ምዕራፍ 1

1፤ እንዲህም ሆነ፤ ኢያሱ ከሞተ በኋላ የእስራኤል ልጆች። ከነዓናውያንን ለመውጋት ማን በፊት ይወጣልናል? ብለው እግዚአብሔርን ጠየቁ።
2፤ እግዚአብሔርም። ይሁዳ ይውጣ፤ እነሆ፥ ምድሪቱን በእጁ አሳልፌ ሰጥቻለሁ አለ።
3፤ ይሁዳም ወንድሙን ስምዖንን። ከነዓናውያንን እንወጋ ዘንድ ከእኔ ጋር ወደ ዕጣዬ ውጣ፥ እኔም ደግሞ ከአንተ ጋር ወደ ዕጣህ እሄዳለሁ አለው። ስምዖንም ከእርሱ ጋር ሄደ።
4፤ ይሁዳም ወጣ፤ እግዚአብሔርም ከነዓናውያንንና ፌርዛውያንን በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው፥ ከእነርሱም በቤዜቅ ውስጥ አሥር ሺህ ሰዎች ገደሉ።
5፤ አዶኒቤዜቅንም በቤዜቅ አገኙትና ተዋጉት፤ ከነዓናውያንንና ፌርዛውያንንም መቱአቸው።
6፤ አዶኒቤዜቅም ሸሸ፤ አሳድደውም ያዙት፥ የእጁንና የእግሩንም አውራ ጣት ቈረጡ።
7፤ አዶኒቤዜቅም። የእጃቸውና የእግራቸው አውራ ጣት የተቈረጡ ሰባ ነገሥታት ከገበታዬ በታች ፍርፋሪ ይለቅሙ ነበር፤ እኔ እንዳደረግሁ እግዚአብሔር እንዲሁ መለሰልኝ አለ። ወደ ኢየሩሳሌምም አመጡት፥ በዚያም ሞተ።
8፤ የይሁዳም ልጆች ኢየሩሳሌምን ተዋግተው ያዙአት፥ በሰይፍ ስለትም መቱአት፥ ከተማይቱንም በእሳት አቃጠሉአት።
9፤ ከዚያም በኋላ የይሁዳ ልጆች በተራራማው አገርና በደቡቡ በኩል በቈላውም ውስጥ የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ሊወጉ ወረዱ።
10፤ ይሁዳም በኬብሮን የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ሊወጋ ሄደ። የኬብሮንም ስም አስቀድሞ ቂርያትአርባቅ ነበረ። ሴሲንና አኪመንን ተላሚንም ገደሉ።
11፤ ከዚያም የዳቤርን ሰዎች ሊወጋ ሄደ፤ አስቀድሞም የዳቤር ስም ቅርያትሤፍር ነበረ።
12፤ ካሌብም። ቅርያትሤፍርን ለሚመታና ለሚይዝ ልጄን ዓክሳን አጋባዋለሁ አለ።
13፤ የካሌብም ትንሽ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል ያዛት፤ ልጁንም ዓክሳን አጋባው።
14፤ እርስዋም ወደ እርሱ በመጣች ጊዜ ከአባትዋ እርሻ እንዲለምን መከረችው። እርስዋም ከአህያዋ ወረደች፤ ካሌብም። ምን ፈለግሽ? አላት።
15፤ እርስዋም። በረከትን ስጠኝ፤ በደቡብ በኩል ያለውን ምድር ሰጥተኸኛልና የውኃ ምንጭ ደግሞ ስጠኝ አለችው። ካሌብም ላይኛውንና ታችኛውን ምንጭ ሰጣት።
16፤ የቄናዊው የሙሴ አማት ልጆችም ከይሁዳ ልጆች ጋር ዘንባባ ካለባት ከተማ ተነሥተው ከዓራድ በደቡብ በኩል ወዳለው ወደ ይሁዳ ምድረ በዳ ወጡ፤ ሄደውም ከሕዝቡ ጋር ተቀመጡ።
17፤ ይሁዳም ከወንድሙ ከስምዖን ጋር ሄደ፥ በጽፋት የተቀመጡትንም ከነዓናውያንን መቱ፥ ፈጽመውም አጠፉአት። የከተማይቱንም ስም ሔርማ ብለው ጠሩአት።
18፤ ይሁዳም ጋዛንና ዳርቻዋን፥ አስቀሎናንና ዳርቻዋን፥ አቃሮንንና ዳርቻዋን ያዘ።
19፤ እግዚአብሔርም ከይሁዳ ጋር ነበረ፤ ይሁዳም ተራራማውን አገር ወረሰ፤ በሸለቆው የሚኖሩት ግን የብረት ሰረገሎች ነበሩአቸውና ሊያወጣቸው አልቻለም።
20፤ ሙሴም እንደ ተናገረ ለካሌብ ኬብሮንን ሰጡት፤ ከዚያም ሦስቱን የዔናቅ ልጆች አወጣ።
21፤ ነገር ግን በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያንን የብንያም ልጆች አላወጡአቸውም፤ ኢያቡሳውያንም ከብንያም ልጆች ጋር እስከ ዛሬ ድረስ በኢየሩሳሌም ተቀምጠዋል።
22፤ የዮሴፍም ወገን ደግሞ በቤቴል ላይ ወጡ፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ነበረ።
23፤ የዮሴፍም ወገን ቤቴልን የሚሰልሉ ላኩ። አስቀድሞም የከተማይቱ ስም ሎዛ ይባል ነበር።
24፤ ጠባቂዎቹም አንድ ሰው ከከተማ ሲወጣ አይተው። የከተማይቱን መግቢያ አሳየን፥ እኛም ቸርነት እናደርግልሃለን አሉት።
25፤ የከተማይቱንም መግቢያ አሳያቸው፥ ከተማይቱንም በሰይፍ ስለት መቱ፤ ያንን ሰውና ወገኖቹን ግን ለቀቁአቸው።
26፤ ሰውየውም ወደ ኬጢያውያን ምድር ሄደ፥ በዚያም ከተማን ሠራ፥ ስምዋንም ሎዛ ብሎ ጠራት። እስከ ዛሬም ድረስ ስምዋ ይህ ነው።
27፤ ምናሴም የቤትሳንንና የመንደሮችዋን፥ የታዕናክንና የመንደሮችዋን፥ የዶርንና የመንደሮችዋን፥ የይብለዓምንና የመንደሮችዋን፥ የመጊዶንና የመንደሮችዋን ሰዎች አላወጣቸውም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በዚያ አገር በመቀመጥ ጸኑ።
28፤ እስራኤልም በበረቱ ጊዜ ከነዓናውያንን አስገበሩአቸው፥ ፈጽመውም አላወጡአቸውም።
29፤ ኤፍሬምም በጌዝር የተቀመጡትን ከነዓናውያንን አላወጣቸውም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በመካከላቸው በጌዝር ተቀመጡ።
30፤ ዛብሎንም የቂድሮንንና የነህሎልን ሰዎች አላወጣቸውም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በመካከላቸው ተቀመጡ፥ ግብርም የሚገብሩለት ሆኑ።
31፤ አሴርም የዓኮንና የሲዶንን የአሕላብንም የአክዚብንም የሒልባንም የአፌቅንም የረአብንም ሰዎች አላወጣቸውም።
32፤ በዚያችም ምድር የተቀመጡትን ከነዓናውያን አላወጡአቸውምና በመካከላቸው የአሴር ልጆች ተቀመጡ።
33፤ ንፍታሌምም የቤትሳሚስንና የቤትዓናትን ሰዎች አላወጣቸውም፥ በምድሩም በተቀመጡት በከነዓናውያን መካከል ተቀመጡ፤ ነገር ግን የቤትሳሚስና የቤትዓናት ሰዎች ግብር የሚገብሩለት ሆኑ።
34፤ አሞራውያንም የዳንን ልጆች ወደ ተራራማው አገር እንዲያፈገፍጉ አስገደዱአቸው፥ ወደ ሸለቆውም እንዳይወርዱ ከለከሉአቸው።
35፤ አሞራውያን በሔሬስ ተራራና በኤሎን በሸዓልቢምም በመቀመጥ ጸኑ፤ ነገር ግን የዮሴፍ ቤት እጅ ከበደች፥ አስገበረቻቸውም።
36፤ የአሞራውያንም ድንበር ከአቅረቢም ዐቀበት ከጭንጫው ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ ነበረ።
ምዕራፍ 2

1፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ከጌልገላ ወደ ቦኪም ወጥቶ እንዲህ አለ። እኔ ከግብፅ አውጥቻችኋለሁ፥ ለአባቶቻችሁም ወደ ማልሁላቸው ምድር አግብቻችኋለሁ፤ እኔም። ከእናንተ ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን ለዘላለም አላፈርስም፤
2፤ እናንተም መሠዊያቸውን አፍርሱ እንጂ በዚህች ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን አታድርጉ አልሁ። እናንተ ግን ቃሌን አልሰማችሁም፤
3፤ ይህንስ ለምን አደረጋችሁ? ስለዚህም። ከፊታችሁ አላወጣቸውም፥ ነገር ግን ያስጨንቋችኋል፥ አማልክቶቻቸውም ወጥመድ ይሆኑባችኋል አልሁ።
4፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ይህን ቃል ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በተናገረ ጊዜ ሕዝቡ ድምፃቸውን አንሥተው አለቀሱ።
5፤ የዚያንም ስፍራ ስም ቦኪም ብለው ጠሩት፤ በዚያም ለእግዚአብሔር ሠዉ።
6፤ ኢያሱም ሕዝቡን ባሰናበተ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ምድሪቱን ሊወርሱ ወደ እየርስታቸው ሄዱ።
7፤ ኢያሱም በነበረበት ዘመን ሁሉ፥ ለእስራኤልም ያደረገውን ታላቁን የእግዚአብሔርን ሥራ ሁሉ ባዩት፥ ከኢያሱ በኋላ በነበሩ ሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ፥ ሕዝቡ እግዚአብሔርን አመለኩ።
8፤ የእግዚአብሔርም ባሪያ የነዌ ልጅ ኢያሱ ዕድሜው መቶ አሥር ዓመት ሲሆነው ሞተ።
9፤ በተራራማውም በኤፍሬም አገር በገዓስ ተራራ በሰሜን ባለችው በርስቱ ዳርቻ በተምናሔሬስ ቀበሩት።
10፤ ትውልድ ሁሉ ደግሞ ወደ አባቶቻቸው ተከማቹ፤ ከእነዚያም በኋላ እግዚአብሔርን ለእስራኤልም ያደረገውን ሥራ ያላወቀ ሌላ ትውልድ ተነሣ።
11፤ የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነ ነገር አደረጉ፥ በኣሊምንም አመለኩ።
12፤ ከግብፅ ምድርም ያወጣቸውን የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ተዉ፥ በዙሪያቸውም ካሉት ከአሕዛብ አማልክት ሌሎችን አማልክት ተከተሉ፥ ሰገዱላቸውም፤ እግዚአብሔርንም አስቈጡ።
13፤ እግዚአብሔርንም ትተው በኣልንና አስታሮትን አመለኩ።
14፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ ወደ ማረኩአቸውም ማራኪዎች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ በዙሪያቸውም ባሉት በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ ጠላቶቻቸውንም ከዚያ ወዲያ ሊቋቋሙ አልቻሉም።
15፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ፥ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ እንደማለ፥ ወደ ወጡበት ሁሉ የእግዚአብሔር እጅ ትከፋባቸው ነበረች፤ እጅግም ተጨነቁ።
16፤ እግዚአብሔርም መሳፍንትን አስነሣላቸው፥ ከሚማርኩአቸውም እጅ አዳኑአቸው።
17፤ ሌሎች አማልክትን ተከትለው አመነዘሩ ሰገዱላቸውም እንጂ መሳፍንቶቻቸውን አልሰሙም፤ አባቶቻቸውም ይሄዱበት ከነበረ መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ፤ አባቶቻቸው ለእግዚአብሔር ትእዛዝ እንደ ታዘዙ እንዲሁ አላደረጉም።
18፤ እግዚአብሔርም መሳፍንትን ባስነሣላቸው ጊዜ እግዚአብሔር ከመስፍኑ ጋር ነበረ፤ እግዚአብሔርም ስለሚጋፉአቸውና ስለሚያስጨንቋቸው በጩኸታቸው ያዝን ነበርና በመስፍኑ ዘመን ሁሉ ከጠላቶቻቸው እጅ አዳናቸው።
19፤ መስፍኑ ግን ከሞተ በኋላ ይመለሱ ነበር፥ ሌሎችንም አማልክት በመከተላቸው እነርሱንም በማምለካቸውና ለእነርሱ በመስገዳቸው አባቶቻቸው አድርገውት ከነበረው የከፋ ያደርጉ ነበር፤ የእልከኝነታቸውን መንገድና ሥራቸውን አልተዉም ነበር።
20፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ እንዲህም አለ። ይህ ሕዝብ ለአባቶቻቸው ያዘዝሁትን ቃል ኪዳን ስለ ተላለፉ፥ ድምፄንም ስላልሰሙ አባቶቻቸውም እንደ ጠበቁ፥
21
22፤ ይሄዱባት ዘንድ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ወይም አይጠብቁ እንደ ሆነ እስራኤልን እፈትንባቸው ዘንድ፥ ኢያሱ በሞተ ጊዜ ከተዋቸው አሕዛብ አንዱን ሰው እንኳ ከእንግዲህ ወዲህ ከፊታቸው አላወጣም።
23፤ እግዚአብሔርም እነዚህን አሕዛብ አስቀረ፥ ፈጥኖም አላወጣቸውም፥ በኢያሱም እጅ አሳልፎ አልሰጣቸውም።
ምዕራፍ 3

1
2፤ ከከነዓናውያንም ጋር መዋጋት ያላወቁትን እስራኤልን በእነርሱ ይፈትናቸው ዘንድ፥ በፊትም ሰልፍን ያልለመዱ የእስራኤል ልጆች ትውልድ መዋጋትን ያውቁና ይማሩ ዘንድ እግዚአብሔር ያስቀራቸው አሕዛብ እነዚህ ናቸው፤
3፤ አምስቱ የፍልስጥኤማውያን መኳንንት፥ ከነዓናውያንም ሁሉ፥ ሲዶናውያንም፥ ከበኣልአርሞንዔም ተራራ ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ በሊባኖስ ተራራ የሚኖሩትም ኤዊያውያን።
4፤ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ ለአባቶቻቸው ያዘዘውን ትእዛዝ መስማታቸው እንዲታወቅ እስራኤል ይፈተኑባቸው ዘንድ እነዚህ ቀሩ።
5፤ የእስራኤልም ልጆች በከነዓናውያን በኬጢያውያንም በአሞራውያንም በፌርዛውያንም በኤዊያውያንም በኢያቡሳውያንም መካከል ተቀመጡ።
6፤ ሴት ልጆቻቸውንም አገቡአቸው፥ እነርሱም ሴቶች ልጆቻቸውን ለወንዶች ልጆቻቸው ሰጡ፥ አማልክቶቻቸውንም አመለኩ።
7፤ የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር አደረጉ፥ አምላካቸውንም እግዚአብሔርን ረስተው በኣሊምንና አስታሮትን አመለኩ።
8፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ በመስጴጦምያ ንጉሥ በኵሰርሰቴም እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ የእስራኤልም ልጆች ለኵሰርሰቴም ስምንት ዓመት ተገዙለት።
9፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔርም የሚያድናቸውን አዳኝ የካሌብን የታናሽ ወንድሙን የቄኔዝን ልጅ ጎቶንያልን አስነሣላቸው።
10፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ መጣ፥ በእስራኤልም ላይ ይፈርድ ነበር፤ ለሰልፍ ወጣ፥ እግዚአብሔርም የመስጴጦምያን ንጉሥ ኵሰርሰቴምን በእጁ አሳልፎ ሰጠው፤ እጁም በኵሰርሰቴም ላይ አሸነፈች።
11፤ ምድሪቱም አርባ ዓመት ዐረፈች፤ የቄኔዝም ልጅ ጎቶንያል ሞተ።
12፤ የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ስለ ሠሩ እግዚአብሔር የሞዓብን ንጉሥ ዔግሎምን በእስራኤል ላይ አበረታባቸው።
13፤ የአሞንን ልጆችና አማሌቅን ወደ እርሱ ሰበሰበ፤ ሄዶም እስራኤልን መታ፥ ዘንባባም ያለባትን ከተማ ያዙአት።
14፤ የእስራኤልም ልጆች ለሞዓብ ንጉሥ ለዔግሎም አሥራ ስምንት ዓመት ተገዙለት።
15፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔርም ብንያማዊውን የጌራን ልጅ ናዖድን ግራኙን ሰው አዳኝ አስነሣላቸው፤ የእስራኤልም ልጆች በእርሱ እጅ ወደ ሞዓብ ንጉሥ ወደ ዔግሎም ግብር ላኩ።
16፤ ናዖድም ሁለት አፍ ያለው ርዝመቱ አንድ ክንድ የሆነ ሰይፍ አበጀ፥ ከልብሱም በታች በቀኝ ጭኑ በኩል አደረገው።
17፤ ለሞዓብም ንጉሥ ለዔግሎም ግብሩን አቀረበ፤ ዔግሎምም እጅግ ወፍራም ሰው ነበረ።
18፤ ግብሩንም ማቅረብ በጨረሰ ጊዜ፥ ግብር የተሸከሙትን ሰዎች ሰደደ።
19፤ ናዖድ ግን በጌልገላ ከነበሩት ትክል ድንጋዮች ዘንድ ተመልሶ። ንጉሥ ሆይ፥ የምሥጢር ነገር አለኝ አለ፤ ንጉሡም። ዝም በል አለ፤ በዙሪያውም የቆሙት ሁሉ ወጡ።
20፤ ናዖድም ወደ እርሱ ቀረበ፤ እርሱም በሰገነት ቤት ለብቻው ተቀምጦ ነበር። ናዖድም። የእግዚአብሔር መልእክት ለአንተ አለኝ አለ። ከዙፋኑም ተነሣ።
21፤ ናዖድም ግራ እጁን ዘርግቶ ከቀኝ ጭኑ ሰይፉን ወሰደ፥ ሆዱንም ወጋው፤
22፤ የሰይፉም እጀታው ደግሞ ከስለቱ በኋላ ገባ፤ ስቡም ስለቱን ከደነው፥ ሰይፉንም ከሆዱ መልሶ አላወጣውም፤ በኋላውም ወጣ።
23፤ ናዖድም ወደ ደርቡ ወጣ፥ የሰገነቱንም ደጅ ዘግቶ ቈለፈው።
24፤ ናዖድም ከሄደ በኋላ ባሪያዎቹ መጡ፤ የሰገነቱም ደጅ ተቈልፎ ባዩ ጊዜ። ምናልባት በሰገነቱ ውስጥ ወገቡን ይሞክር ይሆናል አሉ።
25፤ እስኪያፍሩም ድረስ እጅግ ዘገዩ፤ የሰገነቱንም ደጅ እንዳልከፈተ ባዩ ጊዜ መክፈቻውን ወስደው ከፈቱ፥ እነሆም፥ ጌታቸው በምድር ወድቆ ሞቶም አገኙት።
26፤ በዘገዩበትም ጊዜያት ናዖድ ሸሸ፥ ትክል ድንጋዮቹንም አለፈ፥ ወደ ቤይሮታም አመለጠ።
27፤ በመጣም ጊዜ በተራራማው በኤፍሬም አገር ቀንደ መለከት ነፋ፤ የእስራኤልም ልጆች ከእርሱ ጋር ከተራራማው አገር ወረዱ፥ እርሱም በፊታቸው ሄደ።
28፤ እርሱም። እግዚአብሔር ጠላቶቻችሁን ሞዓባውያንን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአልና ተከተሉኝ አላቸው። ተከትለውትም ወረዱ፥ ወደ ሞዓብም የሚያሻግረውን የዮርዳኖስን መሻገርያ ያዙ፥ ማንንም አላሳለፉም።
29፤ የዚያን ጊዜም ከሞዓብ አሥር ሺህ የሚያህሉትን፥ ጕልማሶችና ጽኑዓን ሁሉ፥ መቱ፤ አንድ እንኳ አላመለጠም።
30፤ በዚያም ቀን ሞዓብ ከእስራኤል እጅ በታች ተዋረደ፤ ምድሪቱም ሰማንያ ዓመት ዐረፈች።
31፤ ከእርሱም በኋላ የዓናት ልጅ ሰሜጋር ተነሣ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ስድስት መቶ ሰው በበሬ መውጊያ ገደለ፤ እርሱም ደግሞ እስራኤልን አዳነ።
ምዕራፍ 4

1፤ ናዖድም ከሞተ በኋላ የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ።
2፤ እግዚአብሔርም በአሶር በነገሠው በከነዓን ንጉሥ በኢያቢስ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ የሠራዊቱም አለቃ በአሕዛብ አሪሶት የተቀመጠው ሲሣራ ነበረ።
3፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ ዘጠኝ መቶ የብረት ሰረገሎች ነበሩትና፥ የእስራኤልንም ልጆች ሀያ ዓመት ያህል እጅግ ያስጨንቃቸው ነበር።
4፤ በዚያ ጊዜም ነቢይቱ የለፊዶት ሚስት ዲቦራ በእስራኤል ላይ ትፈርድ ነበረች።
5፤ እርስዋም በተራራማው በኤፍሬም አገር በራማና በቤቴል መካከል ካለው የዲቦራ ዛፍ ከሚባለው ከዘንባባው በታች ተቀምጣ ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እርስዋ ለፍርድ ይወጡ ነበር።
6፤ ልካም ከቃዴስ ንፍታሌም የአቢኒኤምን ልጅ ባርቅን ጠርታ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር። ሄደህ ወደ ታቦር ተራራ ውጣ፥ ከአንተም ጋር ከንፍታሌምና ከዛብሎን ልጆች አሥር ሺህ ሰዎች ውሰድ፤
7፤ እኔም የኢያቢስን ሠራዊት አለቃ ሲሣራን ሰረገሎቹንም ሕዝቡንም ሁሉ ወደ አንተ ወደ ቂሶን ወንዝ እስባለሁ፥ በእጅህም አሳልፌ እሰጠዋለሁ ብሎ አላዘዘህምን? አለችው።
8፤ ባርቅም። አንቺ ከእኔ ጋር ብትሄጂ እኔ እሄዳለሁ፤ አንቺ ግን ከእኔ ጋር ባትሄጂ እኔ አልሄድም አላት።
9፤ እርሷም። በእውነት ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሲሣራን በሴት እጅ አሳልፎ ይሰጣልና በዚህ በምትሄድበት መንገድ ለአንተ ክብር አይሆንም አለችው። ዲቦራም ተነሥታ ከባርቅ ጋር ወደ ቃዴስ ሄደች።
10፤ ባርቅም ዛብሎንንና ንፍታሌምን ወደ ቃዴስ ጠራቸው፥ አሥር ሺህም ሰዎች ተከትለውት ወጡ፤ ዲቦራም ከእርሱ ጋር ወጣች።
11፤ ቄናዊውም ሔቤር ከሙሴ አማት ከኦባብ ልጆች ከቄናውያን ተለይቶ ድንኳኑን በቃዴስ አጠገብ በጻዕናይም እስከ ነበረው እስከ ትልቁ ዛፍ ድረስ ተከለ።
12፤ የአቢኒኤምም ልጅ ባርቅ ወደ ታቦር ተራራ እንደ ወጣ ለሲሣራ ነገሩት።
13፤ ሲሣራም ሰረገሎቹን ሁሉ፥ ዘጠኝ መቶ የብረት ሰረገሎች፥ ከእርሱም ጋር የነበሩትን ሕዝቡን ሁሉ ከአሪሶት ወደ ቂሶን ወንዝ ሰበሰባቸው።
14፤ ዲቦራም ባርቅን። እግዚአብሔር ሲሣራን በእጅህ አሳልፎ የሚሰጥበት ቀን ዛሬ ነውና ተነሣ፤ እነሆ፥ እግዚአብሔር በፊትህ ወጥቶአል አለችው። ባርቅም አሥር ሺህ ሰዎች ተከትለውት ከታቦር ተራራ ወረደ።
15፤ እግዚአብሔርም ሲሣራን ሰረገሎቹንም ሁሉ ሠራዊቱንም ሁሉ ከባርቅ ፊት በሰይፍ ስለት አስደነገጣቸው፤ ሲሣራም ከሰረገላው ወርዶ በእግሩ ሸሸ።
16፤ ባርቅም ሰረገሎችንና ሠራዊቱን እስከ አሪሶት ድረስ አባረረ፤ የሲሣራም ሠራዊት ሁሉ በሰይፍ ስለት ወደቀ፤ አንድ እንኳ አልቀረም።
17፤ በአሶር ንጉሥም በኢያቢስና በቄናዊው በሔቤር ቤት መካከል ሰላም ነበረና ሲሣራ በእግሩ ሸሽቶ ወደ ቄናዊው ወደ ሔቤር ሚስት ወደ ኢያዔል ድንኳን ደረሰ።
18፤ ኢያዔልም ሲሣራን ለመገናኘት ወጥታ። ግባ፥ ጌታዬ ሆይ፥ ወደ እኔ ግባ፤ አትፍራ አለችው። ወደ እርስዋም ወደ ድንኳንዋ ገባ፥ በመጐናጸፊያዋም ሸፈነችው።
19፤ እርሱም። ጠምቶኛልና እባክሽ የምጠጣው ጥቂት ውኃ ስጭኝ አላት፤ እርስዋም የወተቱን አቁማዳ ፈትታ አጠጣችው፥ ሸፈነችውም።
20፤ እርሱም። ከድንኳኑ ደጃፍ ቁሚ፤ ሰውም መጥቶ። በዚህ ሰው አለን? ብሎ ቢጠይቅሽ አንቺ። የለም ትዪዋለሽ አላት።
21፤ የሔቤርም ሚስት ኢያዔል የድንኳን ካስማ ወሰደች፥ በእጅዋም መዶሻ ያዘች፥ ቀስ ብላም ወደ እርሱ ቀረበች፤ በጆሮግንዱ ካስማውን ቸነከረች፤ እርሱም ደክሞ እንቀላፍቶ ነበርና ካስማው ወደ መሬት ጠለቀ፥ እርሱም ሞተ።
22፤ እነሆም፥ ባርቅ ሲሣራን ሲያባርር ኢያዔል ልትገናኘው ወጥታ። ና የምትሻውንም ሰው አሳይሃለሁ አለችው። ወደ እርስዋም ገባ፥ እነሆም፥ ሲሣራን ወድቆ ሞቶም አገኘው፥ ካስማውም ከጆሮግንዱ ውስጥ ነበረ። v
23፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር የከነዓንን ንጉሥ ኢያቢስን በእስራኤል ልጆች ፊት አዋረደ።
24፤ የከነዓንን ንጉሥ ኢያቢስንም እስኪያጠፉ ድረስ በከነዓን ንጉሥ በኢያቢስ ላይ የእስራኤል ልጆች እጅ እየበረታች ሄደች።
ምዕራፍ 5

1፤ በዚያም ቀን ዲቦራና የአቢኒኤም ልጅ ባርቅ እንዲህ ብለው ተቀኙ።
2፤ በእስራኤል ውስጥ መሪዎች ስለ መሩ፥ ሕዝቡም ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ስለ ሰጡ፥ እግዚአብሔርን አመስግኑ።
3፤ ነገሥታት ሆይ፥ ስሙ፤ መኳንንት ሆይ፥ አድምጡ፤ እኔ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ።
4፤ አቤቱ፥ ከሴይር በወጣህ ጊዜ፥ ከኤዶምያስም ሜዳ በተራመድህ ጊዜ፥ ምድሪቱ ተናወጠች፥ ሰማያቱም አንጠበጠቡ፤ ደመናትም ደግሞ ውኃን አንጠበጠቡ።
5፤ ተራሮች ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ ቀለጡ፥ ያም ሲና ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ።
6፤ በዓናት ልጅ በሰሜጋር ዘመን፥ በኢያዔል ዘመን መንገዶች ተቋረጡ፤ መንገደኞች በስርጥ መንገድ ይሄዱ ነበር።
7፤ አንቺ፥ ዲቦራ፥ እስክትነሽ ድረስ፥ ለእስራኤልም እናት ሆነሽ እስክትነሽ ድረስ፥ ኃያላን በእስራኤል ዘንድ አነሱ፥ አለቁም።
8፤ አዲሶች አማልክትን መረጡ፤ በዚያ ጊዜ ሰልፍ በበሮች ሆነ፤ በአርባ ሺህ በእስራኤል ዘንድ ጦርና ጋሻ አልታየም።
9፤ ልቤ ወደ እስራኤል አለቆች ነው፥ በሕዝቡ መካከል ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ወደ ሰጡት፤ እግዚአብሔርን አመስግኑ።
10፤ በነጫጭ አህዮች ላይ የምትጫኑ፥ በወላንሳ ላይ የምትቀመጡ፥ በመንገድም የምትሄዱ፥ ተናገሩ።
11፤ በማጠጫው መካከል ካሉት ከቀስተኞች ጩኸት ርቀው፥ በዚያ የእግዚአብሔርን ጽድቅ፥ በእስራኤል ላይ የግዛቱን ጽድቅ ይጫወታሉ፤ ከዚያም በኋላ የእግዚአብሔር ሕዝብ ወደ በሮች ወረዱ።
12፤ ንቂ፥ ንቂ፥ ዲቦራ ሆይ፤ ንቂ፥ ንቂ፥ ቅኔውን ተቀኚ፤ ባርቅ ሆይ፥ ተነሣ፤ የአቢኒኤም ልጅ ሆይ፥ ምርኮህን ማርክ።
13፤ በዚያ ጊዜ የቀሩት ወደ ኃያላኑና ወደ ሕዝቡ ወረዱ፤ እግዚአብሔርም ስለ እኔ በኃያላን ላይ ወረደ።
14፤ በአማሌቅ ዘንድ ሥር የነበራቸው እነርሱ ከኤፍሬም፥ ብንያም ሆይ፥ በሕዝብህ መካከል ከአንተ በኋላ ወረዱ፤ አለቆች ከማኪር፥ የንጉሥንም ዘንግ የሚይዙ ከዛብሎን ወረዱ።
15፤ የይሳኮርም አለቆች ከዲቦራ ጋር ነበሩ፤ ይሳኮርም እንደ ባርቅ ነበረ፤ ከእግሩ በኋላ ወደ ሸለቆው ቸኰሉ፤ በሮቤል ፈሳሾች አጠገብ ብዙ የልብ ማመንታት ነበረ።
16፤ መንጎች ሲያፍዋጩ ለመስማት በበጎች ጕረኖ መካከል ለምን ተቀመጥህ? በሮቤል ፈሳሾች አጠገብ ታላቅ የልብ ምርምር ነበረ።
17፤ ገለዓድ በዮርዳኖስ ማዶ ተቀመጠ፤ ዳንም ለምን በመርከብ ውስጥ ቀረ? አሴርም በባሕሩ ዳር ተቀመጠ፥ በወንዞቹም ዳርቻ ዐረፈ።
18፤ ዛብሎን ነፍሱን ወደ ሞት ያሳለፈ ሕዝብ ነው፥ ንፍታሌምም በአገሩ ኮረብታ ላይ ነው።
19፤ ነገሥታት መጡ፥ ተዋጉም፤ በዚያ ጊዜ በመጊዶ ውኆች አጠገብ በታዕናክ የከነዓን ነገሥታት ተዋጉ፤ የብር ዘረፋም አልወሰዱም።
20፤ ከዋክብት ከሰማይ ተዋጉ፤ በአካሄዳቸውም ከሲሣራ ጋር ተዋጉ።
21፤ ከዱሮ ጀምሮ የታወቀ ያ የቂሶን ወንዝ፥ የቂሶን ወንዝ ጠርጎ ወሰዳቸው። ነፍሴ ሆይ፥ በኃይል እርገጪ።
22፤ ከኃያላን ግልቢያ ብርታት የተነሣ የፈረሶች ጥፍሮች ተቀጠቀጡ።
23፤ የእግዚአብሔር መልአክ። ሜሮዝን እርገሙ፤ እግዚአብሔርን በኃያላን መካከል ለመርዳት፥ እግዚአብሔርን ለመርዳት አልመጡምና የተቀመጡባትን ሰዎች ፈጽማችሁ እርገሙ አለ።
24፤ የቄናዊው የሔቤር ሚስት ኢያዔል ከሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን፤ በድንኳን ውስጥ ከሚኖሩ ሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን።
25፤ ውኃ ለመነ፥ ወተትም ሰጠችው፤ በተከበረ ዳካ እርጎ አቀረበችለት።
26፤ እጅዋን ወደ ካስማ፥ ቀኝ እጅዋንም ወደ ሠራተኛ መዶሻ አደረገች፤ በመዶሻውም ሲሣራን መታች፥ ራሱንም ቸነከረች፤ ጆሮግንዱንም በሳች፥ ጎዳችውም።
27፤ በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፥ ተኛ፤ በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፤ በተደፋበት ስፍራ በዚያ ወድቆ ሞተ።
28፤ ከመስኮት ሆና ተመለከተች፤ የሲሣራ እናት በሰቅሰቅ ዘልቃ። ስለ ምን ለመምጣት ሰረገላው ዘገየ? ስለ ምንስ የሰረገላው መንኰራኵር ቈየ? ብላ ጮኸች።
29፤ ብልሃተኞች ሴቶችዋ መለሱላት፤ እርስዋ ደግሞ ለራስዋ እንዲህ ብላ መለሰች።
30፤ ምርኮ አግኝተው የለምን? ተካፍለውስ የለምን? ለእያንዳንዱ ሰው ምርኮ አንዲት ወይም ሁለት ቈነጃጅት፤ ለሲሣራ ምርኮ ልዩ ልዩ ያለው ልብስ፥ በአንገትጌ ላይ በሁለት እጥፍ የተጠለፈ ዝንጕርጕር ልብስ።
31፤ አቤቱ፥ ጠላቶችህ ሁሉ እንዲሁ ይጥፉ፤ ወዳጆችህ ግን ፀሐይ በኃይሉ በወጣ ጊዜ እንደሚሆን፥ እንዲሁ ይሁኑ። ምድሪቱም አርባ ዓመት ያህል ዐረፈች።
ምዕራፍ 6

1፤ የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠሩ፤ እግዚአብሔርም በምድያም እጅ ሰባት ዓመት አሳልፎ ሰጣቸው።
2፤ የምድያምም እጅ በእስራኤል ላይ ጠነከረች፤ ከምድያምም የተነሣ የእስራኤል ልጆች በተራራ ላይ ጕድጓድና ዋሻ ምሽግም አበጁ።
3፤ እስራኤልም ዘር በዘሩ ጊዜ ምድያማውያን አማሌቃውያንም በምሥራቅም የሚኖሩ ሰዎች ይመጡባቸው ነበር፤
4፤ በእነርሱም ላይ ይሰፍሩ ነበር፥ እስከ ጋዛም ድረስ የምድሩን ቡቃያ ያጠፉ ነበር፥ ምግብንም ለእስራኤል አይተዉም ነበር፤ በግ ወይም በሬ ወይም አህያ ቢሆን አይተዉም።
5፤ እንስሶቻቸውንና ድንኳኖቻቸውን ይዘው በብዛት እንደ አንበጣ ሆነው ይመጡ ነበር፤ ለእነርሱና ለግመሎቻቸውም ቍጥር አልነበራቸውም፤ ምድሪቱንም ያጠፉ ዘንድ ይመጡ ነበር።
6፤ ከምድያምም የተነሣ እስራኤል እጅግ ተጠቁ፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።
7፤ እንዲህም ሆነ፤ የእስራኤል ልጆች በምድያም ምክንያት ወደ እግዚአብሔር በጮኹ ጊዜ፥
8፤ እግዚአብሔር ወደ እስራኤል ልጆች ነቢይ ላከ፥ እርሱም አለ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ከግብፅ ምድር አወጣኋችሁ፥ ከባርነትም ቤት አስለቀቅኋችሁ፤
9፤ ከግብፃውያንም እጅ፥ ከሚጋፉአችሁም ሁሉ እጅ አዳንኋችሁ፥ ከፊታችሁም አሳደድኋቸው፥ አገራቸውንም ሰጠኋችሁ፤
10፤ እናንተንም። እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ፤ በምድራቸው የተቀመጣችሁባቸውን የአሞራያውያንን አማልክት አትፍሩ አልኋችሁ። እናንተ ግን ድምፄን አልሰማችሁም።
11፤ የእግዚአብሔርም መልአክ መጥቶ በዖፍራ ባለችው ለአቢዔዝራዊው ለኢዮአስ በነበረችው በአድባሩ ዛፍ በታች ተቀመጠ፤ ልጁም ጌዴዎን ከምድያማውያን ለመሸሸግ በወይን መጥመቂያው ውስጥ ስንዴ ይወቃ ነበር።
12፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ለእርሱ ተገልጦ። አንተ ጽኑዕ ኃያል ሰው፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው አለው።
13፤ ጌዴዎንም። ጌታዬ ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብን? አባቶቻችንስ። እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶናል ብለው ይነግሩን የነበረ ተአምራቱ ወዴት አለ? ወዴት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል፥ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል አለው።
14፤ እግዚአብሔርም ወደ እርሱ ዘወር ብሎ። በዚህ በጕልበትህ ሂድ፥ እስራኤልንም ከምድያም እጅ አድን፤ እነሆ፥ ልኬሃለሁ አለው።
15፤ እርሱም። ጌታ ሆይ፥ እስራኤልን በምን አድናለሁ? ወገኔ ከምናሴ ነገድ ከሁሉ ይልቅ የተጠቃ ነው፤ እኔም በአባቴ ቤት የሁሉ ታናሽ ነኝ አለው።
16፤ እግዚአብሔርም። በእርግጥ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ ምድያምንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታለህ አለው።
17፤ እርሱም። በአንተ ዘንድ ሞገስ ካገኘሁ፥ የምትናገረኝም አንተ እንደ ሆንህ ምልክት አሳየኝ፤
18፤ ወደ አንተም እስክመለስ ድረስ፥ ቍርባኔንም አምጥቼ እስካቀርብልህ ድረስ፥ እባክህ፥ ከዚህ አትላወስ አለው። እርሱም። እስክትመለስ ድረስ እቆያለሁ አለ።
19፤ ጌዴዎን ገባ የፍየሉንም ጠቦት የኢፍ መስፈሪያም ዱቄት የቂጣ እንጎቻ አዘጋጀ፤ ሥጋውን በሌማት አኖረ፥ መረቁንም በምንቸት ውስጥ አደረገ፥ ሁሉንም ይዞ በአድባሩ ዛፍ በታች አቀረበለት።
20፤ የእግዚአብሔርም መልአክ። ሥጋውንና የቂጣውን እንጎቻ ወስደህ በዚህ ድንጋይ ላይ አኑር፥ መረቁንም አፍስስ አለው። እንዲሁም አደረገ።
21፤ የእግዚአብሔርም መልአክ በእጁ ያለውን የበትሩን ጫፍ ዘርግቶ ሥጋውንና የቂጣውን እንጎቻ አስነካ፤ እሳትም ከድንጋዩ ውስጥ ወጥቶ ሥጋውንና የቂጣውን እንጎቻ በላ። የእግዚአብሔርም መልአክ ከዓይኑ ተሰወረ።
22፤ ጌዴዎንም የእግዚአብሔር መልአክ እንደ ሆነ አየ፤ ጌዴዎንም። አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ ወዮልኝ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና አለ።
23፤ እግዚአብሔርም። ሰላም ለአንተ ይሁን፤ አትፍራ፤ አትሞትም አለው።
24፤ ጌዴዎንም በዚያ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፥ ስሙንም። እግዚአብሔር ሰላም ብሎ ጠራው። እርሱም እስከ ዛሬ ድረስ ለአቢዔዝራውያን በምትሆነው በዖፍራ አለ።
25፤ እግዚአብሔርም በዚያ ሌሊት። የአባትህን በሬ፥ ሰባት ዓመት የሆነውን ሁለተኛውን በሬ፥ ውሰድ፥ የአባትህ የሆነውንም የበኣል መሠዊያ አፍርስ፥ በእርሱም ዙሪያ ያለውን የማምለኪያ ዐፀድ ቍረጥ፤
26፤ በዚያም ኮረብታ አናት ላይ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሠዊያ አሳምረህ ሥራ ሁለተኛውንም በሬ ውሰድ፥ በዚያም በቈረጥኸው በማምለኪያ ዐፀዱ እንጨት ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቅርብ አለው።
27፤ ጌዴዎንም ከባሪያዎቹ አሥር ሰዎችን ወስዶ እግዚአብሔር እንዳለው አደረገ፤ የአባቱን ቤተ ሰቦች የከተማውንም ሰዎች ስለ ፈራ ይህን በቀን ለማድረግ አልቻለም፥ ነገር ግን በሌሊት አደረገው።
28፤ የከተማውም ሰዎች ማልደው ተነሡ፥ እነሆም፥ የበኣል መሠዊያ ፈርሶ፥ በዙሪያው ያለውም የማምለኪያ ዐፀድ ተቈርጦ፥ በተሠራውም መሠዊያ ላይ ሁለተኛው በሬ ተሠውቶ አገኙት።
29፤ እርስ በርሳቸውም። ይህን ነገር ያደረገ ማን ነው? ተባባሉ። በጠየቁና በመረመሩም ጊዜ። ይህን ነገር ያደረገ የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን ነው አሉ።
30፤ የከተማውም ሰዎች ኢዮአስን። የበኣልን መሠዊያ አፍርሶአልና፥ በዙሪያውም ያለውን የማምለኪያ ዐፀድ ቈርጦአልና እንዲሞት ልጅህን አውጣ አሉት።
31፤ ኢዮአስም እርሱን የተቃወሙትን ሁሉ። ለበኣል ትምዋገቱለታላችሁን? ወይስ እርሱን ታድናላችሁን? የሚምዋገትለት ሁሉ እስከ ነገ ይሙት፤ እርሱ አምላክ ከሆነ መሠዊያውን ካፈረሰው ጋር ለራሱ ይምዋገት አላቸው።
32፤ ስለዚህም በዚያ ቀን። መሠዊያውን አፍርሶአልና በኣል ከእርሱ ጋር ይምዋገት ብሎ ጌዴዎንን። ይሩበኣል ብሎ ጠራው።
33፤ ምድያማውያንም አማሌቃውያንም ሁሉ የምሥራቅም ሰዎች አንድ ሆነው ተሰበሰቡ፥ ዮርዳኖስንም ተሻገሩ፥ በኢይዝራኤልም ሸለቆ ሰፈሩ።
34፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በጌዴዎን ገባበት፥ እርሱም ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ የአቢዔዝርም ሰዎች ተጠርተው በኋላው ተከተሉት።
35፤ ወደ ምናሴም ነገድ ሁሉ መልክተኞችን ሰደደ እነርሱም ደግሞ ተጠርተው በኋላው ተከተሉት፤ መልክተኞችንም ወደ አሴርና ወደ ዛብሎን ወደ ንፍታሌምም ሰደደ፥ እነርሱም ሊገናኙአቸው ወጡ።
36፤ ጌዴዎንም እግዚአብሔርን። እንደ ተናገርህ የእስራኤልን ልጆች በእኔ እጅ ታድን እንደ ሆነ፥
37፤ እነሆ፥ በአውድማው ላይ የተባዘተ የበግ ጠጕር አኖራለሁ፤ በጠጕሩ ብቻ ላይ ጠል ቢሆን በምድሩም ሁሉ ደረቅ ቢሆን፥ እንደ ተናገርህ የእስራኤልን ልጆች በእኔ እጅ እንድታድናቸው አውቃለሁ አለ።
38፤ እንዲሁም ሆነ፤ በነጋውም ማልዶ ተነሣ፥ ጠጕሩንም ጨመቀው፥ ከጠጕሩም የተጨመቀው ጠል ቆሬ ሙሉ ውኃ ሆነ።
39፤ ጌዴዎንም እግዚአብሔርን። እኔ ይህን አንድ ጊዜ ስናገር አትቈጣኝ፤ እኔ ይህን አንድ ጊዜ በጠጕሩ፥ እባክህ፥ ልፈትን፤ አሁንም በጠጕሩ ብቻ ላይ ደረቅ ይሁን፥ በምድሩም ሁሉ ላይ ጠል ይሁን አለው።
40፤ እግዚአብሔርም በዚያ ሌሊት እንዲሁ አደረገ፤ በጠጕሩ ብቻ ላይ ደረቅ ነበረ፥ በምድሩም ሁሉ ላይ ጠል ነበረ። a
ምዕራፍ 7

1፤ ጌዴዎን የተባለውም ይሩበኣል ከእርሱም ጋር የነበሩ ሕዝብ ሁሉ ማልደው ተነሡ፥ በሐሮድ ምንጭ አጠገብም ሰፈሩ፤ የምድያምም ሰፈር ከእነርሱ ወደ ሰሜን በኩል በሞሬ ኮረብታ አጠገብ በሸለቆው ውስጥ ነበረ።
2፤ እግዚአብሔርም ጌዴዎንን። ከአንተ ጋር ያለው ሕዝብ በዝቶአል፤ ስለዚህ እስራኤል። እጄ አዳነኝ ብሎ እንዳይታበይብኝ እኔ ምድያምን በእጃቸው አሳልፌ አልሰጣቸውም።
3፤ አሁንም እንግዲህ። የፈራ የደነገጠም ከገለዓድ ተራራ ተነሥቶ ይመለስ ብለህ በሕዝቡ ጆሮ አውጅ አለው። ከሕዝቡም ሀያ ሁለት ሺህ ተመለሱ፥ አሥርም ሺህ ቀሩ።
4፤ እግዚአብሔርም ጌዴዎንን። ሕዝቡ ገና ብዙ ነው፤ ወደ ውኃ አውርዳቸው፥ በዚያም እፈትናቸዋለሁ፤ እኔም። ይህ ከአንተ ጋር ይሂድ የምለው እርሱ ከአንተ ጋር ይሄዳል፤ እኔም። ይህ ከአንተ ጋር አይሂድ የምለው እርሱ አይሄድም አለው።
5፤ ሕዝቡንም ወደ ውኃ አወረደ። እግዚአብሔርም ጌዴዎንን። ውሻ እንደሚጠጣ ውኃ በምላሱ የሚጠጣውን ሁሉ፥ እርሱን ለብቻው አድርገው፤ እንዲሁም ሊጠጣ በጕልበቱ የሚንበረከከውን ሁሉ ለብቻው አድርገው አለው።
6፤ በእጃቸውም ውኃ ወደ አፋቸው አድርገው የጠጡት ቍጥር ሦስት መቶ ነበረ፤ የቀሩት ሕዝብ ግን ውኃ ሊጠጡ በጕልበታቸው ተንበረከኩ።
7፤ እግዚአብሔርም ጌዴዎንን። በእጃቸው ውኃ በጠጡት በሦስት መቶ ሰዎች አድናችኋለሁ፥ ምድያማውያንንም በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ የቀሩት ሕዝብ ሁሉ ግን ወደ ስፍራቸው ይመለሱ አለው።
8፤ የሕዝቡንም ስንቅና ቀንደ መለከት በእጃቸው ወሰዱ፤ የቀሩትንም የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ወደ ድንኳናቸው ሰደዳቸው፥ ሦስቱን መቶ ሰዎች ግን በእርሱ ዘንድ ጠበቃቸው፤ የምድያምም ሰፈር ከእርሱ በታች በሸለቆው ውስጥ ነበረ።
9፤ በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር። በእጅህ አሳልፌ ሰጥቻቸዋለሁና ተነሥተህ ወደ ሰፈር ውረድ።
10፤ አንተም ለመውረድ ብትፈራ አንተ ከሎሌህ ከፉራ ጋር ወደ ሰፈሩ ውረድ፤
11፤ የሚናገሩትንም ትሰማለህ፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ትወርድ ዘንድ እጅህ ትበረታለች አለው። እርሱና ሎሌው ፉራ በሰፈሩ ዳርቻ ወደ ነበሩት ሰልፈኞች ወረዱ።
12፤ ብዛታቸውም እንደ አንበጣ የሆነ ምድያማውያንና አማሌቃውያን የምሥራቅም ሰዎች ሁሉ በሸለቆው ውስጥ ሰፍረው ነበር፤ የግመሎቻቸውም ብዛት ቍጥር እንደ ሌለው በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ነበረ።
13፤ ጌዴዎንም በደረሰ ጊዜ አንድ ሰው ሕልምን ለባልንጀራው ሲያጫውት። እነሆ፥ ሕልም አለምሁ፤ እነሆም፥ አንዲት የገብስ እንጎቻ ወደ ምድያም ሰፈር ተንከባልላ ወረደች፥ ወደ ድንኳኑም ደርሳ እስኪወድቅ ድረስ መታችው፥ ገለበጠችውም፥ ድንኳኑም ተጋደመ ይል ነበር።
14፤ ባልንጀራውም መልሶ። ይህ ነገር ከእስራኤል ሰው ከኢዮአስ ልጅ ከጌዴዎን ሰይፍ በቀር ሌላ አይደለም፤ እግዚአብሔር ምድያምንና ሠራዊቱን ሁሉ በእጁ አሳልፎ ሰጥቶአል አለው።
15፤ ጌዴዎንም ሕልሙንና ትርጓሜውን በሰማ ጊዜ ሰገደ፤ ወደ እስራኤልም ሰፈር ተመልሶ። እግዚአብሔር የምድያምን ሠራዊት በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአልና ተነሡ አለ።
16፤ ሦስቱንም መቶ ሰዎች በሦስት ወገን ከፈላቸው፥ በሁሉም እጅ ቀንደ መለከትና ባዶ ማሰሮ፥ በማሰሮውም ውስጥ ችቦ ሰጠ።
17፤ እርሱም። እኔን ተመልከቱ፥ እንዲሁም አድርጉ፤ እነሆም፥ ወደ ሰፈሩ ዳርቻ በደረስሁ ጊዜ እኔ እንደማደርግ እንዲሁ እናንተ አድርጉ፤
18፤ እኔ ከእኔም ጋር ያሉት ሁሉ ቀንደ መለከት ስንነፋ፥ እናንተ ደግሞ በሰፈሩ ዙሪያ ሁሉ ቀንደ መለከታችሁን ንፉ። ለእግዚአብሔርና ለጌዴዎን በሉ አላቸው።
19፤ ጌዴዎንም ከእርሱም ጋር የነበሩት መቶ ሰዎች በመካከለኛው ትጋት ትጋቱም በተጀመረ ጊዜ ወደ ሰፈሩ ዳርቻ መጡ፤ ቀንደ መለከቶችንም ነፉ፥ በእጃቸውም የነበሩትን ማሰሮች ሰባበሩ።
20፤ ሦስቱም ወገኖች ቀንደ መለከቶችን ነፉ፥ ማሰሮችንም ሰበሩ፥ በግራ እጃቸውም ችቦችን፥ በቀኝ እጃቸውም ቀንደ መለከቶችን ይዘው እየነፉ። የእግዚአብሔርና የጌዴዎን ሰይፍ ብለው ጮኹ።
21፤ ሁሉም በየቦታው በሰፈሩ ዙሪያ ቆመ፤ ሠራዊቱም ሁሉ ሮጠ፥ ጮኸ፥ ሸሸም።
22፤ ሦስቱንም መቶ ቀንደ መለከቶች ነፉ፥ እግዚአብሔርም የሰውን ሁሉ ሰይፍ በባልንጀራውና በሠራዊቱ ሁሉ ላይ አደረገ፤ ሠራዊቱም በጽሬራ በኩል እስከ ቤትሺጣ ድረስ በጠባት አጠገብ እስካለው እስከ አቤልምሖላ ዳርቻ ድረስ ሸሸ።
23፤ የእስራኤልም ሰዎች ከንፍታሌምና ከአሴር ከምናሴም ሁሉ ተሰብስበው ምድያምን አሳደዱ።
24፤ ጌዴዎንም። ምድያምን ለመገናኘት ውረዱ፥ እስከ ቤትባራም ድረስ ያለውን ውኃ፥ ዮርዳኖስን፥ ያዙባቸው ብሎ መልክተኞችን በኤፍሬም ወዳለው ተራራማ አገር ሁሉ ሰደደ። የኤፍሬም ሰዎችም ሁሉ ተሰብስበው እስከ ቤትባራ ድረስ ውኃውን፥ ዮርዳኖስን፥ ያዙ።
25፤ የምድያምን ሁለቱን መኳንንት ሔሬብንና ዜብን ያዙ፤ ሔሬብንም በሔሬብ ዓለት አጠገብ ገደሉት፥ ዜብንም በዜብ መጥመቂያ ላይ ገደሉት፤ ምድያምንም አሳደዱ፥ የሔሬብንና የዜብንም ራስ ይዘው ወደ ዮርዳኖስ ማዶ ወደ ጌዴዎን መጡ።
ምዕራፍ 8

1፤ የኤፍሬም ሰዎች። ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው? ምድያምን ለመዋጋት በወጣህ ጊዜ ለምን አልጠራኸንም? አሉት። ጽኑ ጥልም ተጣሉት።
2፤ እርሱም። እኔ ካደረግሁት እናንተ ያደረጋችሁት አይበልጥምን? የኤፍሬም ወይን ቃርሚያ ከአቢዔዝር ወይን መከር አይሻልምን?
3፤ እግዚአብሔር የምድያምን መኳንንት ሔሬብንና ዜብን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋል፤ እናንተ ያደረጋችሁትን የሚመስል እኔ ምን ማድረግ እችል ኖሮአል? አላቸው። ይህን በተናገረ ጊዜ ቍጣቸው በረደ።
4፤ ጌዴዎንም ከሦስቱ መቶ ሰዎች ጋር ወደ ዮርዳኖስ ደርሶ ተሻገረ፤ ምንም እንኳ ቢደክሙ ያሳድዱ ነበር።
5፤ የሱኮትንም ሰዎች። የምድያምን ነገሥታት ዛብሄልንና ስልማናን ሳሳድድ፥ ደክመዋልና እኔን ለተከተሉ ሕዝብ እንጀራ፥ እባካችሁ፥ ስጡ አላቸው።
6፤ የሱኮትም አለቆች። እኛ ለሠራዊትህ እንጀራ እንድንሰጥ የዛብሄልና የስልማና እጅ አሁን በእጅህ ነውን? አሉ።
7፤ ጌዴዎንም። እግዚአብሔር ዛብሄልንና ስልማናን በእጄ አሳልፎ ሲሰጠኝ እኔ በምድረ በዳ እሾህና በኵርንችት ሥጋችሁን እገርፋለሁ አለ።
8፤ ከዚያም ወደ ጵኒኤል ወጣ፥ ለጵኒኤልም ሰዎች እንዲሁ አላቸው፤ የጵንኤልም ሰዎች የሱኮት ሰዎች እንደ መለሱ መለሱለት።
9፤ እርሱም የጵኒኤልን ሰዎች ደግሞ። በደኅና በተመለስሁ ጊዜ ይህን ግንብ አፈርሰዋለሁ ብሎ ተናገራቸው።
10፤ ዛብሄልና ስልማናም ከሠራዊቶቻቸው ጋር በቀርቀር ነበሩ፤ ሰይፍ የሚመዝዙ መቶ ሀያ ሺህ ሰዎች ወድቀው ነበርና ከምሥራቅ ሰዎች ሠራዊት ሁሉ የቀሩ አሥራ አምስት ሺህ ያህል ሰዎች ነበሩ።
11፤ ጌዴዎንም የድንኳን ተቀማጮች ባሉበት መንገድ በኖባህና በዮግብሃ በምሥራቅ በኩል ወጣ፤ ሠራዊቱም ተዘልሎ ነበርና ሠራዊቱን መታ።
12፤ ዛብሄልና ስልማናም ሸሹ፤ እርሱም አሳደዳቸው፥ ሁለቱንም የምድያም ነገሥታት ዛብሄልንና ስልማናን ያዘ፥ ሠራዊቱንም ሁሉ አስደነገጠ።
13፤ የኢዮአስ ልጅም ጌዴዎን ከሔሬስ ዳገት ከሰልፍ ተመለሰ።
14፤ ከሱኮትም ሰዎች አንድ ብላቴና ይዞ ጠየቀው፤ እርሱም የሱኮትን አለቆችና ሽማግሌዎች ሰባ ሳባት ሰዎች ጻፈለት።
15፤ ወደ ሱኮትም ሰዎች መጥቶ። ለደከሙት ሰዎችህ እንጀራ እንሰጥ ዘንድ የዛብሄልና የስልማና እጅ አሁን በእጅህ ነውን? ብላችሁ የተላገዳችሁብኝ፥ ዛብሄልና ስልማና እነሆ፥ አለ።
16፤ የከተማይቱንም ሽማግሌዎች ያዘ፥ የምድረ በዳንም እሾህና ኵርንችት ወስዶ የሱኮትን ሰዎች ገረፋቸው።
17፤ የጵኒኤልንም ግንብ አፈረሰ፥ የከተማይቱንም ሰዎች ገደላቸው።
18፤ ዛብሄልንና ስልማናን። በታቦር የገደላችኋቸው ሰዎች እንዴት ያሉ ነበሩ? አላቸው። እነርሱም። እንደ አንተ ያሉ ነበሩ፥ አንተንም ይመስሉ ነበር፤ መልካቸውም እንደ ንጉሥ ልጆች መልክ ነበረ ብለው መለሱለት።
19፤ እርሱም። የእናቴ ልጆች ወንድሞቼ ነበሩ፤ አድናችኋቸው ቢሆን ኖሮ፥ ሕያው እግዚአብሔርን! እኔ አልገድላችሁም ነበር አለ።
20፤ በኵሩንም ዬቴርን። ተነሥተህ ግደላቸው አለው፤ ብላቴናው ግን ገና ብላቴና ነበረና ስለ ፈራ ሰይፉን አልመዘዘም።
21፤ ዛብሄልና ስልማናም። የሰው ኃይሉ እንደ ሰውነቱ ነውና አንተ ተነሥተህ ውደቅብን አሉት። ጌዴዎንም ተነሥቶ ዛብሄልንና ስልማናን ገደለ፥ በግመሎቻቸውም አንገት የነበሩትን ሥሉሴዎች ማረከ።
22፤ የእስራኤልም ሰዎች ጌዴዎንን። ከምድያም እጅ አድነኸናልና አንተ ልጅህም የልጅ ልጅህም ደግሞ ግዙን አሉት።
23፤ ጌዴዎንም። እኔ አልገዛችሁም፥ ልጄም አይገዛችሁም፤ እግዚአብሔር ይገዛችኋል አላቸው።
24፤ እስማኤላውያንም ስለ ነበሩ የወርቅ ጕትቻ ነበራቸውና ጌዴዎን። ሁላችሁ ከምርኮአችሁ ጕትቻችሁን እንድትሰጡኝ እለምናችኋለሁ አላቸው።
25፤ እነርሱም። ፈቅደን እንሰጥሃለን ብለው መለሱለት። መጎናጸፊያም አነጠፉ፥ ሰውም ሁሉ የምርኮውን ጕትቻ በዚያ ላይ ጣለ።
26፤ የለመነውም የወርቅ ጕትቻ ሚዛኑ፥ ከአምባሩ፥ ከድሪውም፥ የምድያምም ነገሥታት ከለበሱት ከቀዩ ቀሚስ፥ በግመሎቻቸውም አንገት ከነበሩት ሥሉሴዎች ሌላ፥ ሺህ ሰባት መቶ ሰቅለ ወርቅ ነበረ።
27፤ ጌዴዎንም ኤፉድ አድርጎ አሠራው፥ በከተማውም በዖፍራ አኖረው፤ እስራኤልም ሁሉ ተከትሎት አመነዘረበት፤ ለጌዴዎንና ለቤቱም ወጥመድ ሆነ።
28፤ ምድያምም በእስራኤል ልጆች ተዋረደ፥ ራሳቸውንም ዳግመኛ አላነሡም፤ በጌዴዎንም ዕድሜ ምድሪቱ አርባ ዓመት ዐረፈች።
29፤ የኢዮአስም ልጅ ይሩበኣል ሄዶ በቤቱ ተቀመጠ።
30፤ ለጌዴዎንም ብዙ ሚስቶች ነበሩትና ከወገቡ የወጡ ሰባ ልጆች ነበሩት።
31፤ በሴኬምም የነበረችው ቁባቱ ወንድ ልጅ ወለደችለት፥ ስሙንም አቤሜሌክ ብሎ ጠራው።
32፤ የኢዮአስም ልጅ ጌዴዎን በመልካም ሽምግልና ሞተ፥ በአቢዔዝራውያንም ከተማ በዖፍራ በነበረችው በአባቱ በኢዮአስ መቃብር ተቀበረ።
33፤ እንዲህም ሆነ፤ ጌዴዎን ከሞተ በኋላ የእስራኤል ልጆች ተመለሱ፥ በኣሊምንም ተከትለው አመነዘሩ፤ በኣልብሪትንም አምላካቸው አደረጉ።
34፤ የእስራኤልም ልጆች በዙሪያቸው ከነበሩት ከጠላቶቻቸው ሁሉ እጅ ያዳናቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን አላሰቡትም፤
35፤ እርሱም ለእስራኤል በጎ ነገርን ሁሉ እንዳደረገ መጠን፥ እነርሱ ለጌዴዎን ለይሩበኣል ቤት ወረታ አላደረጉም።
ምዕራፍ 9

1፤ የይሩበኣል ልጅ አቤሜሌክም ወደ ሴኬም ወደ እናቱ ወንድሞች ሄደ፥ ለእነርሱም ለእናቱ አባት ቤተ ሰቦችም ሁሉ።
2፤ በሴኬም ሰዎች ሁሉ ጆሮ። ሰባ የሆኑት የይሩበኣል ልጆች ሁሉ ቢገዙአችሁ ወይስ አንድ ሰው ቢገዛችሁ ምን ይሻላችኋል? ብላችሁ ንገሩአቸው ብዬ እለምናችኋለሁ፤ ደግሞ እኔ የአጥንታችሁ ፍላጭ የሥጋችሁ ቍራጭ እንደ ሆንሁ አስቡ ብሎ ተናገራቸው።
3፤ የእናቱም ወንድሞች ይህን ቃል ሁሉ ስለ እርሱ በሴኬም ሰዎች ሁሉ ጆሮ ተናገሩ፤ እነርሱም። እርሱ ወንድማችን ነው ብለው አቤሜሌክን ለመከተል ልባቸውን አዘነበሉት።
4፤ ከበኣልብሪትም ቤት ሰባ ብር ሰጡት፤ በዚያም አቤሜሌክ ምናምንቴዎችንና ወሮበሎችን ቀጠረበት፥ እነርሱም ተከተሉት።
5፤ ወደ አባቱም ቤት ወደ ዖፍራ ሄደ፤ ሰባ የሆኑትን የይሩበኣልን ልጆች ወንድሞቹን በአንድ ድንጋይ ላይ አረዳቸው፤ ትንሹ የይሩበኣል ልጅ ኢዮአታም ግን ተሸሽጎ ነበርና ተረፈ።
6፤ የሴኬምም ሰዎች ሁሉ ቤትሚሎም ሁሉ ተሰበሰቡ፥ ሄደውም በሴኬም በዓምዱ አጠገብ ባለው በአድባሩ ዛፍ በታች አቤሜሌክን አነገሡ።
7፤ ይህንም ነገር ለኢዮአታም በነገሩት ጊዜ፥ ሄዶ በገሪዛን ተራራ ራስ ላይ ቆመ፥ ድምፁንም አንሥቶ ጮኸ፥ እንዲህም አላቸው። የሴኬም ሰዎች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲሰማችሁ ስሙኝ።
8፤ አንድ ጊዜ ዛፎች በላያቸው ንጉሥ ሊያነግሡ ጌዱ፤ ወይራውንም። በእኛ ላይ ንገሥ አሉት።
9፤ ወይራው ግን። እግዚአብሔርና ሰዎች በእኔ የሚከበሩበትን ቅባቴን ትቼ በዛፎች ላይ እንድሰፍፍ ልሂድ? አላቸው።
10፤ ዛፎችም በለሱን። መጥተህ በላያችን ንገሥ አሉት።
11፤ በለሱ ግን። ጣፋጭነቴንና መልካሙን ፍሬዬን ትቼ በዛፎች ላይ እንድሰፍፍ ልሂድ? አላቸው።
12፤ ዛፎችም ውይኑን። መጥተህ በላያችን ንገሥ አሉት።
13፤ ወይኑም። እግዚአብሔርንና ሰውን ደስ የሚያሰኘውን የወይን ጠጄን ትቼ በዛፎች ላይ እንድሰፍፍ ልሂድ? አላቸው።
14፤ ዛፎችም ሁሉ እሾህን። መጥተህ በላያችን ንገሥ አሉት።
15፤ እሾሁም ዛፎችን። በእውነት እኔን በእናንተ ላይ ታነግሡኝ እንደ ሆነ ኑ ከጥላዬ በታች ተጠጉ። እንዲሁም ባይሆን እሳት ከእሾህ ይውጣ፥ የሊባኖስንም ዝግባ ያቃጥል አላቸው።
16፤ አሁን እንግዲህ አቤሜሌክን በማንገሣችሁ እውነትንና ቅንነትን አድርጋችሁ እንደ ሆነ፥ ለይሩበኣልም ለቤቱም በጎ አድርጋችሁ እንደ ሆነ፥ እንዳደረገውም መጠን ለእርሱ የተገባውን አድርጋችሁ እንደ ሆነ፥
17፤ አባቴ ስለ እናንተ ተጋድሎ ነበርና፥ ከምድያምም እጅ ሊያድናችሁ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶ ነበርና፥
18፤ እናንተም ዛሬ በአባቴ ቤት ተነሥታችኋልና፥ ሰባ የሆኑትን ልጆቹንም በአንድ ድንጋይ ላይ አርዳችኋልና፥ ወንድማችሁም ስለ ሆነ የባሪያይቱን ልጅ አቤሜሌክን በሴኬም ሰዎች ላይ አንግሣችኋልና፥
19፤ እንግዲህ ለይሩበኣልና ለቤቱ እውነትንና ቅንነትን ዛሬ አድርጋችሁ እንደ ሆነ፥ በአቤሜሌክ ደስ ይበላችሁ፥ እርሱ ደግሞ በእናንተ ደስ ይበለው፤
20፤ እንዲህ ባይሆን ግን ከአቤሜሌክ እሳት ይውጣ፥ የሴኬምንም ሰዎች ቤትሚሎንም ይብላ፤ ከሴኬምም ሰዎች ከቤትሚሎም እሳት ይውጣ፥ አቤሜሌክንም ይብላ።
21፤ ኢዮአታምም ሸሽቶ አመለጠ፥ ወንድሙንም አቤሜሌክን ፈርቶ ወደ ብኤር ሄደ፥ በዚያም ተቀመጠ።
22፤ አቤሜሌክም በእስራኤል ላይ ሦስት ዓመት ነገሠ።
23፤ እግዚአብሔር በአቤሜሌክና በሴኬም ሰዎች መካከል ክፉን መንፈስ ሰደደ፤ የሴኬምም ሰዎች በአቤሜሌክ ላይ ተንኰል አደረጉ።
24፤ ይህም የሆነው፥ በሰባ የይሩበኣል ልጆቹ ላይ የተደረገው ዓመፅ እንዲመጣ፥ ደማቸውም በገደላቸው በወንድማቸው በአቤሜሌክ ላይ፥ ወንድሞቹንም እንዲገድል እጆቹን ባጸኑአቸው በሴኬም ሰዎች ላይ እንዲሆን ነው።
25፤ የሴኬምም ሰዎች በተራሮች ራስ ላይ ድብቅ ጦር አደረጉ፥ መንገድ ተላላፊዎችንም ሁሉ ይዘርፉ ነበር፤ አቤሜሌክም ይህን ወሬ ሰማ።
26፤ የአቤድም ልጅ ገዓል ከወንድሞቹ ጋር መጥቶ ወደ ሴኬም ገባ፤ የሴኬምም ሰዎች ታመኑበት።
27፤ ወደ እርሻውም ወጡ ወይናቸውንም ለቀሙ፥ ጠመቁትም፥ የደስታም በዓል አደረጉ፤ ወደ አምላካቸውም ቤት ገቡ፥ በሉም ጠጡም፥ አቤሜሌክንም ሰደቡ።
28፤ የአቤድም ልጅ ገዓል። የምንገዛለት አቤሜሌክ ማን ነው? ሴኬምስ ምንድርነው? እርሱ የይሩብኣል ልጅ አይደለምን? ዜቡልም የእርሱ ሹም አይደለምን? ለሴኬም አባት ለኤሞር ሰዎች ተገዙ፤
29፤ ስለ ምንስ ለዚህ እንገዛለን? ይህ ሕዝብ ከእጄ በታች ቢሆን ኖሮ አቤሜሌክን አሳድደው ነበር አለ። አቤሜሌክንም። ሠራዊትህን አብዝተህ ና፥ ውጣ አለው።
30፤ የከተማይቱ ገዥ ዜቡልም የአቤድን ልጅ የገዓልን ቃል በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ።
31፤ እንዲህም ብሎ ወደ አቤሜሌክ በተንኰል መልክተኞች ላከ። እነሆ፥ የአቤድ ልጅ ገዓልና ወንድሞቹ ወደ ሴኬም መጥተዋል፥ በአንተም ላይ ከተማይቱን አሸፍተዋል።
32፤ አሁንም አንተና ከአንተ ጋር ያሉት ሕዝብ በሌሊት ተነሡ፥ በሜዳም ሸምቁ፤
33፤ ነገም ፀሐይ በወጣች ጊዜ ማልደህ ተነሣ፥ በከተማይቱም ላይ ውደቅባት፤ እነሆም፥ እርሱና ከእርሱ ጋር ያሉት ሕዝብ በአንተ ላይ በወጡ ጊዜ እጅህ እንዳገኘች አድርግበት።
34፤ አቤሜሌክና ከእርሱም ጋር ያሉ ሕዝብ ሁሉ በሌሊት ተነሡ፥ በሴኬምም አቅራቢያ በአራት ወገን ሸመቁበት።
35፤ የአቤድም ልጅ ገዓል ወጥቶ በከተማይቱ በር አደባባይ ቆመ፤ አቤሜሌክና ከእርሱ ጋር ያሉት ሕዝብ ከሸመቁበት ስፍራ ተነሱ።
36፤ ገዓልም ሕዝቡን ባየ ጊዜ ዜቡልን። እነሆ፥ ከተራሮች ራስ ሕዝብ ይወርዳል አለው። ዜቡልም። ሰዎች የሚመስለውን የተራሮችን ጥላ ታያለህ አለው።
37፤ ገዓልም ደግሞ። እነሆ፥ ሕዝብ በምድር መካከል ይወርዳል፤ አንድም ወገን በምዖንኒም በአድባሩ ዛፍ መንገድ ይመጣል ብሎ ተናገረ።
38፤ ዜቡልም። እንገዛለት ዘንድ አቤሜሌክ ማን ነው? ያልህበት አፍህ አሁን የት አለ? ይህ የናቅኸው ሕዝብ አይደለምን? አሁንም ወጥተህ ከእነርሱ ጋር ተዋጋ አለው።
39፤ ገዓልም በሴኬም ሰዎች ፊት ወጣ፥ ከአቤሜሌክም ጋር ተዋጋ።
40፤ አቤሜሌክም አሳደደው፤ በፊቱም ሸሸ፥ እስከ በሩም አደባባይ ድረስ ብዙዎች ተጐድተው ወደቁ።
41፤ አቤሜሌክም በአሩማ ተቀመጠ፤ ዜቡልም ገዓልንና ወንድሞቹን በሴኬም እንዳይኖሩ አሳደዳቸው።
42፤ በነጋውም ሕዝቡ ወደ እርሻ ወጡ፤ አቤሜሌክም ሰማ።
43፤ ሕዝቡንም ወስዶ በሦስት ወገን ከፈላቸው፥ በሜዳም ሸመቀ፤ ተመለከተም፥ እነሆም፥ ሕዝቡ ከከተማ ወጡ፥ ተነሣባቸውም መታቸውም።
44፤ አቤሜሌክም ከእርሱም ጋር ያሉት ወገኖች ተጣደፉ በከተማይቱም በር አደባባይ ቆሙ፤ ሁለቱም ወገኖች በእርሻው ውስጥ በነበሩት ሁሉ ላይ ሮጡባቸው፥ መቱአቸውም።
45፤ አቤሜሌክም በዚያ ቀን ሁሉ ከከተማይቱ ጋር ተዋጋ፤ ከተማይቱንም ይዞ በእርሷ የነበሩትን ሕዝብ ገደለ፤ ከተማይቱንም አፈረሰ፥ ጨውም ዘራባት።
46፤ በሴኬምም ግንብ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ ወደ ኤልብሪት ቤት ወደ ምሽጉ ውስጥ ገቡ።
47፤ አቤሜሌክም በሴኬም ግንብ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ አንድ ሆነው እንደ ተሰበሰቡ ሰማ።
48፤ አቤሜሌክና ከእርሱ ጋር ያሉትም ሕዝብ ሁሉ ወደ ሰልሞን ተራራ ወጡ፤ አቤሜሌክም በእጁ መጥረቢያ ወስዶ የዛፉን ቅርንጫፍ ቈረጠ፥ አንሥቶም በጫንቃው ላይ አደረገው፤ ከእርሱም ጋር ለነበሩት ሕዝብ። እኔ ሳደርግ ያያችሁትን፥ እናንተም ፈጥናችሁ እኔ እንዳደረግሁ አድርጉ አላቸው።
49፤ ሕዝቡም ሁሉ እንዲሁ እያንዳንዳቸው የዛፉን ቅርንጫፎች ቈረጡ፥ አቤሜሌክንም ተከትለው በምሽጉ ዙሪያ አኖሩአቸው፥ ምሽጉንም በላያቸው አቃጠሉት፤ የሴኬምም ግንብ ሰዎች ሁሉ ደግሞ አንድ ሺህ የሚያህሉ ወንድና ሴት ሞቱ።
50፤ አቤሜሌክም ወደ ቴቤስ መጣ፥ ቴቤስንም ከብቦ ያዛት።
51፤ በከተማይቱም ውስጥ ብርቱ ግንብ ነበረ፥ የከተማይቱም ሰዎች ሁሉ፥ ወንዱና ሴቱ ሁሉ፥ ወደዚያ ሸሹ፤ ደጁንም በኋላቸው ዘጉ፥ ወደ ግንቡም ሰገነት ላይ ወጡ።
52፤ አቤሜሌክም ወደ ግንቡ ቀርቦ ይዋጋ ነበር፥ በእሳትም ሊያቃጥለው ወደ ግንቡ ደጅ ደረሰ።
53፤ አንዲትም ሴት በአቤሜሌክ ራስ ላይ የወፍጮ መጅ ጣለችበት፥ አናቱንም ሰበረችው።
54፤ እርሱም ፈጥኖ ጋሻ ዣግሬውን ጠርቶ። እኔን። ሴት ገደለችው እንዳይሉ ሰይፍህን መዝዘህ ግደለኝ አለው፤ ጕልማሳውም ወጋው፥ ሞተም።
55፤ የእስራኤልም ሰዎች አቤሜሌክ እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ እያንዳንዱ ወደ ስፍራው ተመለሰ።
56፤ እንዲሁ ሰባ ወንድሞቹን በመግደል አቤሜሌክ በአባቱ ላይ ያደረገውን ክፋት እግዚአብሔር መለሰበት።
57፤ እግዚአብሔርም የሴኬምን ሰዎች ክፋት ሁሉ በራሳቸው ላይ መለሰባቸው፤ የይሩበኣልም ልጅ የኢዮአታም እርግማን ደረሰባቸው።
ምዕራፍ 10

1፤ ከአቤሜሌክም በኋላ ከይሳኮር ነገድ የሆነ የዱዲ ልጅ የፎሖ ልጅ ቶላ እስራኤልን ለማዳን ተነሣ፤ በተራራማውም በኤፍሬም አገር ባለችው በሳምር ተቀምጦ ነበር።
2፤ በእስራኤልም ላይ ሀያ ሦስት ዓመት ፈረደ፤ ሞተም፥ በሳምርም ተቀበረ።
3፤ ከእርሱም በኋላ ገለዓዳዊው ኢያዕር ተነሣ፥ በእስራኤልም ላይ ሀያ ሁለት ዓመት ፈረደ።
4፤ በሠላሳ የአህያ ግልገሎች ይቀመጡ የነበሩ ሠላሳ ልጆችም ነበሩት፤ ለእነርሱም እስከ ዛሬ ድረስ የኢያዕር መንደሮች የተባሉ በገለዓድ ምድር ያሉ ሠላሳ ከተሞች ነበሩአቸው።
5፤ ኢያዕርም ሞተ፥ በቃሞንም ተቀበረ።
6፤ የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ በኣሊምንና አስታሮትን የሶርያንም አማልክት፥ የሲዶናንም አማልክት፥ የሞዓብንም አማልክት፥ የአሞንንም ልጆች አማልክት፥ የፍልስጥኤማውያንንም አማልክት አመለኩ፤ እግዚአብሔርንም ተዉ፥ አላመለኩትምም።
7፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ በፍልስጥኤማውያንና በአሞን ልጆች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው።
8፤ በዚያም ዓመት የእስራኤልን ልጆች ሥቃይ አበዙባቸው፤ በዮርዳኖስ ማዶ በአሞራውያን አገር በገለዓድ ውስጥ ያሉትን የእስራኤልን ልጆች ሁሉ አሥራ ስምንት ዓመት ተጋፉአቸው።
9፤ የአሞንም ልጆች ከይሁዳ ከብንያምና ከኤፍሬም ቤት ጋር ደግሞ ሊዋጋ ዮርዳኖስን ተሻገሩ፤ እስራኤልም እጅግ ተጨነቁ።
10፤ የእስራኤልም ልጆች። አምላካችንን ትተን በኣሊምን አምልከናልና አንተን በድለናል ብለው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።
11፤ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች አላቸው። ግብፃውያን፥ አሞራውያንም፥ የአሞንም ልጆች፥
12፤ ፍልስጥኤማውያንም፥ ሲዶናውያንም፥ አማሌቃውያንም፥ ማዖናውያንም አላስጨነቋችሁምን? ወደ እኔም ጮኻችሁ፥ እኔም ከእጃቸው አዳንኋችሁ።
13፤ እናንተ ግን ተዋችሁኝ ሌሎችንም አማልክት አመለካችሁ፤ ስለዚህም ደግሞ አላድናችሁም።
14፤ ሄዳችሁም የመረጣችኋቸውን አማልክት ጥሩ፤ እነርሱም በመከራችሁ ጊዜ ያድኑአችሁ።
15፤ የእስራኤልም ልጆች እግዚአብሔርን። እኛ ኃጢአትን ሠርተናል፤ አንተ ደስ የሚያሰኝህን አድርግብን ዛሬ ግን፥ እባክህ፥ አድነን አሉት።
16፤ ሌሎችንም አማልክት ከመካከላቸው አስወገዱ፥ እግዚአብሔርንም አመለኩ፤ ነፍሱም ስለ እስራኤል ጕስቍልና አዘነች።
17፤ የአሞንም ልጆች ተሰብስበው በገለዓድ ሰፈሩ። የእስራኤልም ልጆች ተሰብስበው በምጽጳ ሰፈሩ።
18፤ ሕዝቡም፥ የገለዓድ አለቆች፥ እርስ በእርሳቸው። ከአሞን ልጆች ጋር መዋጋት የሚጀምር ማን ነው? እርሱ በገለዓድ ሰዎች ሁሉ ላይ አለቃ ይሆናል አሉ። a
ምዕራፍ 11

1፤ ገለዓዳዊውም ዮፍታሔ ጽኑዕ ኃያል ሰው የጋለሞታ ሴትም ልጅ ነበረ። ገለዓድም ዮፍታሔን ወለደ።
2፤ የገለዓድም ሚስት ወንዶች ልጆችን ወለደችለት፤ ልጆችዋም ባደጉ ጊዜ ዮፍታሔን። የልዩ ሴት ልጅ ነህና በአባታችን ቤት አትወርስም ብለው አሳደዱት።
3፤ ዮፍታሔም ከወንድሞቹ ፊት ሸሽቶ በጦብ ምድር ተቀመጠ፤ ምናምንቴዎችም ሰዎች ተሰብስበው ዮፍታሔን ተከተሉት።
4፤ ከዚያም ወራት በኋላ የአሞን ልጆች ከእስራኤል ጋር ይዋጉ ነበር።
5፤ የአሞንም ልጆች ከእስራኤል ጋር በተዋጉ ጊዜ የገለዓድ ሽማግሌዎች ዮፍታሔን ከጦብ ምድር ለማምጣት ሄዱ።
6፤ ዮፍታሔንም። ና፥ ከአሞን ልጆች ጋር እንድንዋጋ አለቃችን ሁን አሉት።
7፤ ዮፍታሔም የገለዓድን ሽማግሌዎች። የጠላችሁኝ ከአባቴም ቤት ያሳደዳችሁኝ እናንተ አይደላችሁምን? አሁን በተጨነቃችሁ ጊዜ ለምን ወደ እኔ መጣችሁ? አላቸው።
8፤ የገለዓድም ሽማግሌዎች ዮፍታሔን። ከእኛ ጋር እንድትወጣ፥ ከአሞንም ልጆች ጋር እንድትዋጋ፥ ስለዚህ አሁን ወደ አንተ ተመልሰን መጣን፤ በገለዓድም ሰዎች ሁሉ ላይ አለቃችን ትሆናለህ አሉት።
9፤ ዮፍታሔም የገለዓድን ሽማግሌዎች። ከአሞን ልጆች ጋር ለመዋጋት ወደ አገሬ ብትመልሱኝ፥ እግዚአብሔርም በእጄ አሳልፎ ቢሰጣቸው፥ እኔ አለቃችሁ እሆናለሁን? አላቸው።
10፤ የገለዓድም ሽማግሌዎች ዮፍታሔን። እግዚአብሔር በመካከላችን ምስክር ይሁን፤ በእርግጥ እንደ ቃልህ እናደርጋለን አሉት።
11፤ ዮፍታሔም ከገለዓድ ሽማግሌዎች ጋር ሄደ፥ ሕዝቡም በላያቸው ራስና አለቃ አደረጉት፤ ዮፍታሔም ቃሉን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት በምጽጳ ተናገረ።
12፤ ዮፍታሔም ወደ አሞን ልጆች ንጉሥ። አገሬን ለመውጋት ወደ እኔ የምትመጣ አንተ ከእኔ ጋር ምን አለህ? ብሎ መልክተኞችን ላከ።
13፤ የአሞንም ልጆች ንጉሥ የዮፍታሔን መልክተኞች። እስራኤል ከግብፅ በወጣ ጊዜ ከአርኖን ጀምሮ እስከ ያቦቅና እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ምድሬን ስለ ወሰደ ነው፤ አሁንም በሰላም መልሱልኝ ብሎ መለሰላቸው።
14፤ ዮፍታሔም ወደ አሞን ልጆች ንጉሥ መልክተኞችን እንደ ገና ላከ፥
15፤ እንዲህም አለው። ዮፍታሔ እንዲህ ይላል። እስራኤል የሞዓብን ምድር የአሞንንም ልጆች ምድር አልወሰደም፤
16፤ ነገር ግን ከግብፅ በወጣ ጊዜ፥ እስራኤልም በምድረ በዳ በኩል ወደ ኤርትራ ባሕር በሄደ ጊዜ፥ ወደ ቃዴስም በደረሰ ጊዜ፥
17፤ እስራኤል ወደ ኤዶምያስ ንጉሥ። በምድርህ እንዳልፍ፥ እባክህ፥ ፍቀድልኝ ብሎ መልክተኞችን ላከ፤ የኤዶምያስም ንጉሥ አልሰማም። እንዲሁም ወደ ሞዓብ ንጉሥ ላከ፥ እርሱም አልፈቀደም።
18፤ እስራኤልም በቃዴስ ተቀመጠ። በምድረ በዳም በኩል ሄዱ፥ የኤዶምያስንና የሞዓብንም ምድር ዞሩ፤ ከሞዓብ ምድርም በምሥራቅ በኩል መጡ በአርኖንም ማዶ ሰፈሩ፤ አርኖንም የሞዓብ ድንበር ነበረና የሞዓብን ድንበር አላለፉም።
19፤ እስራኤልም ወደ አሞራዊው ወደ ሐሴቦን ንጉሥ ወደ ሴዎን መልክተኞችን ላከ፤ እስራኤልም። በምድርህ በኩል ወደ ስፍራችን፥ እባክህ፥ አሳልፈን አለው።
20፤ ሴዎንም እስራኤል በድንበሩ እንዲያልፍ አላመነውም ነበር፤ ነገር ግን ሴዎን ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰበ፥ በያሀጽም ሰፈረ፥ ከእስራኤልም ጋር ተዋጋ።
21፤ የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር ሴዎንና ሕዝቡን ሁሉ በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጠ፥ መቱአቸውም፤ እስራኤልም በዚያ ምድር ተቀምጠው የነበሩትን የአሞራውያንን ምድር ሁሉ ወረሰ።
22፤ ከአርኖንም እስከ ያቦቅ ድረስ ከምድረ በዳውም እስከ ዮርዳኖስ ድረስ የአሞራውያንን ምድር ሁሉ ወረሱ።
23፤ የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ከእስራኤል ፊት አሞራውያንን አስወገደ፤ አንተም ምድሩን ትወርሳለህን?
24፤ አምላክህ ካሞሽ የሚሰጥህን አትወርስምን? እኛም አምላካችን እግዚአብሔር ከፊታችን ያስወጣቸውን የእነርሱን ምድር እንወርሳለን።
25፤ ወይስ ከሞዓብ ንጉሥ ከሴፎር ልጅ ከባላቅ አንተ ትሻላለህን? በውኑ እርሱ እስራኤልን ከቶ ተጣላውን? ወይስ ተዋጋውን?
26፤ እስራኤልም በሐሴቦንና በመንደሮችዋ፥ በአሮዔርና በመንደሮችዋ፥ በአርኖንም አቅራቢያ ባሉት ከተሞች ሁሉ ሦስት መቶ ዓመት ተቀምጦ በነበረ ጊዜ፥ በዚያ ዘመን ስለ ምን አልወሰዳችኋቸውም ነበር?
27፤ እኔ አልበደልሁህም፥ አንተ ግን ከእኔ ጋር እየተዋጋህ በድለኸኛል፤ ፈራጁ እግዚአብሔር በእስራኤል ልጆችና በአሞን ልጆች መካከል ዛሬ ይፍረድ።
28፤ ነገር ግን ዮፍታሔ የላከበትን ቃል የአሞን ልጆች ንጉሥ አልሰማም።
29፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በዮፍታሔ ላይ መጣ፤ እርሱም ገለዓድንና ምናሴን አለፈ፥ በገለዓድም ያለውን ምጽጳን አለፈ፥ ከምጽጳም ወደ አሞን ልጆች አለፈ።
30፤ ዮፍታሔም። በእውነት የአሞንን ልጆች በእጄ አሳልፈህ ብትሰጠኝ፥
31፤ ከአሞን ልጆች ዘንድ በደኅና በተመለስሁ ጊዜ፥ ሊገናኘኝ ከቤቴ ደጅ የሚወጣው ማንኛውም ለእግዚአብሔር ይሆናል፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አቀርበዋለሁ ብሎ ለእግዚአብሔር ስእለት ተሳለ።
32፤ ዮፍታሔም ሊዋጋቸው ወደ አሞን ልጆች አለፈ፥ እግዚአብሔርም በእጁ አሳልፎ ሰጣቸው።
33፤ ከአሮዔርም እስከ ሚኒትና እስከ አቤልክራሚም ድረስ ሀያ ከተሞችን በታላቅ አገዳደል መታቸው። የአሞንም ልጆች በእስራኤል ልጆች ፊት ተዋረዱ።
34፤ ዮፍታሄም ወደ ቤቱ ወደ ምጽጳ መጣ፥ እነሆም ልጁ ከበሮ ይዛ እየዘፈነች ልትገናኘው ወጣች፤ ለእርሱም አንዲት ብቻ ነበረች፤ ከእርስዋም በቀር ወንድ ወይም ሴት ሌላ ልጅ አልነበረውም።
35፤ እርስዋንም ባየ ጊዜ ልብሱን ቀድዶ። አወይ ልጄ ሆይ! ወደ እግዚአብሔር አፌን ከፍቻለሁና፥ ከዚያውም እመለስ ዘንድ አልችልምና በጣም አዋረድሽኝ አስጨነቅሽኝም አላት።
36፤ እርስዋም። አባቴ ሆይ፥ አፍህን ለእግዚአብሔር ከከፈትህ፥ እግዚአብሔር በጠላቶችህ በአሞን ልጆች ላይ ተበቅሎልሃልና በአፍህ እንደ ተናገርህ አድርግብኝ አለችው።
37፤ አባትዋንም። ይህ ነገር ይደረግልኝ፤ ከዚህ ሄጄ በተራሮች ላይ እንድወጣና እንድወርድ፥ ከባልንጀሮቼም ጋር ለድንግልናዬ እንዳለቅስ ሁለት ወር አሰናብተኝ አለችው።
38፤ እርሱም። ሂጂ አለ። ሁለት ወርም አሰናበታት፤ ከባልንጀሮችዋም ጋር ሄደች፥ በተራሮችም ላይ ለድንግልናዋ አለቀሰች።
39፤ ሁለትም ወር ከተፈጸመ በኋላ ወደ አባትዋ ተመለሰች፥ እንደ ተሳለውም ስእለት አደረገባት፤ እርስዋም ወንድ አላወቀችም ነበር።
40፤ የእስራኤልም ሴቶች ልጆች በዓመት በዓመቱ እየሄዱ የገለዓዳዊውን የዮፍታሔን ልጅ በዓመት አራት ቀን ሙሾ እንዲያወጡ በእስራኤል ዘንድ ልማድ ሆነ።
ምዕራፍ 12

1፤ የኤፍሬም ሰዎች ተሰበሰቡ፥ ወደ ጻፎንም ተሻግረው ዮፍታሔን። ከአሞን ልጆች ጋር ለመዋጋት ስታልፍ ከአንተ ጋር እንድንሄድ ስለ ምን አልጠራኸንም? ቤትህን በአንተ ላይ በእሳት እናቃጥለዋለን አሉት።
2፤ ዮፍታሔም። ከአሞን ልጆች ጋር ለእኔና ለሕዝቤ ጽኑ ጠብ ነበረን፤ በጠራኋችሁም ጊዜ ከእጃቸው አላዳናችሁኝም።
3፤ እንዳላዳናችሁኝም ባየሁ ጊዜ ነፍሴን በእጄ አድርጌ በአሞን ልጆች ላይ አለፍሁ፥ እግዚአብሔርም በእጄ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ለምንስ ዛሬ ልትወጉኝ ወደ እኔ መጣችሁ? አላቸው።
4፤ ዮፍታሔም የገለዓድን ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፥ ከኤፍሬምም ጋር ተዋጋ፤ ኤፍሬምም። ገለዓዳውያን ሆይ፥ እናንተ በኤፍሬምና በምናሴ መካከል የተቀመጣችሁት ከኤፍሬም ሸሽታችሁ ነው ስላሉ የገለዓድ ሰዎች ኤፍሬምን መቱ።
5፤ ገለዓዳውያንም ኤፍሬም የሚያልፍበትን የዮርዳኖስን መሻገሪያ ያዙባቸው፤ የሸሸም የኤፍሬም ሰው። ልለፍ ባለ ጊዜ፥ የገለዓድ ሰዎች። አንተ ኤፍሬማዊ ነህን? አሉት፤ እርሱም። አይደለሁም ቢል፥
6፤ እነርሱ። አሁን ሺቦሌት በል አሉት፤ እርሱም አጥርቶ መናገር አልቻለምና። ሲቦሌት አለ፤ ይዘውም በዮርዳኖስ መሻገሪያ አረዱት፤ በዚያም ጊዜ ከኤፍሬም አርባ ሁለት ሺህ ሰዎች ወደቁ።
7፤ ዮፍታሔም በእስራኤል ላይ ስድስት ዓመት ፈረደ። ገለዓዳዊውም ዮፍታሔ ሞተ፥ ከገለዓድም ከተሞች በአንዲቱ ተቀበረ።
8፤ ከእርሱም በኋላ የቤተ ልሔሙ ኢብጻን በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆነ።
9፤ ሠላሳም ወንዶች ልጆችና ሠላሳ ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ ሠላሳ ሴቶች ልጆቹንም ወደ ውጭ አገር ዳረ፤ ለወንዶች ልጆቹም ከውጭ አገር ሴቶች ልጆችን አመጣ። በእስራኤልም ላይ ሰባት ዓመት ፈረደ።
10፤ ኢብጻንም ሞተ፥ በቤተ ልሔምም ተቀበረ።
11፤ ከእርሱም በኋላ ዛብሎናዊው ኤሎም በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆነ፤ እርሱም በእስራኤል ላይ አሥር ዓመት ፈረደ።
12፤ ዛብሎናዊውም ኤሎም ሞተ፥ በዛብሎንም ምድር ባለችው በኤሎም ተቀበረ።
13፤ ከእርሱም በኋላ የጲርዓቶናዊው የሂሌል ልጅ ዓብዶን በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆነ።
14፤ አርባም ልጆች ሠላሳም የልጅ ልጆች ነበሩት፤ በሰባም አህያ ግልገሎች ላይ ይቀመጡ ነበር። በእስራኤልም ላይ ስምንት ዓመት ፈረደ።
15፤ የጲርዓቶናዊውም የሂሌል ልጅ ዓብዶን ሞተ፥ በተራራማውም በአማሌቃውያን ምድር በኤፍሬም ባለችው በጲርዓቶን ተቀበረ። a
ምዕራፍ 13

1፤ የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ፤ እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያን እጅ አርባ ዓመት አሳልፎ ሰጣቸው።
2፤ ከዳን ወገን የሆነ ማኑሄ የሚባል አንድ የጾርዓ ሰው ነበረ፤ ሚስቱም መካን ነበረች፥ ልጅም አልወለደችም።
3፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ለሴቲቱ ተገልጦ እንዲህ አላት። እነሆ፥ አንቺ መካን ነሽ፥ ልጅም አልወለድሽም፤ ነገር ግን ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ።
4፤ አሁንም ተጠንቀቂ፤ የወይን ጠጅን የሚያሰክርም ነገር አትጠጪ፥ ርኩስም ነገር አትብዪ።
5፤ እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ልጁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ይሆናልና በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት፤ እርሱም እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ማዳን ይጀምራል።
6፤ ሴቲቱም ወደ ባልዋ መጥታ። አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ እኔ መጣ፥ መልኩም እንደ እግዚአብሔር መልአክ እጅግ የሚያስደነግጥ ነበረ፤ ከወዴትም እንደ መጣ አልጠየቅሁትም፥ እርሱም ስሙን አልነገረኝም።
7፤ እርሱም። እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ልጁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ እስኪሞት ድረስ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ይሆናልና አሁን የወይን ጠጅ የሚያሰክርም ነገር አትጠጪ፥ ርኩስም ነገር አትብዪ አለኝ ብላ ተናገረች።
8፤ ማኑሄም። ጌታ ሆይ፥ የላክኸው የእግዚአብሔር ሰው፥ እባክህ፥ እንደ ገና ወደ እኛ ይምጣ፤ ለሚወለደውም ልጅ ምን እንድናደርግ ያስገንዝበን ብሎ ወደ እግዚአብሔር ለመነ።
9፤ እግዚአብሔርም የማኑሄን ድምፅ ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ እንደ ገና ለሴቲቱ በእርሻ ውስጥ ተቀምጣ ሳለች ተገለጠላት፤ ባልዋ ማኑሄ ግን ከእርስዋ ጋር አልነበረም።
10፤ ሴቲቱም ፈጥና ሮጠች ለባልዋም። እነሆ፥ በቀደም ዕለት ወደ እኔ የመጣው ሰው ደግሞ ተገለጠልኝ ብላ ነገረችው።
11፤ ማኑሄም ተነሥቶ ሚስቱን ተከተለ፥ ወደ ሰውዮውም መጥቶ። ከዚህች ሴት ጋር የተነጋገርህ አንተ ነህን? አለው። እርሱም። እኔ ነኝ አለ።
12፤ ማኑሄም። ቃልህ በደረሰ ጊዜ የልጁ ሥርዓት ምንድር ነው? የምናደርግለትስ ምንድር ነው? አለው።
13፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ማኑሄን። ሴቲቱ ከነገርኋፅት ሁሉ ትጠንቀቅ።
14፤ ከወይንም ከሚወጣው ሁሉ አትብላ፥ የወይን ጠጅንም የሚያሰክርንም ነገር አትጠጣ፥ ርኩስም ነገር ሁሉ አትብላ፤ ያዘዝኋትን ሁሉ ትጠብቅ አለው።
15፤ ማኑሄም የእግዚአብሔርን መልአክ። የፍየል ጠቦት እስክናዘጋጅልህ ድረስ፥ እባክህ፥ ቆይ አለው።
16፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ማኑሄን። አንተ የግድ ብትለኝ መብልህን አልበላም፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ማዘጋጀት ብትወድድ ለእግዚአብሔር አቅርበው አለው። ማኑሄም የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን አላወቀም ነበር።
17፤ ማኑሄም የእግዚአብሔርን መልአክ። ነገርህ በደረሰ ጊዜ እንድናከብርህ ስምህ ማን ነው? አለው።
18፤ የእግዚአብሔርም መልአክ። ስሜ ድንቅ ነውና ለምን ትጠይቃለህ? አለው።
19፤ ማኑሄም የፍየሉን ጠቦትና የእህሉን ቍርባን ወስዶ በድንጋይ ላይ ለእግዚአብሔር አቀረበው። መልአኩም ተአምራት አደረገ፥ ማኑሄና ሚስቱም ይመለከቱ ነበር።
20፤ ነበልባሉም ከመሠዊያው ላይ ወደ ሰማይ በወጣ ጊዜ የእግዚአብሔርም መልአክ በመሠዊያው ነበልባል ውስጥ ዐረገ፤ ማኑሄና ሚስቱም ተመለከቱ፥ በምድርም በግምባራቸው ተደፉ።
21፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ዳግመኛ ላማኑሄና ለሚስቱ አልተገለጠም፤ ያን ጊዜም ማኑሄ የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን አወቀ።
22፤ ማኑሄም ሚስቱን። እግዚአብሔርን አይተናልና ሞት እንሞታለን አላት።
23፤ ሚስቱም። እግዚአብሔርስ ሊገድለን ቢወድድ ኖሮ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን ከእጃችን ባልተቀበለን፥ ይህንም ነገር ሁሉ ባላሳየን፥ እንዲህ ያለ ነገርም በዚህ ጊዜ ባላስታወቀን ነበር አለችው።
24፤ ሴቲቱም ወንድ ልጅ ወለደች፥ ስሙንም ሶምሶን ብላ ጠራችው፤ ልጁም አደገ እግዚአብሔርም ባረከው።
25፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ባለው በዳን ሰፈር ውስጥ ሊያነቃቃው ጀመረ።
ምዕራፍ 14

1፤ ሶምሶንም ወደ ተምና ወረደ፥ በተምናም ከፍልስጥኤማውያን ልጆች አንዲት ሴት አየ።
2፤ ወጥቶም ለአባቱና ለእናቱ። በተምና ከፍልስጥኤማውያን ልጆች አንዲት ሴት አይቻለሁ፤ አሁንም እርስዋን አጋቡኝ አላቸው።
3፤ አባቱና እናቱም። ካልተገረዙት ከፍልስጥኤማውያን ሚስት ለማግባት ትሄድ ዘንድ ከወንድሞችህ ሴቶች ልጆች ከሕዝቤም ሁሉ መካከል ሴት የለምን? አሉት። ሶምሶንም አባቱን። ለዓይኔ እጅግ ደስ አሰኝታኛለችና እርስዋን አጋባኝ አለው።
4፤ እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያን ላይ ምክንያት ይፈልግ ነበርና ነገሩ ከእርሱ ሆነ፤ አባቱና እናቱ ግን አላወቁም። በዚያን ጊዜም ፍልስጥኤማውያን በእስራኤል ላይ ገዦች ነበሩ።
5፤ ሶምሶንም አባቱና እናቱም ወደ ተምና ወረዱ፥ በተምናም ወዳለው ወደ ወይኑ ስፍራ መጡ፤ እነሆም፥ የአንበሳ ደቦል እያገሣ ወደ እርሱ ደረሰ።
6፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ በኃይል ወረደ፤ ጠቦትን እንደሚቆራርጥ በእጁ ምንም ሳይኖር ቈራረጠው፤ ያደረገውንም ለአባቱና ለእናቱ አልነገረም።
7፤ ወርዶም ከሴቲቱ ጋር ተነጋገረ፤ እጅግም ደስ አሰኘችው።
8፤ ከጥቂትም ቀን በኋላ ሊያገባት ተመለሰ፥ የአንበሳውንም ሬሳ ያይ ዘንድ ከመንገድ ፈቀቅ አለ፤ እነሆም፥ በአንበሳው ሬሳ ውስጥ ንብ ሰፍሮበት ነበር፥ ማርም ነበረበት።
9፤ በእጁም ወስዶ መንገድ ለመንገድ እየበላ ሄደ፤ ወደ አባቱና ወደ እናቱ መጣ፥ ማሩንም ሰጣቸው፥ እነርሱም በሉ፤ ማሩንም ከአንበሳው ሬሳ ውስጥ እንደ ወሰደ አልነገራቸውም።
10፤ አባቱም ወደ ሴቲቱ ወረደ፤ ጎበዞችም እንዲህ ያደርጉ ነበርና ሶምሶን በዚያ በዓል አደረገ።
11፤ ባዩትም ጊዜ ከእርሱ ጋር ይሆኑ ዘንድ ሌሎች ሠላሳ ሰዎች ሰጡት።
12፤ ሶምሶንም። እንቆቅልሽ ልስጣችሁ፤ በሰባቱም በበዓሉ ቀኖች ውስጥ ፈትታችሁ ብትነግሩኝ፥ ሠላሳ የበፍታ ቀሚስና ሠላሳ ልውጥ ልብስ እሰጣችኋለሁ፤
13፤ መፍታትም ባትችሉ ሠላሳ የበፍታ ቀሚስና ሠላሳ ልውጥ ልብስ ትሰጡኛላችሁ አላቸው። እነርሱም። እንድንሰማው እንቆቅልሽህን ንገረን አሉት።
14፤ እርሱም። ከበላተኛው ውስጥ መብል ወጣ፥ ከብርቱም ውስጥ ጥፍጥ ወጣ አላቸው። ሦስት ቀንም እንቈቅልሹን መተርጎም አልቻሉም።
15፤ በአራተኛውም ቀን የሶምሶንን ሚስት። እንቈቅልሹን እንዲነግረን ባልሽን ሸንግዪው፥ አለዚያም እንቺንና የአባትሽን ቤት በእሳት እናቃጥላለን፤ ወደዚህ ጠራችሁን ልትገፉን ነውን? አሉአት።
16፤ የሶምሶንም ሚስት በፊቱ እያለቀሰች። በእውነት ጠልተኸኛል፥ ከቶም አትወድደኝም፤ ለሕዝቤ ልጆች እንቈቅልሽ ሰጥተሃቸዋልና ትርጓሜውንም አልነገርኸኝም አለችው። እርሱም። እነሆ፥ ለአባቴና ለእናቴ አልነገርኋቸውም፥ ለአንቺ እነግርሻለሁን? አላት።
17፤ ሰባቱንም የበዓል ቀን በፊቱ አለቀሰች፤ እርስዋም ነዝንዛዋለችና በሰባተኛው ቀን ነገራት። ትርጓሜውንም ለሕዝብዋ ልጆች ነገረች።
18፤ በሰባተኛውም ቀን ፀሐይ ሳትገባ የከተማይቱ ሰዎች። ከማር የሚጣፍጥ ምንድር ነው? ከአንበሳስ የሚበረታ ማን ነው? አሉት። እርሱም። በጥጃዬ ባላረሳችሁ የእንቈቅልሼን ትርጓሜ ባላወቃችሁ ነበር አላቸው።
19፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በላዩ በኃይል ወረደ፤ ወደ አስቀሎናም ወረደ፥ ከዚያም ሠላሳ ሰዎችን ገደለ፥ ልብሳቸውንም ወስዶ እንቈቅልሹን ለፈቱት ሰዎች ሰጠ። ቍጣውም ነደደ፥ ወደ አባቱም ቤት ወጣ።
20፤ የሶምሶን ሚስት ግን ከተባበሩት ከሚዜዎቹ ለአንደኛው ሆነች። a
ምዕራፍ 15

1፤ ከዚህም በኋላ በስንዴ መከር ጊዜ ሶምሶን የፍየል ጠቦት ይዞ ሚስቱን ሊጠይቅ ሄደና። ወደ ጫጉላ ቤት ወደ ሚስቴ ልግባ አለ፤ አባትዋ ግን እንዳይገባ ከለከለው።
2፤ አባትዋም። ፈጽመህ የጠላሃት መስሎኝ ለሚዜህ አጋባኋፅት፤ ታናሽ እኅትዋ ከርስዋ ይልቅ የተዋበች አይደለችምን? እባክህ፥ በእርስዋ ፋንታ አግባት አለው።
3፤ ሶምሶንም። ከእንግዲህ ወዲህ በፍልስጥኤማውያን ላይ ክፉ ባደርግ እኔ ንጹሕ ነኝ አላቸው።
4፤ ሶምሶንም ሄዶ ሦስት መቶ ቀበሮች ያዘ፤ ችቦም ወስዶ ሁለት ሁለቱንም ቀበሮዎች በጅራታቸው አሰረ፥ በሁለቱም ጅራቶች ማካከል አንድ ችቦ አደረገ።
5፤ ችቦውንም አንድዶ በቆመው በፍልስጥኤማውያን እህል መካከል ሰደዳቸው፤ ነዶውንም የቆመውንም እህል ወይኑንም ወይራውንም አቃጠለ።
6፤ ፍልስጥኤማውያንም። ይህን ያደረገው ማን ነው? አሉ። እነርሱም። ሚስቱን ወስዶ ለሚዜው አጋብቶበታልና የተምናዊው አማች ሶምሶን ነው አሉ። ፍልስጥኤማያንም ወጥተው ሴቲቱንና አባትዋን በእሳት አቃጠሉ።
7፤ ሶምሶንም። እናንተ እንዲሁ ብታደርጉ እኔ እበቀላችኋለሁ፥ ከዚያም በኋላ ዐርፋለሁ አላቸው።
8፤ እርሱም ጭን ጭናቸውን ብሎ በታላቅ አገዳደል መታቸው፤ ወርዶም በኤጣም ዓለት ባለው ዋሻ ውስጥ ተቀመጠ።
9፤ ፍልስጥኤማውያንም ወጡ፥ በይሁዳም ሰፈሩ፥ በሌሒ ላይም ተበታትነው ተቀመጡ።
10፤ የይሁዳም ሰዎች። በእኛ ላይ የወጣችሁት ለምንድር ነው? አሉ። እነርሱም። ሶምሶንን ልናስር፥ እንዳደረገብንም ልናደርግበት መጥተናል አሉ።
11፤ ከይሁዳም ሰዎች ሦስት ሺህ የሚያህሉ በኤጣም ዓለት ወዳለው ዋሻ ወርደው ሶምሶንን። ገዦቻችን ፍልስጥኤማውያን እንደ ሆኑ አታውቅምን? ያደረግህብን ይህ ምንድር ነው? አሉት። እርሱም። እንዳደረጉብኝ እንዲሁ አደረግሁባቸው አላቸው።
12፤ እነርሱም። አስረን በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፈን ልንሰጥህ መጥተናል አሉት። ሶምሶንም። እናንተ እንዳትገድሉኝ ማሉልኝ አላቸው።
13፤ እነርሱም። አስረን በእጃቸው አሳልፈን እንሰጥሃለን እንጂ አንገድልህም ብለው ተናገሩት። በሁለትም አዲስ ገመድ አስረው ከዓለቱ ውስጥ አወጡት።
14፤ ወደ ሌሒ በመጣ ጊዜም ፍልስጥኤማውያን እልል እያሉ ተገናኙት። የእግዚአብሔርም መንፈስ በኃይል ወረደበት፤ ክንዱም የታሰረበት ገመድ በእሳት እንደ ተበላ እንደ ተልባ እግር ፈትል ሆነ፥ ማሰሪያዎቹም ከእጁ ወደቁ።
15፤ አዲስም የአህያ መንጋጋ አገኘ፥ እጁንም ዘርግቶ ወሰደው፥ በእርሱም አንድ ሺህ ሰው ገደለ።
16፤ ሶምሶንም። በአህያ መንጋጋ ክምር በክምር ላይ አድርጌአቸዋለሁ፤ በአህያ መንጋጋ አንድ ሺህ ሰው ገድያለሁ አለ።
17፤ መናገሩንም በፈጸመ ጊዜ መንጋጋውን ከእጁ ጣለ፤ የዚያንም ስፍራ ስም ራማትሌሒ ብሎ ጠራው።
18፤ እርሱም እጅግ ተጠምቶ ነበርና። አንተ ይህችን ታላቅ ማዳን በባሪያህ እጅ ሰጥተሃል፤ አሁንም በጥም እሞታለሁ፥ ባልተገረዙትም እጅ እወድቃለሁ ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።
19፤ እግዚአብሔርም በሌሒ ያለውን አዘቅት ሰነጠቀ፥ ከእርሱም ውኃ ወጣ፤ እርሱም ጠጣ፥ ነፍሱም ተመለሰች፥ ተጠናከረም። ስለዚህም የዚያን ቦታ ስም ዓይንሀቆሬ ብሎ ጠራው፤ ይህም እስከ ዛሬ ድረስ በሌሒ አለ።
20፤ በፍልስጥኤማውያንም ዘመን በእስራኤል ላይ ሀያ ዓመት ፈረደ።
ምዕራፍ 16

1፤ ሶምሶንም ወደ ጋዛ ሄደ፥ በዚያም ጋለሞታ ሴት አይቶ ወደ እርስዋ ገባ።
2፤ የጋዛ ሰዎችም ሶምሶን ወደ ከተማ ውስጥ እንደ ገባ ሰሙ፥ ከበቡትም፥ ሌሊቱንም ሁሉ በከተማይቱ በር ሸመቁበት። ማለዳ እንገድለዋለን ብለውም ሌሊቱን ሁሉ በዝምታ ተቀመጡ።
3፤ ሶምሶንም እስከ እኩለ ሌሊት ተኛ፤ እኩለ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ተነሥቶ የከተማይቱን በር መዝጊያ ያዘ፥ ከሁለቱ መቃኖችና ከመወርወሪያውም ጋር ነቀለው፥ በትከሻውም ላይ አደረገ፥ በኬብሮንም ፊት ወዳለው ተራራ ራስ ላይ ተሸክሞት ወጣ በዚያም ጣለው።
4፤ ከዚህም በኋላ በሶሬቅ ሸለቆ የነበረች ደሊላ የተባለች አንዲት ሴትን ወደደ።
5፤ የፍልስጥኤማውያንም መኳንንት ወደ እርስዋ ወጥተው። እርሱን ሸንግለሽ በእርሱ ያለ ታላቅ ኃይል በምን እንደ ሆነ፥ እኛስ እርሱን ለማዋረድ እናስረው ዘንድ የምናሸንፈው በምን እንደ ሆነ እወቂ፤ እኛም እያንዳንዳችን ሺህ አንድ መቶ ብር ሺህ አንድ መቶ ብር እንሰጥሻለን አሉአት።
6፤ ደሊላም ሶምሶንን። ታላቅ ኃይልህ በምን እንደ ሆነ፥ እንድትዋረድስ የምትታሰርበት ምን እንደ ሆነ፥ እባክህ፥ ንገረኝ አለችው።
7፤ ሶምሶንም። በሰባት ባልደረቀ በእርጥብ ጠፍር ቢያስሩኝ፥ እደክማለሁ እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ አላት።
8፤ የፍልስጥኤማውያንም መኳንንት ሰባት ያልደረቀ እርጥብ ጠፍር አመጡላት፥ በእርሱም አሰረችው።
9፤ በጓዳዋም ውስጥ ሰዎች ተደብቀው ነበር። እርስዋም። ሶምሶን ሆይ፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ አለችው። እርሱም የተልባ እግር ፈትል እሳት በሸተተው ጊዜ እንዲበጠስ ጠፍሩን በጣጠሰው፤ ኃይሉም በምን እንደ ሆነ አልታወቀም።
10፤ ደሊላም ሶምሶንን። እነሆ፥ አታለልኸኝ፥ የነገርኸኝም ሀሰት ነው፤ አሁንም የምትታሰርበት ምን እንደ ሆነ፥ እባክህ፥ ንገረኝ አለችው።
11፤ እርሱም። ሥራ ባልተሠራበት በአዲስ ገመድ ቢያስሩኝ፥ እደክማለሁ፥ እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ አላት።
12፤ ደሊላም አዲስ ገመድ ወስዳ በእርሱ አሰረችው፤ በጓዳዋም የተደበቁ ሰዎች ተቀምጠው ነበር። እርስዋም። ሶምሶን ሆይ፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ አለችው። ገመዱንም ከክንዱ እንደ ፈትል በጣጠሰው።
13፤ ደሊላም ሶምሶንን። እስከ አሁን ድረስ አታለልኸኝ፥ የነገርኸኝም ሐሰት ነው፤ የምትታሰርበት ምን እንደ ሆነ ንገረኝ አለችው። እርሱም። የራሴን ጠጕር ሰባቱን ጕንጕን ከድር ጋር ብትጐነጕኚው፥ በችካልም ብትቸክዪው፥ እደክማለሁ፥ እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ አላት።
14፤ ሶምሶንም በተኛ ጊዜ ደሊላ የራሱን ጠጕር ሰባቱን ጕንጕን ከድሩ ጋር ጐነጐነችው፥ በችካልም ቸከለችውና። ሶምሶን ሆይ፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ አለችው። ከእንቅልፉም ነቃ፥ ችካሉንም ከነቆንዳላው ድሩንም ነቀለ።
15፤ እርስዋም። አንተ። እወድድሻለሁ እንዴት ትለኛለህ፥ ልብህ ከእኔ ጋር አይደለም? ስታታልለኝ ይህ ሦስተኛ ጊዜህ ነው፥ ታላቅ ኃይልህም በምን እንደ ሆነ አልነገርኸኝም አለችው።
16፤ ዕለት ዕለትም በቃልዋ ነዘነዘችው አስቸገረችውም፥ ነፍሱም እስከ ሞት ድረስ ተጨነቀች።
17፤ እርሱም። ከእናቴ ማኅፀን ጀምሬ ለእግዚአብሔር የተለየሁ ነኝና በራሴ ላይ ምላጭ አልደረሰም፤ የራሴንም ጠጕር ብላጭ ኃይሌ ከእኔ ይሄዳል፥ እደክማለሁም፥ እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ ብሎ የልቡን ሁሉ ገለጠላት።
18፤ ደሊላም የልቡን ሁሉ እንደ ገለጠላት ባየች ጊዜ። የልቡን ሁሉ ገልጦልኛልና ይህን ጊዜ ደግሞ ኑ ብላ ላከችና የፍልስጥኤማውያንን መኳንንት ጠራች። የፍልስጥኤማውያን መኳንንትም ብሩን በእጃቸው ይዘው ወደ እርስዋ መጡ።
19፤ እርስዋም በጕልበትዋ ላይ አስተኛችው፤ አንድ ሰውም ጠራች፥ እርሱም ሰባቱን የራሱን ጕንጕን ላጨው። ልታዋርደውም ጀመረች፥ ኃይሉም ከእርሱ ሄደ።
20፤ እርስዋም። ሶምሶን ሆይ፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ አለችው። ከእንቅልፉም ነቅቶ። እወጣለሁ እንደ ወትሮውም ጊዜ አደርጋለሁ አለ። ነገር ግን እግዚአብሔር ከእርሱ እንደ ተለየው አላወቀም።
21፤ ፍልስጥኤማውያንም ይዘው ዓይኖቹን አወጡት፤ ወደ ጋዛም አምጥተው በናስ ሰንሰለት አሰሩት፤ በግዞትም ሆኖ እህል ይፈጭ ነበር።
22፤ የራሱም ጠጕር ከላጩት በኋላ ያድግ ጀመር።
23፤ የፍልስጥኤምም መኳንንት። አምላካችን ጠላታችንን ሶምሶንን በእጃችን አሳልፎ ሰጠን እያሉ ለአምላካቸው ለዳጎን ታላቅ መሥዋዕት ይሠዉ ዘንድ ደስም ይላቸው ዘንድ ተሰበሰቡ።
24፤ ሕዝቡም ሁሉ ባዩት ጊዜ። ምድራችንን ያጠፋውን፥ ከእኛም ብዙ ሰው የገደለውን ጠላታችንን አምላካችን በእጃችን አሳልፎ ሰጠን እያሉ አምላካቸውን አመሰገኑ።
25፤ ልባቸውንም ደስ ባለው ጊዜ። በፊታችን እንዲጫወት ሶምሶንን ጥሩት አሉ። ሶምሶንንም ከግዞት ቤት ጠሩት፥ በፊታቸውም ተጫወተ፤ ተዘባበቱበትም፥ በምሰሶና በምሰሶም መካከል አቆሙት።
26፤ ሶምሶንም እጁን የያዘውን ብላቴና። ቤቱን የደገፉትን ምሰሶች እጠጋባቸው ዘንድ፥ እባክህ፥ አስይዘኝ አለው።
27፤ በቤትም ውስጥ ወንዶችና ሴቶች ሞልተውበት ነበር፥ የፍልስጥኤምም መኳንንት ሁሉ በዚያ ነበሩ፤ በቤቱም ሰገነት ላይ ሶምሶን ሲጫወት የሚያዩ ሦስት ሺህ የሚያህሉ ወንዶችና ሴቶች ነበሩ።
28፤ ሶምሶንም። ስለ ሁለቱ ዓይኖቼ ፍልስጥኤማውያንን አሁን እንድበቀል፥ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ እባክህ፥ አስበኝ፤ አምላክ ሆይ፥ ይህን አንድ ጊዜ ብቻ፥ እባክህ፥ አበርታኝ ብሎ እግዚአብሔርን ጠራ።
29፤ ሶምሶንም ቤቱ ተደግፎባቸው የነበሩትን ሁለቱን መካከለኞች ምሰሶች ያዘ፤ አንዱን በቀኝ እጁ አንዱንም በግራ እጁ ይዞ ተጠጋባቸው።
30፤ ሶምሶንም። ከፍልስጥኤማውያን ጋር ልሙት አለ፤ ተጎንብሶም ምሰሶቹን በሙሉ ኅይሉ ገፋ፥ ቤቱም በውስጡ በነበሩት በመኳንንቱም በሕዝቡም ሁሉ ላይ ወደቀ፤ በሞቱም የገደላቸው ሙታን በሕይወት ሳለ ከገደላቸው በዙ።
31፤ ወንድሞቹም የአባቱ ቤተ ሰቦችም ሁሉ ወረዱ፥ ይዘውም አመጡት፤ በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ባለው በአባቱ በማኑሄ መቃብር ቀበሩት። እርሱም በእስራኤል ላይ ሀያ ዓመት ፈረደ። a
ምዕራፍ 17

1፤ በተራራማውም በኤፍሬም አገር ሚካ የተባለ አንድ ሰው ነበረ።
2፤ እናቱንም። ከአንቺ ዘንድ የተወሰደው፥ የረገምሽበትም፥ በጆሮዬም የተናገርሽበት አንድ ሺህ አንድ መቶ ብር፥ እነሆ፥ በእኔ ዘንድ አለ፤ እኔም ወስጄዋለሁ አላት። እናቱም። ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔር ይባርክህ አለችው።
3፤ አንዱን ሺህ አንዱን መቶ ብርም መለሰላት፤ እናቱም። ይህን ብር የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ምስል አድርጌ ከእጄ ስለ ልጄ ለእግዚአብሔር እቀድሰዋለሁ፤ አሁንም ለአንተ እመልሰዋለሁ አለች።
4፤ ለእናቱም ገንዘቡን በመለሰላት ጊዜ እናቱ ሁለቱን መቶ ብር ወስዳ ለአንጥረኛ ሰጠችው፥ እርሱም የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ምስል አደረገው። ያም በሚካ ቤት ነበረ።
5፤ ሰውዮውም ሚካ የአምላክ ቤት ነበረው፤ ኤፉድና ተራፊም አደረገ፥ ከልጆቹም አንዱን ቀደሰው፥ ካህንም ሆነለት።
6፤ በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም፤ ሰውም ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር።
7፤ በቤተ ልሔም ይሁዳም ከይሁዳ ወገን የሆነ አንድ ጕልማሳ ነበረ፥ እርሱም ሌዋዊ ነበረ፥ በዚያም ይቀመጥ ነበር።
8፤ ይህም ሰው የሚቀመጥበትን ስፍራ ለመሻት ከከተማው ከቤተ ልሔም ይሁዳ ወጣ፤ ሲሔድም ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም አገር ወደ ሚካ ቤት መጣ።
9፤ ሚካም። ከወዴት መጣህ? አለው። እርሱም። ከቤተ ልሔም ይሁዳ የሆንሁ ሌዋዊ ነኝ፤ የምቀመጥበትንም ስፍራ ለመሻት እሄዳለሁ አለው።
10፤ ሚካም። ከእኔ ዘንድ ተቀመጥ፥ አባትና ካህንም ሁነኝ፤ እኔም ልብሶችንና ምግብህን፥ በእየዓመቱም አሥር ብር እሰጥሃለሁ አለው። ሌዋዊውም ገባ።
11፤ ሌዋዊውም ከሰውዮው ጋር መቀመጥን ፈቀደ፤ ጕልማሳውም ከልጆቹ እንደ አንዱ ሆነለት።
12፤ ሚካም ሌዋዊውን ቀደሰ፥ ጕልማሳውም ካህኑ ሆነለት፥ በሚካም ቤት ነበረ።
13፤ ሚካም። ሌዋዊ ካህን ስለ ሆነልኝ እግዚአብሔር መልካም እንዲሠራልኝ አሁን አውቃለሁ አለ።
ምዕራፍ 18

1፤ በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም። እስከዚያም ቀን ድረስ ለዳን ነገድ በእስራኤል ነገዶች መካከል ርስት አልደረሳቸውም ነበርና በዚያ ዘመን የሚቀመጡባት ርስት ይሹ ነበር።
2፤ የዳንም ልጆች ከወገናቸው አምስት ጽኑዓን ሰዎች ምድሪቱን እንዲሰልሉና እንዲመረምሩ። ሂዱ ምድሪቱንም ሰልሉ ብለው ከጾርዓና ከኤሽታኦል ሰደዱ። እነዚያም ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም አገር ወደ ሚካ ቤት መጥተው በዚያ አደሩ።
3፤ በሚካ ቤት አጠገብም በነበሩ ጊዜ የሌዋዊውን የጕልማሳውን ድምፅ አወቁ፤ ወደ እርሱም ቀርበው። ወደዚህ ማን አመጣህ? በዚህስ የምታደርገው ምንድር ነው? በዚህስ ምን አለህ? አሉት።
4፤ እርሱም። ሚካ እንዲህ እንዲህ አደረገልኝ፥ ቀጠረኝም፥ እኔም ካህን ሆንሁለት አላቸው።
5፤ እነርሱም። የምንሄድበት መንገድ የቀና መሆኑን እናውቅ ዘንድ፥ እባክህ፥ እግዚአብሔርን ጠይቅልን አሉት።
6፤ እርሱም። የምትሄዱበት መንገድ በእግዚአብሔር ፊት ነውና በደኅና ሂዱ አላቸው።
7፤ አምስቱም ሰዎች ሄዱ ወደ ሌሳም መጡ፥ በውስጡም የነበሩትን ሕዝብ ተዘልለው አዩአቸው፥ አንደ ሲዶናውያንም ልማድ ጸጥ ብለው ተዘልለው ተቀምጠው ነበር፤ የሚያስቸግራቸውም የሚገዛቸውም አልነበረም፥ ከሲዶናውያንም ርቀው ከሰውም ሁሉ ተለይተው ለብቻቸው ይኖሩ ነበር።
8፤ ወደ ወንድሞቻቸውም ወደ ጾርዓና ወደ ኤሽታኦል ተመለሱ፤ ወንድሞቻቸውም። ምን ወሬ ይዛችኋል? አሉአቸው።
9፤ እነርሱም ምድሪቱን እግጅ መልካም እንደ ሆነች አይተናልና ተነሡ፥ በእነርሱ ላይ እንውጣ፤ እናንተ ዝም ትላላችሁን? ትሄዱ ዘንድ ምድሪቱንም ለመውረስ ትገቡ ዘንድ ቸል አትበሉ።
10፤ በሄዳችሁ ጊዜ ተዘልለው ወደ ተቀመጡ ሕዝብ ትደርሳላችሁ፥ ምድሪቱም ሰፊ ናት፤ እግዚአብሔርም በምድር ካለው ነገር ሁሉ አንዳች የማይጎድልበትን ስፍራ በእጃችሁ ሰጥቶአል አሉ።
11፤ ከዳን ወገንም የጦር ዕቃ የታጠቁ ስድስት መቶ ሰዎች ከዚያ ከጾርዓና ከኤሽታኦል ተነሥተው ሄዱ።
12፤ ወጥተውም በይሁዳ ባለችው በቂርያትይዓሪም ሰፈሩ፤ ስለዚህም የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ የዳን ሰፈር ተብሎ ተጠራ፤ እነሆም፥ ከቂርያትይዓሪም በስተ ኋላ ነው።
13፤ ከዚያም ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም አገር አለፉ፤ ወደ ሚካም ቤት መጡ።
14፤ የሌሳን ምድር ሊሰልሉ ሄደው የነበሩት አምስቱ ሰዎችም ወንድሞቻቸውን። በእነዚህ ቤቶች ውስጥ ኤፉድና ተራፊም፥ የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ምስልም እንዳሉ ታውቃላችሁን? አሁንም የምታደርጉትን ምከሩ ብለው ተናገሩአቸው።
15፤ ከመንገዱም ፈቀቅ ብለው ጕልማሳው ሌዋዊ ወደ ነበረበት ወደ ሚካ ቤት መጡ፥ ደኅንነቱንም ጠየቁት።
16፤ የጦር ዕቃ የታጠቁት፥ ከዳን ልጆችም የሆኑት ስድስቱ መቶ ሰዎች በደጃፉ አጠገብ ቆመው ነበር።
17፤ ምድሪቱንም ሊሰልሉ ሄደው የነበሩት አምስቱ ሰዎች ወጥተው ወደዚያ ገቡ፤ የተቀረጸውን ምስል ኤፉዱንም ተራፊሙንም ቀልጦ የተሠራውን ምስልም ወሰዱ፤ ካህኑም የጦር ዕቃ ከታጠቁት ከስድስት መቶ ሰዎች ጋር በደጃፉ አጠገብ ቆሞ ነበር።
18፤ እነዚህም ወደ ሚካ ቤት ገብተው የተቀረጸውን ምስል ኤፉዱንም ተራፊሙንም ቀልጦ የተሠራውን ምስልም በወሰዱ ጊዜ፥ ካህኑ። ምን ታደርጋላችሁ? አላቸው።
19፤ እነርሱም። ዝም በል፥ እጅህንም በአፍህ ላይ ጫን፥ ከእኛም ጋር መጥተህ አባትና ካህን ሁንልን፤ ለአንድ ሰው ቤት ካህን መሆን ወይስ በእስራኤል ዘንድ ለነገድና ለወገን ካህን መሆን ማናቸው ይሻልሃል? አሉት።
20፤ ካህኑም በልቡ ደስ አለው፥ ኤፉዱንም ተራፊሙንም የተቀረጸውንም ምስል ወሰደ፥ በሕዝቡም መካከል ሄደ።
21፤ እነርሱም ዞረው ሄዱ፥ ሕፃናቶችንና ከብቶችን ዕቃዎችንም በፊታቸው አደረጉ።
22፤ ከሚካም ቤት በራቁ ጊዜ የሚካ ጐረቤቶች ተሰበሰቡ፥ የዳንም ልጆች ተከትለው ደረሱባቸው።
23፤ ወደ ዳንም ልጆች ጮኹ፥ የዳንም ልጆች ፊታቸውን መልሰው ሚካን። የምትጮኸው ምን ሆነህ ነው? አሉት።
24፤ እርሱም። የሠራኋቸውን አማልክቴን ካህኑንም ይዛችሁ ሄዳችኋል፤ ሌላ ምን አለኝ? እናንተስ። ምን ሆነሃል እንዴት ትሉኛላችሁ? አለ።
25፤ የዳንም ልጆች። የተቈጡ ሰዎች እንዳይወድቁብህ ነፍስህም የቤተ ሰቦችህም ነፍስ እንዳይጠፋብህ፥ ድምፅህን በእኛ መካከል አታሰማ አሉት።
26፤ የዳንም ልጆች መንገዳቸውን ሄዱ፤ ሚካም ከእርሱ እንደ በረቱ ባየ ጊዜ ተመልሶ ወደ ቤቱ ሄደ።
27፤ እነርሱም ሚካ የሠራውን ጣዖትና ለእርሱ የነበረውን ካህን ይዘው ወደ ሌሳ፥ ጸጥ ብሎ ተዘልሎም ወደ ተቀመጠው ሕዝብ፥ መጡ፤ በሰይፍም ስለት መቱአቸው፥ ከተማይቱንም በእሳት አቃጠሉአት።
28፤ ከተማይቱ ከሲዶና ራቅ ያለች ነበረችና፥ እነርሱም ከሌሎች ሰዎች ተለይተው ብቻቸውን ይኖሩ ነበርና የሚታደግ አልነበራቸውም። ሌሳም በቤትሮዖብ አጠገብ ባለች ሸለቆ ውስጥ ነበረች። ከተማይቱንም ሠርተው ተቀመጡባት።
29፤ ከተማይቱንም ከእስራኤል በተወለደው በአባታቸው በዳን ስም ዳን ብለው ጠሩአት፤ የከተማይቱም ስም አስቀድሞ ሌሳ ነበረ።
30፤ የዳንም ልጆች የተቀረጸውን ምስል ለራሳቸው አቆሙ፤ የሙሴም ልጅ የጌርሳም ልጅ ዮናታን፥ እርሱና ልጆቹ የአገሩ ሰዎች እስከሚማረኩበት ቀን ድረስ የዳን ነገድ ካህናት ነበሩ።
31፤ ሚካም ያደረገውን የተቀረጸ ምስል የእግዚአብሔር ቤት በሴሎ ባለበት ዘመን ሁሉ አቆሙ። a
ምዕራፍ 19

1፤ በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ በሌለበት ጊዜ በተራራማው በኤፍሬም አገር ማዶ የተቀመጠ ሌዋዊ ነበረ፤ ከቤተ ልሔምም ይሁዳ ቁባት አገባ።
2፤ ቁባቱም አመነዘረችበት፥ ትታውም ወደ አባትዋ ቤት ወደ ቤተ ልሔም ይሁዳ ሄደች፤ በዚያም አራት ወር ተቀመጠች።
3፤ ባልዋም ተነሣ፥ ከእርስዋም ዕርቅ ሽቶ ወደ ቤቱ ሊመልሳት ፍለጋዋን ተከትሎ ሄደ፤ ከእርሱም ጋር አንድ አሽከር ሁለትም አህዮች ነበሩ። እርስዋም ወደ አባትዋ ቤት አገባችው፤ አባትዋም ባየው ጊዜ ደስ ብሎት ተገናኘው።
4፤ የብላቴናይቱም አባት አማቱ የግድ አለ፥ በቤቱም ሦስት ቀን ተቀመጠ፤ በሉም፥ ጠጡም፥ በዚያም አደሩ።
5፤ በአራተኛውም ቀን ማልደው ተነሡ፥ እርሱም ለመሄድ ተነሣ፤ የብላቴናይቱም አባት አማቹን። ሰውነትህን በቍራሽ እንጀራ አበርታ፥ ከዚያም በኋላ ትሄዳለህ አለው።
6፤ ተቀመጡም በአንድ ላይም በሉ ጠጡም፤ የብላቴናይቱም አባት ሰውዮውን። ዛሬ ደግሞ ከዚህ ለማደር፥ እባክህ፥ ፍቀድ፥ ልብህንም ደስ ይበለው አለው።
7፤ ሰውዮውም ሊሄድ ተነሣ፤ አማቱ ግን የግድ አለው፥ ዳግመኛም በዚያ አደረ።
8፤ በአምስተኛውም ቀን ለመሄድ ማልዶ ተነሣ፤ የብላቴናይቱም አባት። እባክህ፥ ሰውነትህን አበርታ፥ ቀኑም እስኪዋገድ ድረስ ቆይ አለው። ሁለቱም በሉ።
9፤ ሰውዮውም ከቁባቱና ከአሽከሩ ጋር ለመሄድ በተነሣ ጊዜ የብላቴናይቱ አባት አማቱ። እነሆ፥ ቀኑ ተዋግዶአል፤ በዚህ እደሩ፤ እነሆ፥ ቀኑ ለማለፍ ተዋግዶአል፤ ልባችሁ ደስ እንዲለው በዚህ እደሩ፤ ነገም ወደ ቤታችሁ እንድትደርሱ ማልዳችሁ መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ አለው።
10፤ ሰውዮው ግን በዚያ ሌሊት ለማደር አልፈቀደም፥ ተነሥቶም ሄደ፥ ኢየሩሳሌምም ወደ ተባለች ወደ ኢያቡስ ፊት ለፊት ደረሰ። ከእርሱም ጋር ሁለት የተጫኑ አህዮች ነበሩ፥ ቁባቱም ከእርሱ ጋር ነበረች።
11፤ ወደ ኢያቡስም በደረሱ ጊዜ መሸባቸው፥ አሽከሩም ጌታውን። ና፥ ወደዚህ ወደ ኢያቡሳውያን ከተማ፥ እባክህ፥ እናቅና፥ በእርስዋም እንደር አለው።
12፤ ጌታውም። ከእስራኤል ወገን ወዳልሆነች ወደ እንግዳ ከተማ አንገባም፤ እኛ ወደ ጊብዓ እንለፍ አለው።
13፤ አሽከሩንም። ና፥ ከእነዚህ ስፍራ ወደ አንዱ እንቅረብ፤ በጊብዓ ወይም በራማ እንደር አለው።
14፤ መንገዳቸውንም ይዘው ሄዱ፤ የብንያምም ነገድ በምትሆነው በጊብዓ አጠገብ ሳሉ ፀሐይ ገባችባቸው።
15፤ በጊብዓም ገብተው ያድሩ ዘንድ ወደዚያ አቀኑ። በገባም ጊዜ ሊያሳድራቸው ማንም በቤቱ አልተቀበላቸውምና በከተማው አደባባይ ተቀመጡ።
16፤ እነሆም፥ አንድ ሽማግሌ ከእርሻው ሥራ ወደ ማታ መጣ፤ ይህም ሰው ከተራራማው ከኤፍሬም አገር ነበረ በጊብዓም በእንግድነት ተቀምጦ ነበር፤ የዚያ አገር ሰዎች ግን ብንያማውያን ነበሩ።
17፤ ዓይኑንም አንሥቶ መንገደኛውን በከተማው አደባባይ አየ፤ ሽማግሌውም። ወዴት ትሄዳለህ? ከወዴትስ መጣህ? አለው።
18፤ እርሱም። እኛ ከቤተ ልሔም ይሁዳ ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም አገር ማዶ እናልፋለን፤ እኔ ከዚያ ነኝ፥ ወደ ቤተ ልሔምም ይሁዳ ሄጄ ነበር፥ አሁንም ወደ እግዚአብሔር ቤት እሄዳለሁ፤ በቤቱም የሚያሳድረኝ አጣሁ፤
19፤ ለአህዮቻችን ገለባና ገፈራ አለን፤ ለእኔና ለገረድህ ከባሪያዎችህም ጋር ላለው አሽከር እንጀራና የወይን ጠጅ አለን፤ አንዳችም አላጣንም አለው።
20፤ ሽማግሌውም። ሰላም ከአንተ ጋር ይሁን፤ የምትሻውንም ሁሉ እኔ እሰጥሃለሁ፤ በአደባባይ ግን አትደር አለው።
21፤ ወደ ቤቱም አስገባው፥ ለአህዮቹም ገፈራ ጣለላቸው፤ እግራቸውንም ታጠቡ፥ በሉም ጠጡም።
22፤ ሰውነታቸውንም ደስ ባሰኙ ጊዜ ወስላቶች የሆኑ የከተማው ሰዎች ቤቱን ከበቡ በሩንም ይደበድቡ ነበር፤ ባለቤቱንም ሽማግሌውን። ወደ ቤትህ የገባውን ሰው እንድንደርስበት አውጣልን አሉት።
23፤ ባለቤቱም ሽማግሌው ወደ እነርሱ ወጥቶ። ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህን ክፉ ነገር፥ እባካችሁ፥ አታድርጉ፤ ይህ ሰው ወደ ቤቴ ገብቶአልና እንደዚህ ያለ ኃጢአት አትሥሩ።
24፤ ድንግል ልጄና የእርሱም ቁባት፥ እነሆ፥ አሉ፥ አሁንም አወጣቸዋለሁ፤ አዋርዱአቸው እንደ ወደዳችሁም አድርጉባቸው፤ ነገር ግን በዚህ ሰው ላይ እንደዚህ ያለ ኃጢአት አታድርጉ አላቸው።
25፤ ሰዎቹ ግን ነገሩን አልሰሙም፤ ሰውዮውም ቁባቱን ይዞ አወጣላቸው፤ ደረሱባትም፥ ሌሊቱንም ሁሉ እስኪነጋ ድረስ አመነዘሩባት፤ ጎህ በቀደደም ጊዜ ለቀቁአት።
26፤ ሴቲቱም ማለዳ መጣች፥ ጌታዋም ባለበት በሰውዮው ቤት ደጅ ወድቃ እስኪነጋ ድረስ በዚያ ቀረች።
27፤ ጌታዋም ማለዳ ተነሣ የቤቱንም ደጅ ከፈተ፥ መንገዱንም ለመሄድ ወጣ፤ እነሆም ቁባቲቱ ሴት በቤቱ ደጃፍ ወድቃ፥ እጅዋም በመድረክ ላይ ነበረ።
28፤ እርሱም። ተነሺ፥ እንሂድ አላት፤ እርስዋ ግን ሞታ ነበርና አልመለሰችም፤ በዚያን ጊዜ በአህያው ላይ ጫናት፥ ተነሥቶም ወደ ስፍራው ሄደ።
29፤ ወደ ቤቱም በመጣ ጊዜ ካራ አነሣ፥ ቁባቱንም ይዞ ከአጥንቶችዋ መለያያ ላይ ለአሥራ ሁለት ቈራርጦ ወደ እስራኤል አገር ሁሉ ሰደደ።
30፤ ያየም ሁሉ። የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ከወጡ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እንዲህ ያለ ነገር ከቶ አልተደረገም፥ አልታየምም፤ አስቡት፥ በዚህም ተመካከሩ፥ ተነጋገሩም ይባባል ነበር።
ምዕራፍ 20

1፤ የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ወጡ፥ ማኅበሩም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ፥ ከገለዓድም አገር ሰዎች ጋር፥ ወደ እግዚአብሔር ወደ ምጽጳ እንደ አንድ ሰው ሆነው ተሰበሰቡ።
2 ፤ ከእስራኤልም ነገድ ሁሉ የሆኑ የሕዝብ ሁሉ አለቆች ሰይፍ በሚመዝዙ በቍጥርም አራት መቶ ሺህ እግረኞች በሆኑ በእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ ቆሙ።
3 ፤ የብንያምም ልጆች የእስራኤል ልጆች ወደ ምጽጳ እንደ ወጡ ሰሙ። የእስራኤልም ልጆች። ይህ ክፉ ነገር እንደምን እንደ ተደረገ ንገሩን አሉ።
4 ፤ የተገደለችውም ሴት ባል ሌዋዊው እንዲህ ብሎ መለሰላቸው። እኔና ቁባቴ በዚያ ለማደር ወደ ብንያም አገር ወደ ጊብዓ መጣን።
5 ፤ የጊብዓም ሰዎች ተነሡብኝ፥ ቤቱንም በሌሊት በእኛ ላይ ከበቡት፤ ሊገድሉኝም ወደዱ፥ በቁባቴም አጥብቀው አመነዘሩባት፥ እርስዋም ሞተች።
6 ፤ እኔም ቁባቴን ይዤ ቈራረኋጥጥኋት በእስራኤልም ዘንድ እንደዚህ ያለ ኃጢአትና ስንፍና ስለ ተሠራ ወደ እስራኤል ርስት አገር ሁሉ ሰደድሁ።
7 ፤ እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ ሁላችሁ፥ ምክራችሁንና እዝናታችሁን በዚህ ስጡ።
8 ፤ ሕዝቡም ሁሉ እንደ አንድ ሰው ተነሥተው አሉ። ከእኛ ዘንድ ማንም ወደ ድንኳኑ አይሄድም፥ ወደ ቤቱም አይመለስም።
9 ፤ ነገር ግን በጊብዓ ላይ የምናደርገው ነገር ይህ ነው፤ በዕጣ እንወጣባታለን።
10 ፤ ወደ ብንያም ጊብዓ በመጡ ጊዜ እርስዋ በእስራኤል ላይ እንዳደረገችው እንደ ስንፍናዋ እንዲያደርጉ፥ ለሕዝብ ስንቅ የሚይዙ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ከመቶው አሥር ሰው ከሺሁም መቶ ሰው ከአሥሩም ሺህ አንድ ሺህ ሰው እንወስዳለን።
11 ፤ የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ እንደ አንድ ሰው ሆነው በከተማይቱ ላይ ተሰበሰቡ።
12
13 ፤ የእስራኤልም ነገዶች። በእናንተ መካከል የተደረገ ይህ ክፉ ነገር ምንድር ነው? አሁንም እንድንገድላቸው ከእስራኤልም ክፋትን እንድናርቅ በጊብዓ ውስጥ ያሉትን ምናምንቴዎቹን ሰዎች አውጥታችሁ ስጡን ብለው ወደ ብንያም ነገድ ሁሉ
14 ፤ የብንያምም ልጆች ከእስራኤል ልጆች ጋር ሊዋጉ ከየከተማው ወደ ጊብዓ ተሰበሰቡ።
15 ፤ በዚያም ቀን ከየከተማው የመጡ የብንያም ልጆች ተቈጠሩ፤ ቍጥራቸውም ከጊብዓ ሰዎች ሌላ ሀያ ስድስት ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎች ነበሩ፤ ከጊብዓም ሰባት መቶ የተመረጡ ሰዎች ተቈጠሩ።
16 ፤ ከእነዚያም ሕዝብ ሁሉ ሰባት መቶ የተመረጡ ግራኝ ሰዎች ነበሩ፤ እነዚህም ሁሉ ድንጋይ ይወነጭፉ ነበር፤ አንዲት ጠጕርስ እንኳ አይስቱም።
17 ፤ ከብንያምም ልጆች ሌላ የእስራኤል ሰዎች አራት መቶ ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎች ተቈጠሩ፤ እነዚህም ሁሉ ሰልፈኞች ነበሩ።
18 ፤ የእስራኤልም ልጆች ተነሥተው ወደ ቤቴል ወጡ፥ እግዚአብሔርንም። የብንያምን ልጆች ለመውጋት አስቀድሞ ማን ይውጣልን? ብለው ጠየቁት፤ እግዚአብሔርም። ይሁዳ ይቅደም አለ።
19 ፤ የእስራኤልም ልጆች በማለዳ ተነሥተው በጊብዓ ፊት ሰፈሩ።
20 ፤ የእስራኤልም ሰዎች ከብንያም ጋር ሊዋጉ ወጡ፤ የእስራኤልም ሰዎች በጊብዓ አጠገብ በእነርሱ ላይ ተሰልፈው ቆሙ።
21 ፤ የብንያምም ልጆች ከጊብዓ ወጡ፥ በዚያም ቀን ከእስራኤላውያን ሀያ ሁለት ሺህ ሰዎች ገደሉ።
22 ፤ ሕዝቡም፥ የእስራኤል ሰዎች፥ ተበራቱ፥ በፊተኛውም ቀን በተሰለፉበት ስፍራ ደግመው ተሰለፉ።
23 ፤ የእስራኤልም ልጆች ወጥተው በእግዚአብሔር ፊት እስከ ማታ ድረስ አለቀሱ፤ እግዚአብሔርንም። ከወንድሞቻችን ከብንያም ልጆች ጋር ለመዋጋት ዳግመኛ እንቀርባለን? ብለው ጠየቁ። እግዚአብሔርም። በእነርሱ ላይ ውጡ አለ።
24 ፤ በሁለተኛውም ቀን የእስራኤል ልጆች ከብንያም ልጆች ጋር ሊዋጉ ቀረቡ።
25 ፤ በሁለተኛውም ቀን ብንያም ከጊብዓ በእነርሱ ላይ ወጣ፥ ከእስራኤልም ልጆች ደግሞ አሥራ ስምንት ሺህ ሰዎች ገደሉ፤ እነዚህም ሁሉ ሰይፍ የሚመዝዙ ነበሩ።
26 ፤ የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ሕዝቡም ሁሉ ወጥተው ወደ ቤቴል መጡ፥ አለቀሱም፥ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ተቀመጡ፥ በዚያም ቀን እስከ ማታ ድረስ ጾሙ፤ በእግዚአብሔር ፊት የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕት አቀረቡ።
27
28 ፤ በዚያም ዘመን የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት በዚያ ነበረና፥ በዚያም ዘመን የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ በፊቱ ይቆም ነበርና የእስራኤል ልጆች እግዚአብሔርን። ከወንድሞቻችን ከብንያም ልጆች ጋር ለመዋጋት ዳግመኛ እንውጣን
29 ፤ እስራኤልም በጊብዓ ዙሪያ የተደበቁ ሰዎች አኖሩባት።
30 ፤ በሦስተኛውም ቀን የእስራኤል ልጆች ወደ ብንያም ልጆች ወጡ፥ በጊብዓም ፊት እንደ ቀድሞው ጊዜ ተሰለፉ።
31 ፤ የብንያምም ልጆች በሕዝቡ ላይ ወጡ፥ ከከተማይቱም ተሳቡ፤ እንደ ቀድሞውም ጊዜ፥ በአውራዎቹ መንገዶች፥ አንደኛው ወደ ቤቴል ሁለተኛውም ወደ ጊብዓ ሜዳ በሚወስዱት መንገዶች ላይ፥ ሕዝቡን ይመቱ ይገድሉም ጀመር፤
32 ፤ የብንያምም ልጆች። እንደ ቀድሞው በፊታችን ተመቱ አሉ። የእስራኤል ልጆች ግን። እንሽሽ፥ ከከተማም ወደ መንገድ እንሳባቸው አሉ።
33 ፤ የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ከስፍራቸው ተነሥተው በበኣልታማር ተሰለፉ። ከእስራኤልም ተደብቀው የነበሩት ከስፍራቸው ከጊብዓ ሜዳ ወጡ።
34 ፤ ከእስራኤልም ሁሉ የተመረጡ አሥር ሺህ ሰዎች ወደ ጊብዓ አንጻር መጡ፤ ሰልፍም በርትቶ ነበር፤ መከራም እንዲያገኛቸው አላወቁም ነበር።
35 ፤ እግዚአብሔርም ብንያምን በእስራኤል ፊት መታ፤ በዚያም ቀን የእስራኤል ልጆች ከብንያም ሀያ አምስት ሺህ አንድ መቶ ሰዎች ገደሉ፤ እነዚህ ሁሉ ሰይፍ የሚመዝዙ ነበሩ።
36 ፤ የብንያም ልጆች እንደ ተመቱ አዩ፤ የእስራኤል ልጆች ግን በጊብዓ ላይ ባኖሩት ድብቅ ጦር ታምነዋልና ለብንያም ስፍራ ለቀቁላቸው።
37 ፤ ተደብቀውም የነበሩት ፈጥነው ወደ ጊብዓ ሮጡ፤ ተደብቀውም የነበሩት መጥተው ከተማውን ሁሉ በሰይፍ ስለት መቱ።
38 ፤ የተደበቁትም ሰዎች ከከተማው ብዙ ጢስ እንደ ደመና እንዲያስነሡ በእስራኤል ልጆችና በተደበቁት ሰዎች መካከል ምልክት ተደርጎ ነበር።
39 ፤ የእስራኤልም ሰዎች ከሰልፉ አፈገፈጉ፤ ብንያማውያንም። እንደ ቀድሞው ሰልፍ በፊታችን ተመትተዋል እያሉ ከእስራኤል ሰዎች ሠላሳ የሚያህሉ ሰዎች መምታትና መግደል ጀመሩ።
40 ፤ ምልክቱ በጢሱ ዓምድ ከከተማው ሊወጣ በጀመረ ጊዜ ብንያማውያን ወደ ኋላቸው ተመለከቱ፥ እነሆም፥ የሞላ ከተማው ጥፋት ወደ ሰማይ ወጣ።
41 ፤ የእስራኤልም ሰዎች ተመለሱ፥ የብንያምም ሰዎች ክፉ ነገር እንደ ደረሰባቸው አይተዋልና ደነገጡ።
42 ፤ ከእስራኤልም ሰዎች ፊት ጀርባቸውን መልሰው ወደ ምድረ በዳ መንገድ ሸሹ፤ ሰልፉም ተከታትሎ ደረሰባቸው፤ ከየከተማውም የወጡት በመካከላቸው ገደሉአቸው።
43 ፤ ብንያማውያንንም ከበቡ፥ በምሥራቅም በኩል እስካለው እስከ ጊብዓ አንጻር ድረስ አሳደዱአቸው፥ በመኑሔም አጠፉአቸው።
44 ፤ ከብንያምም አሥራ ስምንት ሺህ ሰው ሞተ፤ እነዚህ ሁሉ ጽኑዓን ነበሩ።
45 ፤ ከእነርሱም የተረፉት ተመልሰው ወደ ምድረ በዳ ወደ ሬሞን ዓለት ሸሹ፥ ከእነርሱም በየመንገዱ ላይ አምስት ሺህ ሰው ለቀሙ፤ ወደ ጊድአምም አሳደዱአቸው፥ ከእነርሱም ሁለት ሺህ ሰዎችን ገደሉ።
46 ፤ እንዲሁም በዚያ ቀን ከብንያም የሞቱት ሀያ አምስት ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎች ነበሩ፤ እነዚህ ሁሉ ጽኑዓን ነበሩ።
47 ፤ ስድስቱም መቶ ሰዎች ተመልሰው ወደ ምድረ በዳ ወደ ሬሞን ዓለት ሸሹ፥ በሬሞን ዓለት አራት ወር ተቀመጡ።
48 ፤ የእስራኤልም ሰዎች በብንያም ልጆች ላይ ዳግመኛ ተመለሱ፤ ሞላውን ከተማ ከብቱንም ያገኙትንም ሁሉ በሰይፍ ስለት መቱ፤ ያገኙትንም ከተማ ሁሉ በእሳት አቃጠሉ።
ምዕራፍ 21

1፤ የእስራኤልም ሰዎች። ከእኛ ማንም ሰው ልጁን ለብንያም ልጆች አያጋባ ብለው በምጽጳ ተማምለው ነበር።
2፤ ሕዝቡም ወደ ቤቴል መጥተው በዚያ በእግዚአብሔር ፊት እስከ ማታ ድረስ ተቀመጡ፥ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው ጽኑ ልቅሶ አለቀሱ።
3፤ እነርሱም። አቤቱ፥ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ ዛሬ ከእስራኤል አንድ ነገድ መታጣቱ፥ ስለ ምን ይህ በእስራኤል ላይ ሆነ? አሉ።
4፤ በነጋውም ሕዝቡ ማልደው ተነሡ፥ በዚያም መሠዊያ ሠሩ፥ የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕትንም አቀረቡ።
5፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ወደ ምጽጳ ስላልወጣ ሰው። እርሱ ፈጽሞ ይገደል ብለው ታላቅ መሐላ ምለው ነበርና። ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ወደ ጉባኤ ወደ እግዚአብሔር ያልወጣ ማን ነው? አሉ።
6፤ የእስራኤልም ልጆች ስለ ወንድሞቻቸው ስለ ብንያም ልጆች ተጸጽተው። ዛሬ ከእስራኤል አንድ ነገድ ጠፍቶአል።
7፤ እኛ ልጆቻችንን እንዳንድርላቸው በእግዚአብሔር ምለናልና የተረፉት ሚስቶችን እንዲያገኙ ምን እናድርግ? አሉ።
8፤ እነርሱም። ከእስራኤል ነገድ ወደ እግዚአብሔር ወደ ምጽጳ ያልወጣ ማን ነው? አሉ። እነሆም፥ ከኢያቢስ ገለዓድ ወደ ሰፈሩ ወደ ጉባኤ ማንም አልወጣም ነበር።
9፤ ሕዝቡም በተቈጠሩ ጊዜ፥ እነሆ፥ በኢያቢስ ገለዓድ የሚኖር ሰው አልተገኘም።
10፤ ማኅበሩም ወደዚያ አሥራ ሁለት ሺህ ኃያላን ሰዎች ሰድደው። ሂዱ በኢያቢስ ገለዓድም ያሉትን ሰዎች ከሴቶችና ከሕፃናት ጋር በሰይፍ ስለት ግደሉ።
11፤ የምታደርጉትም ይህ ነው፤ ወንዱን ሁሉ፥ ከወንድ ጋር የተኛችይቱንም ሴት ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉ ብለው አዘዙአቸው።
12፤ ወንድ ያላወቁ አራት መቶ ቈነጃጅት ደናግሎች በኢያቢስ ገለዓድ በሚኖሩ መካከል አገኙ፤ በከነዓንም አገር ወዳለችው ወደ ሴሎ ወደ ሰፈሩ አመጡአቸው።
13፤ ማኅበሩም ሁሉ በሬሞን ዓለት ወዳሉት ወደ ብንያም ልጆች መልክተኞችን ላኩ፥ በዕርቅ ቃልም ተናገሩአቸው።
14፤ በዚያም ጊዜ የብንያም ልጆች ተመለሱ፤ ከኢያቢስ ገለዓድም ሴቶች ያዳኑአቸውን ሴቶች አገቡአቸው። ነገር ግን የሚበቁ ሴቶች አላገኙም።
15፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ነገድ ውስጥ ስብራት ስላደረገ ሕዝቡ ስለ ብንያም ተጸጸቱ።
16፤ የማኅበሩ ሽማግሌዎች። ከብንያም ሴቶች ጠፍተዋልና የቀሩት ሰዎች ሚስት እንዲያገኙ ምን እናደርጋለን? አሉ።
17፤ ደግሞም። ከእስራኤል አንድ ነገድ እንዳይደመሰስ ከብንያም ላመለጡት ርስት ይኑር።
18፤ የእስራኤልም ልጆች። ልጁን ለብንያም የሚድር ርጉም ይሁን ብለው ምለዋልና እኛ ልጆቻችንን ለእነርሱ ማጋባት አይሆንልንም አሉ።
19፤ እነርሱም። እነሆ፥ በቤቴል በሰሜን በኩል፥ ከቤቴልም ወደ ሴኬም በሚወስደው መንገድ በምሥራቅ በኩል፥ በለቦና በደቡብ በኩል ባለችው በሴሎ የእግዚአብሔር በዓል በየዓመቱ አለ አሉ።
20፤ የብንያምንም ልጆች እንዲህ ብለው አዘዙአቸው። ሂዱ በወይኑ ስፍራ ተደበቁ፤
21፤ ተመልከቱም፥ እነሆም፥ የሴሎ ሴቶች ልጆች አታሞ ይዘው ለዘፈን ሲወጡ ከወይኑ ስፍራ ውጡ፥ ከሴሎም ሴቶች ልጆች ለየራሳችሁ ሚስት ንጠቁ፥ ወደ ብንያም ምድርም ሂዱ።
22፤ አባቶቻቸውና ወንድሞቻቸውም ሊጣሉአችሁ ወደ እኛ በመጡ ጊዜ። ስለ እኛ ማሩአቸው፤ እኛ ሚስት ለያንዳንዳቸው በሰልፍ አልወሰድንላቸውምና፥ እናንተም በደል ይሆንባችሁ ስለ ነበረ አላጋባችኋቸውምና፥ እንላችኋለን።
23፤ የብንያምም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፥ በቍጥራቸውም መጠን ከተነጠቁት ዘፋኞች ሚስት ወሰዱ፤ ወደ ርስታቸውም ተመልሰው ሄዱ፥ ከተሞችንም ሠርተው ተቀመጡባቸው።
24፤ በዚያን ጊዜም የእስራኤል ልጆች ከዚያ ተነሡ፥ እያንዳንዱም ወደ ነገዱና ወደ ወገኑ ሄደ፤ ሰውም ሁሉ ከዚያ ወደ ርስቱ ተመለሰ።
25፤ በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም፤ ሰው ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር።