘዛቸውን እነዚህን ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፥
23፤ እግዚአብሔር ካዘዘበት ከፊተኛው ቀን ጀምሮ ወደ ፊትም እስከ ልጅ ልጃችሁ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ ያዘዛችሁን ሁሉ ባታደርጉ፥
24፤ ማኅበሩ ሳያውቁ በስሕተት ቢደረግ፥ ማኅበሩ ሁሉ ለሚቃጠል መሥዋዕት ከእህሉ ቍርባንና ከመጠጡ ቍርባን ጋር እንደ ሕጉ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን አንድ ወይፈን፥ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል ያቀርባሉ።
25፤ ካህኑም ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ያስተሰርይላቸዋል፥ ስሕተትም ነበረና ይሰረይላቸዋል፤ ስለ ስሕተታቸውም ለእግዚአብሔር ቍርባናቸውን በእሳት አቅርበዋል፥ ለእግዚአብሔርም የኃጢአታቸውን መሥዋዕት አቅርበዋል።
26፤ በሕዝቡም ሁሉ ዘንድ ያለ እውቀት ተደርጎአልና ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በመካከላቸውም ለሚኖሩት መጻተኞች ስርየት ይደረግላቸዋል።
27፤ አንድ ሰው ሳያውቅ ኃጢአት ቢሠራ፥ ለኃጢአት መሥዋዕት አንዲት የአንድ ዓመት እንስት ፍየል ያቀርባል።
28፤ ኃጢአት ሠርቶ ሳያውቅ፥ ለሳተ ለዚያ ሰው ካህኑ ያስተሰርይለታል፤ በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል፥ ይሰረይለትማል።
29፤ ትውልዱ በእስራኤል ልጆች መካከል ቢሆን፥ ወይም በመካከላቸው የሚቀመጥ መጻተኛ ቢሆን፥ ሳያውቅ ኃጢአትን ለሚሠራ ሁሉ ሕጉ አንድ ይሆንለታል።
30፤ የአገር ልጅ ቢሆን ወይም መጻተኛ ቢሆን፥ አንዳች በትዕቢት የሚያደርግ ሰው እግዚአብሔርን ሰድቦአል፤ ያም ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋል።
31፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ናቀ፥ ትእዛዙንም ስለ ሰበረ፥ ያ ሰው ፈጽሞ ይጥፋ፤ ኃጢአቱ በራሱ ላይ ነው።
32፤ የእስራኤልም ልጆች በምድረ በዳ ሳሉ አንድ ሰው በሰንበት ቀን እንጨት ሲለቅም አገኙ።
33፤ እንጨትም ሲለቅም ያገኙት ሰዎች ወደ ሙሴና ወደ አሮን ወደ ማኅበሩም ሁሉ አመጡት።
34፤ ያደርጉበትም ዘንድ የሚገባው አልተገለጠምና በግዞት አስቀመጡት።
35፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። ሰውየው ፈጽሞ ይገደል፤ ከሰፈሩ ውጭ ማኅበሩ ሁሉ በድንጋይ ይውገሩት አለው።
36፤ ማኅበሩም ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ አወጡት፥ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ወገሩት።
37፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
38፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው። እነርሱም ትውልዶቻቸውም በልብሳቸው ጫፍ ዘርፍ ያደርጉ ዘንድ፥ በዘርፉም ሁሉ ላይ ሰማያዊ ፈትል ያደርጉ ዘንድ እዘዛቸው።
39፤ የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ ሁሉ ታስቡና ታደርጉ ዘንድ፥ እርስዋን በመከተል ያመነዘራችሁባትን የልባችሁንና የዓይኖቻችሁን ፈቃድ እንዳትከተሉ፥
40፤ ትእዛዜን ሁሉ ታስቡና ታደርጉ ዘንድ፥ ለአምላካችሁም ቅዱሳን ትሆኑ ዘንድ ዘርፉ በልብሳችሁ ላይ እንዲታይ ይሁን።
41፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ አምላክ እሆናችሁ ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
ምዕራፍ 16
1፤ የሌዊም ልጅ የቀዓት ልጅ የይስዓር ልጅ ቆሬ ከሮቤልም ልጆች የኤልያብ ልጆች ዳታንና አቤሮን የፋሌትም ልጅ ኦን በሙሴ ላይ ተነሡ። ች የኤልያብ ልጆች ዳታንና አቤሮን የፋሌትም ልጅ ኦን በሙሴ
2፤ ከእስራኤልም ልጆች ሁለት መቶ አምሳ ሰዎች ከእነርሱ ጋር ወሰዱ፤ ከጉባኤው የተመረጡ ዝናቸውም የተሰማ የማኅበሩ አለቆች ነበሩ።
3፤ በሙሴና በአሮን ላይ ተሰብስበው። ማኅበሩ ሁሉ እያንዳንዳቸው ቅዱሳን ናቸውና፥ እግዚአብሔርም በመካከላቸው ነውና እናንተ እጅግ አብዝታችኋል፤ በእግዚአብሔርም ጉባኤ ላይ ለምን ትታበያላችሁ? አሉ።
4፤ ሙሴም በሰማ ጊዜ በግምባሩ ወደቀ፤
5፤ ለቆሬም ለወገኑም ሁሉ። ነገ እግዚአብሔር ለእርሱ የሚሆነውን፥ ቅዱስም የሚሆነውን ያስታውቃል፤ የመረጠውንም ሰው ወደ እርሱ ያቀርበዋል።
6፤ እንዲሁ አድርጉ፤ ቆሬና ወገንህ ሁሉ፥ ጥናዎቹን ውሰዱ፤
7፤ ነገም በእግዚአብሔር ፊት እሳት አድርጉባቸው፥ ዕጣንም ጨምሩባቸው፤ እንዲህም ይሆናል፤ እግዚአብሔር የሚመርጠው እርሱ ቅዱስ ይሆናል፤ እናንተ የሌዊ ልጆች ሆይ እጅግ አብዝታችኋል ብሎ ተናገራቸው።
8፤ ሙሴም ቆሬን አለው። እናንተ የሌዊ ልጆች፥ ስሙ፤
9፤ የእስራኤል አምላክ ከእስራኤል ማኅበር የለያችሁ፥ የእግዚአብሔርንም ማደሪያ አገልግሎት ትሠሩ ዘንድ፥ እንድታገለግሉአቸውም በማኅበሩ ፊት ትቆሙ ዘንድ ወደ እርሱ ያቀረባችሁ አይበቃችሁምን?
10፤ አንተን ከአንተም ጋር የሌዊን ልጆች ወንድሞችህን ሁሉ ወደ እርሱ አቅርቦአል፤ ክህነትንም ደግሞ ትፈልጋላችሁን?
11፤ ስለዚህም አንተና ወገንህ ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ተሰብስባችኋል፤ በእርሱም ላይ ታጕረመርሙ ዘንድ አሮን ማን ነው?
12፤ ሙሴም የኤልያብን ልጆች ዳታንና አቤሮንን እንዲጠሩአቸው ላከ፤ እነርሱም። አንመጣም፤
13፤ በምድረ በዳ ትገድለን ዘንድ ወተትና ማር ከምታፈስሰው ምድር ያወጣኸን አይበቃህምን? ደግመህ በእኛ ላይ ራስህን አለቃ ታደርጋለህን?
14፤ ደግሞ ወተትና ማር ወደምታፈስስ ምድር አላገባኸንም፥ እርሻና ወይንም አላወረስኸንም፤ የእነዚህንስ ሰዎች ዓይኖቻቸውን ታወጣለህን? አንመጣም አሉ።
15፤ ሙሴም እጅግ ተቈጣ፥ እግዚአብሔርንም። ወደ ቍርባናቸው አትመልከት፤ እኔ ከእነርሱ አንድ አህያ ስንኳ አልወሰድሁም፥ ከእነርሱም አንድ ሰው አልበደልሁም አለው።
16፤ ሙሴም ቆሬን። ነገ አንተ፥ ወገንህም ሁሉ፥ አሮንም በእግዚአብሔር ፊት ሁኑ፤
17፤ ሁላችሁም ጥናዎቻችሁን ውሰዱ፥ ዕጣንም አድርጉባቸው፥ እያንዳንዳችሁም ጥናዎቻችሁን ወደ እግዚአብሔር ፊት አምጡ፥ ሁለት መቶ አምሳ ጥናዎች፤ አንተ ደግሞ አሮንም ጥናዎቻችሁን አምጡ አለው።
18፤ እያንዳንዱም ጥናውን ወሰደ፥ እሳትም አደረገበት፥ ዕጣንም ጨመረበት፥ ከሙሴና ከአሮንም ጋር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቆመ።
19፤ ቆሬም ማኅበሩን ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእነርሱ ላይ ሰበሰበ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ለማኅበሩ ሁሉ ተገለጠ።
20፤ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
21፤ ሁሉን በቅጽበት አጠፋቸው ዘንድ ከዚህ ማኅበር መካከል ፈቀቅ በሉ።
22፤ እነርሱም በግምባራቸው ወድቀው። አምላክ ሆይ፥ አንተ የሰው ሁሉ ነፍስ አምላክ፥ አንድ ሰው ኃጢአት ቢሠራ አንተ በማኅበሩ ሁሉ ላይ ትቈጣለህን? አሉ።
23፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
24፤ ለማኅበሩ። ከቆሬና ከዳታን ከአቤሮንም ማደሪያ ዙሪያ ፈቀቅ በሉ ብለህ ንገራቸው።
25፤ ሙሴም ተነሥቶ ወደ ዳታንና ወደ አቤሮን ሄደ፤ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ተከተሉት።
26፤ ማኅበሩንም። እባካችሁ፥ ከእነዚህ ክፉዎች ድንኳን ፈቀቅ በሉ፤ በኃጢአታቸውም ሁሉ እንዳትጠፉ ለእነርሱ የሆነውን ሁሉ አትንኩ ብሎ ተናገራቸው።
27፤ ከቆሬና ከዳታን ከአቤሮንም ማደሪያ ከዙሪያውም ሁሉ ፈቀቅ አሉ፤ ዳታንና አቤሮንም ሴቶቻቸውም ልጆቻቸውም ሕፃናቶቻቸውም ወጥተው በድንኳኖቻቸው ደጃፍ ቆሙ።
28፤ ሙሴም አለ። ይህን ሥራ ሁሉ አደርግ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ላከኝ እንጂ ከልቤ እንዳይደለ በዚህ ታውቃላችሁ።
29፤ እነዚህ ሰዎች ሰው እንደሚሞት ቢሞቱ፥ ወይም እንደ ሰው ሁሉ ቢቀሠፉ እግዚአብሔር አልላከኝም።
30፤ እግዚአብሔር ግን አዲስ ነገር ቢፈጥር፥ ምድርም አፍዋን ከፍታ እነርሱን ለእነርሱም ያለውን ሁሉ ብትውጣቸው፥ በሕይወታቸውም ወደ ሲኦል ቢወርዱ፥ ያን ጊዜ እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔርን እንደ ናቁ ታውቃላችሁ።
31፤ እንዲህም ሆነ፤ ይህን ቃል ሁሉ መናገር በፈጸመ ጊዜ ከበታቻቸው ያለው መሬት ተሰነጠቀ፤
32፤ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ እነርሱን ቤተ ሰቦቻቸውንም፥ ለቆሬም የነበሩትን ሰዎች ሁሉ፥ ዕቃዎቻቸውንም ሁሉ ዋጠቻቸው።
33፤ እነርሱም ለእነርሱም የነበሩ ሁሉ በሕይወታቸው ወደ ሲኦል ወረዱ፤ ምድሪቱም ተዘጋችባቸው፥ ከጉባኤውም መካከል ጠፉ።
34፤ በዙሪያቸው የነበሩ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ከጩኸታቸው የተነሣ። ምድሪቱ እንዳትውጠን ብለው በረሩ።
35፤ እሳትም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጥታ ያጥኑ የነበሩትን ሁለት መቶ አምሳ ሰዎች በላች።
36፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
37፤ ለካህኑ ለአሮን ልጅ ለአልዓዛር እንዲህ ብለህ ንገረው። ተቀድሰዋልና ጥናዎቹን ከተቃጠሉት ዘንድ ውሰድ፥ እሳቱንም ወደ ውጭ ጣለው፤
38፤ በኃጢአታቸው ሰውነታቸውን ያጠፉትን የእነዚያን ሰዎች ጥናዎች ጠፍጥፈህ ለመሠዊያ መለበጫ አድርጋቸው፤ በእግዚአብሔር ፊት አቅርበዋቸዋልና የተቀደሱ ናቸው፥ ለእስራኤልም ልጆች ምልክት ይሆናሉ።
39፤ ካህኑም አልዓዛር የተቃጠሉት ሰዎች ያቀረቡአቸውን የናስ ጥናዎች ወስዶ ጠፍጥፎም ለመሠዊያው መለበጫ አደረጋቸው።
40፤ በቆሬና በወገኑ የደረሰው እንዳይደርስበት፥ ከአሮን ልጆች ያልሆነ ሌላ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ዕጣን ያጥን ዘንድ እንዳይቀርብ፥ እግዚአብሔር በሙሴ እንደ ተናገረው፥ ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ አደረጋቸው።
41፤ በነጋውም የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ። እናንተ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ገድላችኋል ብለው በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ።
42፤ እንዲህም ሆነ፤ ማኅበሩ በሙሴና በአሮን ላይ በተሰበሰቡ ጊዜ ወደ መገናኛው ድንኳን አዩ፤ እነሆም፥ ደመናው ሸፈነው፥ የእግዚአብሔርም ክብር ተገለጠ።
43፤ ሙሴና አሮንም ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት መጡ።
44፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
45፤ ከዚህ ማኅበር መካከል ፈቀቅ በሉ፥ እኔም በቅጽበት አጠፋቸዋለሁ። በግምባራቸውም ወደቁ።
46፤ ሙሴም አሮንን። ጥናህን ውሰድ፥ ከመሠዊያውም ላይ እሳት አድርግበት፥ ዕጣንም ጨምርበት፥ ወደ ማኅበሩም ፈጥነህ ውሰደው አስተስርይላቸውም፤ ከእግዚአብሔር ፊት ቍጣ ወጥቶአልና መቅሠፍት ጀምሮአል አለው።
47፤ አሮንም ሙሴ እንደ ተናገረው ጥናውን ወስዶ ወደ ጉባኤው መካከል ሮጠ፤ እነሆም፥ መቅሠፍቱ በሕዝቡ መካከል ጀምሮ ነበር፤ ዕጣንም ጨመረ፥ ለሕዝቡም አስተሰረየላቸው።
48፤ በሙታንና በሕያዋን መካከል ቆመ፤ መቅሠፍቱም ተከለከለ።
49፤ በቆሬም ምክንያት ከሞቱት ሌላ በመቅሠፍቱ የሞቱት አሥራ አራት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ።
50፤ አሮንም ወደ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተመለሰ፤ መቅሠፍቱም ተከለከለ።
ምዕራፍ 17
1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2፤ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው፥ ከእነርሱም ከእያንዳንዱ ከየአባቶቻቸው ቤት አንድ አንድ በትር፥ ከአለቆቻቸው ከየአባቶቻቸው ቤት አሥራ ሁለት በትሮች፥ ውሰድ፤ የእያንዳንዱንም ስም በየበትሩ ላይ ጻፍ።
3፤ አንድ በትርም ለአባቶቻቸው ቤት አለቃ ይሆናልና በሌዊ በትር ላይ የአሮንን ስም ጻፍ።
4፤ እኔ ከእናንተ ጋር በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ፊት አኑራቸው።
5፤ እንዲህም ይሆናል፤ የመረጥሁት ሰው በትር ታቈጠቁጣለች፤ በእናንተም ላይ የሚያጕረመርሙባችሁን የእስራኤልን ልጆች ማጕረምረም ከእኔ ዘንድ አጠፋለሁ።
6፤ ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ተናገራቸው፤ አለቆቻቸው ሁሉ አሥራ ሁለት በትሮች፥ እያንዳንዱም አለቃ በየአባቱ ቤት አንድ አንድ በትር፥ ሰጡት፤ የአሮንም በትር በበትሮቻቸው መካከል ነበረች።
7፤ ሙሴም በትሮቹን በእግዚአብሔር ፊት በምስክሩ ድንኳን ውስጥ አኖራቸው።
8፤ እንዲህም ሆነ፤ በነጋው ሙሴ ወደ ምስክሩ ድንኳን ውስጥ ገባ፤ እነሆም፥ ለሌዊ ቤት የሆነች የአሮን በትር አቈጠቈጠች፥ ለመለመችም፥ አበባም አወጣች፥ የበሰለ ለውዝም አፈራች።
9፤ ሙሴም በትሮችን ሁሉ ከእግዚአብሔር ፊት ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ አወጣቸው፤ እነርሱም አዩ፥ እያንዳንዱም በትሩን ወሰደ።
10፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። የአሮንን በትር ወደ ምስክሩ ፊት መልስ፤ ማጕረምረማቸው ከእኔ ዘንድ እንዲጠፋ እነርሱም እንዳይሞቱ ለሚያምፁብኝ ልጆች ምልክት ሆና ትጠበቅ አለው።
11፤ ሙሴም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው እንዲሁ አደረገ።
12፤ የእስራኤልም ልጆች ሙሴን።እነሆ፥ እንሞታለን፥ እንጠፋለን፥ ሁላችንም እንጠፋለን።
13፤ የሚቀርብ ሁሉ፥ ወደ እግዚአብሔር ማደሪያ የሚቀርብ፥ ይሞታል፤ በውኑ ሁላችን እንሞታለንን? ብለው ተናገሩት።
ምዕራፍ 18
1፤ እግዚአብሔርም አሮንን አለው። አንተ ከአንተም ጋር ልጆችህና የአባቶችህ ቤት የመቅደስን ኃጢአት ትሸከማላችሁ፤ አንተም ከአንተም ጋር ልጆችህ የክህነታችሁን ኃጢአት ትሸከማላችሁ።
2፤ ደግሞም የአባትህን የሌዊን ነገድ ወንድሞችህን ከአንተ ጋር አቅርብ፤ ከአንተም ጋር በአንድነት ይሁኑ፥ ያገልግሉህም፤ አንተ ግን ከአንተም ጋር ልጆችህ በምስክሩ ድንኳን ፊት ትሆናላችሁ።
3፤ እነርሱም ትእዛዝህን የድንኳኑንም ሁሉ አገግሎት ይጠብቁ፤ ነገር ግን እንዳይሞቱ፥ እናንተም ደግሞ ከእነርሱ ጋር እንዳትሞቱ፥ እነርሱ ወደ መቅደሱ ዕቃና ወደ መሠዊያው አይቅረቡ።
4፤ ነገር ግን ከእናንተ ጋር በአንድነት ይሁኑ፥ ለድንኳኑም አገልግሎት ሁሉ የመገናኛውን ድንኳን ይጠብቁ፤ ሌላም ሰው ወደ እናንተ አይቅረብ።
5፤ እንደ ገና በእስራኤል ልጆች ላይ ቍጣ እንዳይሆንባቸው እናንተ መቅደሱንና መሠዊያውን ጠብቁ።
6፤ እኔም፥ እነሆ፥ ሌዋውያንን ወንድሞቻችሁን ከእስራኤል ልጆች መካከል ወስጄአለሁ፤ የመገናኛውን ድንኳን አገልግሎት ያደርጉ ዘንድ ለእግዚአብሔር የተሰጡ ለእናንተ ስጦታ ናቸው።
7፤ አንተም ከአንተም ጋር ልጆችህ ለመሠዊያው ሥራ የሚሆነውን ሁሉ፥ በመጋረጃውም ውስጥ የሚሆነውን ታደርጉ ዘንድ ክህነታችሁን ጠብቁ፥ አገልግሉም፤ ክህነቱን ለስጦታ አገልግሎት ሰጥቼአችኋለሁ፤ ሌላም ሰው ቢቀርብ ይገደል።
8፤ እግዚአብሔርም አሮንን ተናገረው እንዲህም አለው። እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ለእኔ የቀደሱትን የማንሣት ቍርባኔን ሁሉ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ፤ ስለ መቀባትህ ለአንተና ለልጆችህ ድርሻ እንዲሆን ለዘላለም ሰጥቼሃለሁ።
9፤ በእሳት ከሚቀርበው ከተቀደሰው ይህ ለአንተ ይሆናል፤ ለእኔ የሚያመጡት መባቸው ሁሉ፥ የእህሉ ቍርባናቸው ሁሉ፥ የኃጢአታቸውም መስዋዕት ሁሉ፥ የበደላቸውም መሥዋዕት ሁሉ፥ ለአንተ ለልጆችህም የተቀደሰ ይሆናል።
10፤ በተቀደሰ ስፍራ ብላው፤ ወንዶች ሁሉ ይብሉት፤ የተቀደሰ ይሆንልሃል።
11፤ ይህም ለአንተ ነው፤ የእስራኤል ልጆች ለስጦታ ያቀረቡትን የማንሣትና የመወዝወዝ ቍርባን ሁሉ ለአንተ ከአንተም ጋር ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችህ ድርሻ እንዲሆን ለዘላለም ሰጥቼሃለሁ፤ በቤትህ ውስጥ ንጹሕ የሆነ ሁሉ ይብላው።
12፤ ለእግዚአብሔር ከሚሰጡት የፍሬ መጀመሪያ ከዘይትና ከወይን ከእህልም የተመረጠውን ሁሉ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ።
13፤ ወደ እግዚአብሔር የሚያመጡት በምድራቸው ያለው ሁሉ የፍሬ መጀመሪያ ለአንተ ይሆናል፤ በቤትህ ውስጥ ንጹሕ የሆነ ሁሉ ይብላው።
14፤ በእስራኤል ዘንድ እርም የሆነው ሁሉ ለአንተ ይሆናል።
15፤ ከሰው ወይም ከእንስሳ ቢሆን፥ ለእግዚአብሔር ከሚያቀርቡት ሥጋ ሁሉ ማኅፀን የሚከፍት ሁሉ ለአንተ ይሆናል፤ ነገር ግን የሰውን በኵራት ፈጽሞ ትቤዠዋለህ፥ ያልነጻውንም እንስሳ በኵራት ትቤዠዋለህ።
16፤ ከአንድ ወር ጀምሮ የምትቤዠውን እንደ ግምትህ ትቤዠዋለህ፤ ግምቱም እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን አምስት ሰቅል ይሆናል፤ እርሱም ሀያ አቦሊ ነው።
17፤ ነገር ግን የላም በኵራት ወይም የበግ በኵራት ወይም የፍየል በኵራት አትቤዥም፤ የተቀደሱ ናቸው፤ ደማቸውን በመሠዊያው ላይ ትረጨዋለህ፥ ስባቸውንም ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ለእሳት ቍርባን ታቃጥለዋለህ።
18፤ ሥጋቸውም ለአንተ ይሆናል፤ እንደ መወዝወዝ ፍርምባ እንደ ቀኙም ወርች ለአንተ ይሆናል።
19፤ የእስራኤል ልጆች ከተቀደሰው ነገር ሁሉ አንሥተው ለእግዚአብሔር ያቀረቡትን ለአንተ ከአንተም ጋር ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችህ ድርሻ እንዲሆን ለዘላለም ሰጥቼሃለሁ፤ በእግዚአብሔር ፊት ለአንተ ከአንተም ጋር ለዘርህ የጨው ቃል ኪዳን ለዘላለም ነው።
20፤ እግዚአብሔርም አሮንን አለው። በምድራቸው ርስት በመካከላቸውም ድርሻ አይሆንልህም፤ በእስራኤል ልጆች መካከል ድርሻህና ርስትህ እኔ ነኝ።
21፤ ለሌዊም ልጆች፥ እነሆ፥ በመገናኛው ድንኳን አገልግሎት ስለሚያገለግሉ፥ የእስራኤልን ልጆች አሥራት ርስት አድርጌ ሰጥቼአለሁ።
22፤ ከዚህም በኋላ ኃጢአትን እንዳይሸከሙ እንዳይሞቱም፥ የእስራኤል ልጆች ወደ መገናኛው ድንኳን አይቅረቡ።
23፤ ሌዋውያን ግን የመገናኛውን ድንኳን አገልግሎት ይሥሩ፥ እነርሱም ኃጢአታቸውን ይሸከማሉ፤ ለልጅ ልጃችሁ ለዘላለም ሥርዓት ይሆናል፤ በእስራኤልም ልጆች መካከል ርስት አይወርሱም።
24፤ ለእግዚአብሔር የማንሣት ቍርባን የሚያቀርቡትን የእስራኤልን ልጆች አሥራት ለሌዋውያን ርስት አድርጌ ሰጥቼአለሁ፤ ስለዚህ። በእስራኤል ልጆች መካከል ርስት አይወርሱም አልኋቸው።
25፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
26፤ ለሌዋውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ከእስራኤል ልጆች ለእናንተ ርስት አድርጌ የሰጠኋችሁን አሥራት በተቀበላችሁ ጊዜ፥ ለእግዚአብሔር ለማንሣት ቍርባን የአሥራት አሥራት ታቀርባላችሁ።
27፤ የማንሣት ቍርባናችሁም እንደ አውድማው እህልና እንደ ወይን መጭመቂያው ፍሬ ይቈጠርላችኋል።
28፤ እንዲሁ እናንተ ደግሞ ከእስራኤል ልጆች ከምትቀበሉት አሥራት ሁሉ ለእግዚአብሔር የማንሣት ቍርባን ታቀርባላችሁ፤ የእግዚአብሔርንም የማንሣት ቍርባን ለካህኑ ለአሮን ትሰጣላችሁ።
29፤ ከምትቀበሉት ስጦታ ሁሉ፥ ከተመረጠው ከተቀደሰውም ድርሻ ሁሉ፥ የእግዚአብሔርን የማንሣት ቍርባን ሁሉ ታቀርባላችሁ።
30፤ ስለዚህ ትላቸዋለህ። ከእርሱ የተመረጠውን ባነሣችሁ ጊዜ እንደ አውድማው እህልና እንደ ወይን መጭመቂያው ፍሬ ለሌዋውያን ይቈጠራል።
31፤ እናንተም ቤተ ሰቦቻችሁም፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የማገልገላችሁ ዋጋ ነውና በሁሉ ስፍራ ትበሉታላችሁ።
32፤ የተመረጠውንም ከእርሱ ባነሣችሁ ጊዜ ስለ እርሱ ኃጢአትን አትሸከሙም፤ እንዳትሞቱም የእስራኤል ልጆች የቀደሱትን አታረክሱም።
ምዕራፍ 19
1፤ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
2፤ እግዚአብሔር ያዘዘው የሕጉ ትእዛዝ ይህ ነው፤ መልካሚቱን፥ ነውርም የሌለባትን፥ ቀንበርም ያልተጫነባትን ቀይ ጊደር ያመጡልህ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው።
3፤ እርስዋንም ለካህኑ ለአልዓዛር ትሰጣላችሁ፥ እርስዋንም ከሰፈር ወደ ውጭ ይወስዳታል፥ አንድ ሰውም በፊቱ ያርዳታል።
4፤ ካህኑም አልዓዛር ከደምዋ በጣቱ ይወስዳል፥ ከደምዋም ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት ሰባት ጊዜ ይረጫል።
5፤ ጊደሪቱም በፊቱ ትቃጠላለች፤ ቁርበትዋም ሥጋዋም ደምዋም ፈርስዋም ይቃጠላል።
6፤ ካህኑም የዝግባ እንጨት ሂሶጵም ቀይ ግምጃም ወስዶ ጊደሪቱ በምትቃጠልበት እሳት መካከል ይጥለዋል።
7፤ ካህኑም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ይገባል፤ ካህኑም እስከ ማታ ርኩስ ይሆናል።
8፤ ያቃጠላትም ሰው ልብሱን በውኃ ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል።
9፤ ንጹሕም ሰው የጊደሪቱን አመድ ያከማቻል ከሰፈሩም ውጭ በንጹሕ ስፍራ ያኖረዋል፤ ርኵሰትም ለሚያነጻ ውኃ ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ይጠበቃል፤ ከኃጢአት ለማንጻት የሚሆን ነው።
10፤ የጊደሪቱንም አመድ ያከማቸ ሰው ልብሱን ያጥባል እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ይህም ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸውም ለሚኖር መጻተኛ ለዘላለም ሥርዓት ይሆናል።
11፤ የሞተውን ሰው በድን የሚነካ ሰባት ቀን ርኵስ ይሆናል፤
12፤ በዚህም ውኃ በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ያጠራል፥ ንጹሕም ይሆናል፤ ነገር ግን በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ባያጠራ ንጹሕ አይሆንም።
13፤ የሞተውን ሰው በድን የነካ ሁለመናውን ባያጠራ የእግዚአብሔርን ማደሪያ ያረክሳል፤ ያ ሰው ከእስራኤል ዘንድ ተለይቶ ይጠፋል፤ በእርሱም ላይ የሚያነጻ ውኃ አልተረጨምና ርኩስ ይሆናል፤ ርኵሰቱ ገና በእርሱ ላይ ነው።
14፤ ሰው በድንኳን ውስጥ ቢሞት ሕጉ ይህ ነው፤ ወደ ድንኳኑ የሚገባ ሁሉ በድንኳኑም ውስጥ ያለው ሁሉ ሰባት ቀን ርኵስ ይሆናል።
15፤ መክደኛው ያልታሰረ የተከፈተ ዕቃ ሁሉ ርኩስ ነው።
16፤ በሜዳም በሰይፍ የተገደለውን ወይም የሞተውን በድን ወይም የሰውን አጥንት ወይም መቃብር የሚነካ ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል።
17፤ ከኃጢአት ለማንጻት እንድትሆን ከተቃጠለችው ጊደር አመድ ለርኩሱ ይወስዱለታል፥ በዕቃውም ውስጥ የምንጭ ውኃ ይቀላቀልበታል።
18፤ ንጹሕም ሰው ሂሶጱን ወስዶ በውኃው ውስጥ ያጠልቀዋል፤ በድንኳኑም፥ በዕቃውም ሁሉ፥ በዚያም ባሉ ሰዎች ላይ፥ አጥንቱንም ወይም የተገደለውን ወይም የሞተውን ወይም መቃብሩን በነካው ላይ ይረጨዋል፤
19፤ ንጹሑም በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን በርኩሱ ላይ ይረጨዋል፤ ባሰባተኛውም ቀን ያጠራዋል፤ እርሱም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ በማታም ጊዜ ንጹሕ ይሆናል።
20፤ ሰውም ርኩስ ቢሆን ሁለመናውንም ባያጠራ፥ ያ ሰው የእግዚአብሔርን መቅደስ አርክሶአልና ከጉባኤው መካከል ተለይቶ ይጠፋል፤ በሚያነጻ ውኃ አልተረጨም፤ ርኩስ ነው።
21፤ ይህም የዘላለም ሥርዓት ይሆንላችኋል፤ የሚያነጻውን ውኃ የሚረጭ ሰው ልብሱን ያጥባል፤ የሚያነጻውንም ውኃ የሚነካ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።
22፤ ርኩሱም የሚነካው ነገር ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ የሚነካውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።
ምዕራፍ 20
1፤ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ በመጀመሪያው ወር ወደ ጺን ምድረ በዳ መጡ፤ ሕዝቡም በቃዴስ ተቀመጡ፤ ማርያምም በዚያ ሞተች፥ በዚያም ተቀበረች።
2፤ ለማኅበሩም ውኃ አልነበረም፤ በሙሴና በአሮንም ላይ ተሰበሰቡ።
3፤ ሕዝቡም ሙሴን ተጣሉት፥ እንዲህም ብለው ተናገሩት። ወንድሞቻችን በእግዚአብሔር ፊት በሞቱ ጊዜ እኛም ምነው በሞትን ኖሮ!
4፤ እኛ ከብቶቻችንም በዚያ እንሞት ዘንድ የእግዚአብሔርን ጉባኤ ወደዚህ ምድረ በዳ ለምን አመጣችሁ?
5፤ ወደዚህ ክፉ ስፍራ ታመጡን ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? ዘርና በለስ ወይንም ሮማንም የሌለበት ስፍራ ነው፤ የሚጠጣም ውኃ የለበትም።
6፤ ሙሴና አሮንም ከጉባኤው ፊት ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሂደው በግምባራቸው ወደቁ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ተገለጠላቸው።
7፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
8፤ በትርህን ውሰድ፤ አንተና ወንድምህ አሮን ማኅበሩን ሰብስቡ፥ ድንጋዩም ውኃን እንዲሰጥ እነርሱ ሲያዩ ተናገሩት፤ ከድንጋዩም ውኃ ታወጣላቸዋለህ፤ እንዲሁም ማኅበሩን ከብቶቻቸውንም ታጠጣላቸዋለህ።
9፤ ሙሴም እንደ ታዘዘ በትሩን ከእግዚአብሔር ፊት ወሰደ።
10፤ ሙሴና አሮንም ጉባኤውን በድንጋዩ ፊት ሰብስበው። እናንተ ዓመፀኞች፥ እንግዲህ ስሙ፤ በውኑ ከዚህ ድንጋይ ውኃን እናወጣላችኋለን? አላቸው።
11፤ ሙሴም እጁን ዘርግቶ ድንጋዩን ሁለት ጊዜ በበትሩ መታው፤ ብዙም ውኃ ወጣ፥ ማኅበሩም ከብቶቻቸውም ጠጡ።
12፤ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን። በእስራኤል ልጆች ፊት ትቀድሱኝ ዘንድ በእኔ አላመናችሁምና ስለዚህ ወደ ሰጠኋቸው ምድር ይህን ጉባኤ ይዛችሁ አትገቡም አላቸው።
13፤ የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ላይ ጠብ ያደረጉበት፥ እርሱም ቅዱስ መሆኑን የገለጠበት ይህ የመሪባ ውኃ ነው።
14፤ ሙሴም ከቃዴስ ወደ ኤዶምያስ ንጉሥ መልእክተኞችን እንዲህ ብሎ ላከ። ወንድምህ እስራኤል እንዲህ ይላል። ያገኘንን መከራ ሁሉ አንተ ታውቃለህ፤
15፤ አባቶቻችን ወደ ግብፅ ወረዱ፥ በግብፅም እጅግ ዘመን ተቀመጥን ግብፃውያንም እኛንና አባቶቻችንን በደሉ፤
16፤ ወደ እግዚአብሔርም በጮኽን ጊዜ ድምፃችንን ሰማ፥ መልአክንም ሰድዶ ከግብፅ አወጣን፤ እነሆም፥ በምድርህ ዳርቻ ባለችው ከተማ በቃዴስ ተቀምጠናል።
17፤ እባክህ፥ በምድርህ ላይ እንለፍ፤ ወደ እርሻም ወደ ወይንም አንገባም፥ ከጕድጓዶችም ውኃን አንጠጣም፤ በንጉሡ ጐዳና እንሄዳለን፥ ዳርቻህንም እስክናልፍ ድረስ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አንልም።
18፤ ኤዶምያስም። በሰይፍ እንዳልገጥምህ በምድሬ ላይ አታልፍም አለው።
19፤ የእስራኤልም ልጆች። በጐዳናው እንሄዳለን፥ እኔም ከብቶቼም ከውኃህ ብንጠጣ ዋጋውን እንከፍላለን፥ ሌላም ምንም አናደርግም፤ ብቻ በእግራችን እንለፍ አሉት።
20፤ እርሱም። አታልፍም አለ። ኤዶምያስም በብዙ ሕዝብና በጽኑ እጅ ሊገጥመው ወጣ።
21፤ ኤዶምያስም እስራኤል በዳርቻው እንዳያልፍ ከለከለ፤ ስለዚህ እስራኤል ከእርሱ ተመለሰ።
22፤ ከቃዴስም ተጓዙ፤ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ወደ ሖር ተራራ መጡ።
23፤ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን በኤዶምያስ ምድር ዳርቻ ባለው በሖር ተራራ እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
24፤ አሮን ወደ ወገኑ ይከማች፤ በመሪባ ውኃ ዘንድ በቃሌ ላይ ስለ ዐመፃችሁ ለእስራኤል ልጆች ወደ ሰጠኋት ምድር አይገባም።
25፤ አሮንና ልጁን አልዓዛርን ይዘህ ወደ ሖር ተራራ ላይ አምጣቸው፤
26፤ ከአሮንም ልብሱን አውጣ፥ ልጁንም አልዓዛርን አልብሰው፤ አሮንም ወደ ወገኑ ይከማች፥ በዚያም ይሙት።
27፤ ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘ አደረገ፤ ማኅበሩም ሁሉ እያዩ ወደ ሖር ተራራ ወጡ።
28፤ ሙሴም የአሮንን ልብስ አወጣ፥ ልጁንም አልዓዛርን አለበሰው፤ አሮንም በዚያ በተራራው ራስ ላይ ሞተ፤ ሙሴና አልዓዛርም ከተራራው ወረዱ።
29፤ ማኅበሩም ሁሉ አሮን እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ፥ የእስራኤል ቤት ሁሉ ለአሮን ሠላሳ ቀን አለቀሱ።
ምዕራፍ 21
1፤ በደቡብም በኩል ተቀምጦ የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ በአታሪም መንገድ እስራኤል እንደ መጡ ሰማ፤ ከእስራኤልም ጋር ሰልፍ አደረገ ከእነርሱም ምርኮ ማረከ።
2፤ እስራኤልም ለእግዚአብሔር። እነዚህን አሳልፈህ በእጄ ብትሰጣቸው ከተሞቻቸውን እርም ብዬ አጠፋለሁ ብሎ ስእለት ተሳለ።
3፤ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ድምፅ ሰማ፥ ከነዓናውያንንም አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱንም ከተሞቻቸውንም እርም ብለው አጠፉ፤ የዚያንም ስፍራ ስም ሔርማ ብለው ጠሩት።
4፤ ከሖርም ተራራ ከኤዶምያስ ምድር ርቀው ሊዞሩ በኤርትራ ባሕር መንገድ ተጓዙ፤ የሕዝቡም ሰውነት ከመንገዱ የተነሣ ደከመ።
5፤ ሕዝቡም በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ። በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? እንጀራ የለም፥ ውኃ የለም፤ ሰውነታችንም ይህን ቀላል እንጀራ ተጸየፈ ብለው ተናገሩ።
6፤ እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ እባቦችን ሰደደ፥ ሕዝቡንም ነደፉ፤ ከእስራኤልም ብዙ ሰዎች ሞቱ።
7፤ ሕዝቡም ወደ ሙሴ መጥተው። በእግዚአብሔርና በአንተ ላይ ስለ ተናገርን በድለናል፤ እባቦችን ከእኛ ያርቅልን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን አሉት።
8፤ ሙሴም ስለ ሕዝቡ ጸለየ። እግዚአብሔርም ሙሴን። እባብን ሠርተህ በዓላማ ላይ ስቀል፤ የተነደፈውም ሁሉ ሲያያት በሕይወት ይኖራል አለው።
9፤ ሙሴም የናሱን እባብ ሠርቶ በዓላማ ላይ ሰቀለ፤ እባብም የነደፈችው ሰው ሁሉ የናሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ።
10፤ የእስራኤልም ልጆች ተጓዙ፥ በኦቦትም ሰፈሩ።
11፤ ከኦቦትም ተጕዘው በሞዓብ ፊት ለፊት ባለችው ምድረ በዳ፥ በፀሐይ መውጫ በኩል፥ በዒዬዓባሪም ሰፈሩ።
12፤ ከዚያም ተጕዘው በዘሬድ ሸለቆ ሰፈሩ።
13፤ ከዚያም ተጕዘው ከአሞራውያን ዳርቻ በሚወጣው ምድረ በዳ ውስጥ በአሮኖን ማዶ ሰፈሩ፤ አሮኖን በሞዓብና በአሞራውያን መካከል ያለ የሞዓብ ዳርቻ ነውና።
14፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር የጦርነት መጽሐፍ እንዲህ ተባለ። ዋሄብ በሱፋ፥ የአርኖንም ሸለቆች፥
15፤ ወደ ዔር ማደሪያ የሚወርድ በሞዓብም ዳርቻ የሚጠጋ የሸለቆች ፈሳሽ።
16፤ ከዚያም ወደ ብኤር ተጓዙ፤ ይኸውም እግዚአብሔር ሙሴን። ሕዝቡን ሰብስብ ውኃንም እሰጣቸዋለሁ ብሎ የተናገረለት ጕድጓድ ነው።
17፤ በዚያም ጊዜ እስራኤል ይህን መዝሙር ዘመረ። አንተ ምንጭ ሆይ፥ ፍለቅ፤ እናንተ ዘምሩለት፤
18፤ በበትረ መንግሥት በበትራቸውም የሕዝብ አዛውንቶች ያጐደጐዱት፥ አለቆችም የቈፈሩት ጕድጓድ።
19፤ ከምድረ በዳም ወደ መቴና ተጓዙ፤ ከመቴናም ወደ ነሃሊኤል፥ ከነሃሊኤልም ወደ ባሞት፥
20፤ ከባሞትም ምድረ በዳውን ከላይ ወደሚመለከተው ወደ ፈስጋ ተራራ ራስ በሞዓብ በረሀ ወዳለው ሸለቆ ተጓዙ።
21፤
22፤ እስራኤልም። በምድርህ ላይ እንለፍ፤ ወደ እርሻና ወደ ወይን ቦታ አንገባም፤ ከጕድጓድም ውኃን አንጠጣም፤ ከምድርህ ዳርቻ እስክንወጣ ድረስ በንጉሥ ጐዳና እንሄዳለን ብለው ወደ አሞራውያን ንጉሥ ወደ ሴዎን መልእክተኞችን ላኩ።
23፤ ሴዎንም እስራኤል በምድሩ ላይ ያልፍ ዘንድ እንቢ አለ፤ ሴዎንም ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰበ፥ እስራኤልንም ለመውጋት ወደ ምድረ በዳ ወጣ፥ ወደ ያሀጽም መጣ፥ ከእስራኤልም ጋር ተዋጋ።
24፤ እስራኤልም በሰይፍ መታው፥ ምድሩንም ከአርኖን ጀምሮ እስከ አሞን ልጆች እስከ ያቦቅ ድረስ ወረሰ፤ የአሞንም ልጆች ዳርቻ የጸና ነበረ።
25፤ እስራኤልም እነዚህን ከተሞች ሁሉ ወሰደ፤ እስራኤልም በአሞራውያን ከተሞች ሁሉ በሐሴቦንና በመንደሮቹ ሁሉ ተቀመጠ።
26፤ ሐሴቦንም የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን ከተማ ነበረ፤ እርሱም የፊተኛውን የሞዓብን ንጉሥ ወግቶ እስከ አርኖን ድረስ ምድሩን ሁሉ ከእጁ ወስዶ ነበር።
27፤ ስለዚህ በምሳሌ እንዲህ ተብሎ ተነገረ። ወደ ሐሴቦን ኑ፤ የሴዎን ከተማ ይሠራ፥ ይመሥረት፤
28፤ እሳት ከሐሴቦን፥ ነበልባልም ከሴዎን ከተማ ወጣ፤ የሞዓብን ዔር፥ የአርኖንን ተራራ አለቆች በላ፤
29፤ ሞዓብ ሆይ፥ ወዮልህ! የከሞስ ሕዝብ ሆይ፥ ጠፋህ፤ ወንዶች ልጆቹን ለሽሽት፥ ሴቶች ልጆቹንም ለምርኮ፥ ለአሞራውያን ንጉሥ ለሴዎን ሰጠ።
30፤ ገተርናቸው፤ ከሐሴቦን እስከ ዴቦን ድረስ ጠፉ፤ ኖፋም እስኪደርሱ እስከ ሜድባ አፈረስናቸው።
31፤ እስራኤልም እንደዚህ በአሞራውያን ምድር ተቀመጡ።
32፤ ሙሴም ሰላዮችን ወደ ኢያዜር ሰደደ፤ መንደሮችዋንም ወሰዱ፥ በዚያም የነበሩትን አሞራውያን አባረሩ።
33፤ ተመልሰውም በበሳን መንገድ ወጡ፤ የባሳንም ንጉሥ ዐግ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር በኤድራይ ይወጋቸው ዘንድ ወጣ።
34፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። እርሱንና ሕዝቡን ሁሉ ምድሪቱንም አሳልፌ በእጅህ ሰጥቼአለሁና አትፍራው፤ በሐሴቦንም በተቀመጠው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን እንዳደረግህ እንዲሁ ታደርግበታለህ አለው።
35፤ እርሱንና ልጆቹን ሕዝቡንም ሁሉ መቱ ሰውም አልቀረለትም፤ ምድሩንም ወረሱ።
ምዕራፍ 22
1፤ የእስራኤልም ልጆች ተጓዙ፥ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በዮርዳኖስ ማዶ ባለው በሞዓብ ሜዳ ሰፈሩ።
2፤ የሴፎር ልጅ ባላቅ እስራኤል በአሞራውያን ላይ ያደረገውን ሁሉ አየ።
3፤ ብዙም ነበረና ሞዓብ ከሕዝቡ እጅግ ፈራ፤ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ ሞዓብ ደነገጠ።
4፤ ሞዓብም የምድያምን ሽማግሌዎች። በሬ የለመለመውን ሣር እንደሚጨርስ ይህ ጭፍራ በዙሪያችን ያለውን ሁሉ ይጨርሳል አላቸው። በዚያን ጊዜም የሴፎር ልጅ ባላቅ የሞዓብ ንጉሥ ነበረ።
5፤
6፤ በወንዙ አጠገብ ባለችው በሕዝቡ ልጆች ምድር በፋቱራ ወደ ተቀመጠው ወደ ቢዖር ልጅ ወደ በለዓም። እነሆ፥ ከግብፅ የወጣ ሕዝብ አለ፤ እነሆም፥ የምድሩን ሁሉ ፊት ሸፈነ፥ በአቅራቢያችንም ተቀምጦአል፤ አሁንም ይህ ሕዝብ ከእኔ ይበልጣልና ልወጋቸውና ከምድሪቱ ላሳድዳቸው እችል እንደ ሆነ፥ እባክህ፥ ና ርገምልኝ፤ አንተ የመረቅኸው ምሩቅ የረገምኸውም ርጉም እንደ ሆነ አውቃለሁና ብሎ ይጠሩት ዘንድ መልእክተኞቹን ላከ።
7፤ የሞዓብ ሽማግሌዎችና የምድያም ሽማግሌዎችም የምዋርቱን ዋጋ በእጃቸው ይዘው ሄዱ፤ ወደ በለዓምም መጡ፥ የባላቅንም ቃል ነገሩት።
8፤ እርሱም። ዛሬ ሌሊት በዚህ እደሩ፥ እግዚአብሔርም እንደሚነግረኝ እመልስላችኋለሁ አላቸው፤ የሞዓብም አለቆች በበለዓም ዘንድ ተቀመጡ።
9፤ እግዚአብሔርም ወደ በለዓም መጥቶ። እነዚህ በአንተ ዘንድ ያሉ ሰዎች እነማን ናቸው? አለው።
10፤
11፤ በለዓምም እግዚአብሔርን። የሞዓብ ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ። እነሆ፥ ከግብፅ የወጣ ሕዝብ የምድርን ፊት ሸፈነ፥ አሁንም ና እርሱንም ርገምልኝ፤ ምናልባት እወጋው አሳድደውም ዘንድ እችል እንደ ሆነ ብሎ ወደ እኔ ልኮአል አለው።
12፤ እግዚአብሔርም በለዓምን። ከእነርሱ ጋር አትሂድ፤ የተባረከ ነውና ሕዝቡን አትረግምም አለው።
13፤ በለዓምም ሲነጋ ተነሥቶ የባላቅን አለቆች። ከእናንተ ጋር እሄድ ዘንድ እግዚአብሔር አልፈቀደምና ወደ ምድራችሁ ሂዱ አላቸው።
14፤ የሞዓብ አለቆች ተነሡ፥ ወደ ባላቅም መጥተው። በለዓም ከእኛ ጋር ይመጣ ዘንድ አልፈቀደም አሉት።
15፤ ባላቅም ደግሞ ከፊተኞች የበዙና የከበሩ ሌሎችን አለቆች ሰደደ።
16፤
17፤ ወደ በለዓምም መጥተው። የሴፎር ልጅ ባላቅ። ክብርህን እጅግ ታላቅ አደርገዋለሁና፥ የተናገርኸውንም ሁሉ አደርግልሃለሁና እባክህ፥ ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ ምንም አይከልክልህ፤ እባክህ፥ ና፥ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ አለ ብለው ነገሩት።
18፤ በለዓምም መልሶ የባላቅን ባሪያዎች። ባላቅ በቤቱ የሞላውን ወርቅና ብር ቢሰጠኝ፥ በትንሹ ወይም በትልቁ ቢሆን የአምላኬን የእግዚአብሔርን ቃል እተላለፍ ዘንድ አይቻለኝም፤
19፤ አሁንም እግዚአብሔር ደግሞ የሚነግረኝን አውቅ ዘንድ፥ እባካችሁ፥ ዛሬ ሌሊት ደግሞ በዚህ እደሩ አላቸው።
20፤ እግዚአብሔርም ወደ በለዓም በሌሊት መጥቶ። ሰዎቹ ይጠሩህ ዘንድ መጥተው እንደ ሆነ፥ ተነሣ ከእነርሱም ጋር ሂድ፤ ነገር ግን የምነግርህን ቃል ብቻ ታደርጋለህ አለው።
21፤ በለዓምም ሲነጋ ተነሣ፥ አህያይቱንም ጭኖ ከሞዓብ አለቆች ጋር ሄደ።
22፤ እርሱም ስለ ሄደ እግዚአብሔር ተቈጣ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ሊቋቋመው በመንገድ ላይ ቆመ። እርሱም በአህያይቱ ላይ፥ ሁለቱም ሎሌዎቹ ከእርሱ ጋር ነበሩ።
23፤ አህያይቱም የእግዚአብሔርን መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየች፤ ከመንገዱም ፈቀቅ ብላ ወደ እርሻው ውስጥ ገባች፤ በለዓምም ወደ መንገድ ይመልሳት ዘንድ አህያይቱን መታት።
24፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ከወይኑ ቦታዎች መካከል በወዲያና በወዲህ ወገን ግንብ በነበረበት በጠባብ መንገድ ላይ ቆመ።
25፤ አህያይቱም የእግዚአብሔርን መልአክ አይታ ወደ ቅጥሩ ተጠጋች፥ የበለዓምንም እግር ከቅጥሩ ጋር አጣበቀች፤ እርሱም ደግሞ መታት።
26፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ወደ ፊት ሄደ፥ በቀኝና በግራ መተላለፊያ በሌለበት በጠባብ ስፍራ ቆመ።
27፤ አህያይቱም የእግዚአብሔርን መልአክ አየች፥ ከበለዓምም በታች ተኛች፤ በለዓምም እጅግ ተቈጣ፥ አህያይቱንም በበትሩ ደበደባት።
28፤ እግዚአብሔርም የአህያይቱን አፍ ከፈተ፥ በለዓምንም። ሦስት ጊዜ የመታኸኝ ምን አድርጌብህ ነው? አለችው።
29፤ በለዓምም አህያይቱን። ስላላገጥሽብኝ ነው፤ በእጄስ ሰይፍ ቢኖር አሁን በገደልሁሽ ነበር አላት።
30፤ አህያይቱም በለዓምን። ከብዙ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የምትቀመጥብኝ አህያህ አይደለሁምን? በውኑ እንዲህ አደርግ ዘንድ ልማዴ ነበረን? አለችው። እርሱም። እንዲህ አላደረግሽብኝም አላት።
31፤ እግዚአብሔርም የበለዓምን ዓይኖች ከፈተ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየ፤ ሰገደም፥ በግምባሩም ወደቀ።
32፤ የእግዚአብሔርም መልአክ። አህያህን ሦስት ጊዜ ለምን መታህ? እነሆ፥ መንገድህ በፊቴ ጠማማ ነውና እቋቋምህ ዘንድ ወጥቼአለሁ፤
33፤ አህያይቱም አይታኝ ከፊቴ ሦስት ጊዜ ፈቀቅ አለች፤ ከፊቴስ ፈቀቅ ባላለች በእውነት አሁን አንተን በገደልሁህ፥ እርስዋንም ባዳንኋት ነበር አለው።
34፤ በለዓምም የእግዚአብሔርን መልአክ። በድያለሁ፤ አንተ በመንገድ ላይ በፊቴ እንደቆምህብኝ አላወቅሁም፤ እንግዲህም አሁን አትወድድ እንደ ሆነ እመለሳለሁ አለው።
35፤ የእግዚአብሔርም መልአክ በለዓምን። ከሰዎቹ ጋር ሂድ፥ ነገር ግን የምናገርህን ቃል ብቻ ትናገራለህ አለው። በለዓምም ከባላቅ አለቆች ጋር ሄደ።
36፤ ባላቅም በለዓም እንደ መጣ በሰማ ጊዜ በአርኖን ዳር ዳርቻ በመጨረሻ ወዳለችው ወደ ሞዓብ ከተማ ሊገናኘው ወጣ።
37፤ ባላቅም በለዓምን። በውኑ አንተን ለመጥራት አልላክሁብህምን? ለምንስ ወደ እኔ አልመጣህም? በውኑ አንተን ለማክበር እኔ አልችልምን? አለው።
38፤ በለዓምም ባላቅን። እነሆ፥ ወደ አንተ መጥቼአለሁ፤ በውኑ አሁን አንዳችን ነገር እናገር ዘንድ እችላለሁን? እግዚአብሔር በአፌ የሚያደርገውን ቃል እርሱን እናገራለሁ አለው።
39፤ በለዓምም ከባላቅ ጋር ሄደ፥ ወደ ቂርያት ሐጾትም መጡ።
40፤ ባላቅም በሬዎችንና በጎችን አርዶ ወደ በለዓም ከእርሱም ጋር ወዳሉት አለቆች ላከ።
41፤ በነጋውም ባላቅ በለዓምን ይዞ ወደ በኣል ኮረብታ መስገጃ አወጣው፤ በዚያም ሆኖ የሕዝቡን ዳርቻ አየ።