መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22


ምዕራፍ 1

1፤ ንጉሡ ዳዊትም ሸመገለ ዕድሜውም በዛ፤ ልብስም ደረቡለት፥ ነገር ግን አይሞቀውም ነበር።
2፤ ባሪያዎቹም። ለጌታችን ለንጉሡ ድንግል ትፈለጋለች፤ በንጉሡም ፊት ቆማ ታገልግለው፥ በጌታችንም በንጉሡ ብብት ተኝታ ታሙቀው አሉት።
3፤ በእስራኤልም አገር ሁሉ የተዋበች ቈንጆ ፈለጉ፤ ሱነማይቱን አቢሳንም አገኙ፥ ወደ ንጉሡም ይዘዋት መጡ።
4፤ ቈንጆይቱም እጅግ ውብ ነበረች፤ ንጉሡንም ትረዳውና ታገለግለው ነበር፥ ንጉሡ ግን አያውቃትም ነበር።
5፤ የአጊትም ልጅ አዶንያስ። ንጉሥ እሆናለሁ ብሎ ተነሣ፤ ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን በፊቱም የሚሮጡ አምሳ ሰዎች አዘጋጀ።
6፤ አባቱም ከቶ በሕይወቱ ሳለ። እንዲህ ለምን ታደርጋለህ? ብሎ አልተቈጣውም ነበር፤ እርሱ ደግሞ እጅግ ያማረ ሰው ነበረ፤ ከአቤሴሎምም በኋላ ተወልዶ ነበር።
7፤ ሴራውም ከጽሩያ ልጅ ከኢዮአብና ከካህኑ ከአብያታር ጋር ነበረ፥ እነርሱም አዶንያስን ተከትለው ይረዱት ነበር።
8፤ ነገር ግን ካህኑ ሳዶቅና የዮዳሄ ልጅ በናያስ ነቢዩም ናታን ሳሚም ሬሲም የዳዊትም ኃያላን ከአዶንያስ ጋር አልነበሩም።
9፤ አዶንያስም በጎችንና በሬዎችን ፍሪዳዎችንም በዓይንሮጌል አጠገብ ባለችው በዞሔሌት ድንጋይ ዘንድ ሠዋ፤ የንጉሡንም ልጆች ወንድሞቹን ሁሉ፥ የንጉሡንም ባሪያዎች፥ የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ጠራ።
10፤ ነገር ግን ነቢዩን ናታንን፥ በናያስንም፥ ኃያላኑንም፥ ወንድሙንም ሰሎሞንን አልጠራም።
11፤ ናታንም የሰሎሞንን እናት ቤርሳቤህን እንዲህ ብሎ ተናገራት። ጌታችን ዳዊት ሳያውቅ የአጊት ልጅ አዶንያስ እንደ ነገሠ አልሰማሽምን?
12፤ አሁንም ነዪ፥ የልጅሽን የሰሎሞንን ነፍስና የአንቺን ነፍስ እንድታድኝ እመክርሻለሁ።
13፤ ሄደሽ ወደ ንጉሡ ወደ ዳዊት ግቢና። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ለእኔ ለባሪያህ። ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፥ በዙፋኔም ይቀመጣል ብለህ አልማልህልኝምን? ስለ ምንስ አዶንያስ ይነግሣል? በዪው።
14፤ እነሆ፥ አንቺ በዚያ ለንጉሥ ስትነግሪ እኔ ከአንቺ በኋላ እገባለሁ፥ ቃልሽንም አጸናለሁ።
15፤ ቤርሳቤህም ወደ ንጉሡ ወደ እልፍኝ ገባች፤ ንጉሡም እጅግ ሸምግሎ ነበር፥ ሱነማይቱም አቢሳ ታገለግለው ነበር።
16፤ ቤርሳቤህም አጐንብሳ ለንጉሡ እጅ ነሣች፤ ንጉሡም። ምን ትፈልጊያለሽ? አለ።
17፤ እርስዋም አለችው። ጌታዬ ሆይ፥ አንተ ለባሪያህ። ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፥ በዙፋኔም ይቀመጣል ብለህ በአምላክህ በእግዚአብሔር ምለህልኛል፤
18፤ አሁንም፥ እነሆ፥ አዶንያስ መንገሡ ነው፤ አንተም ጌታዬ ንጉሥ ይህን አታውቅም፤
19፤ እርሱም ብዙ በሬዎችንና ፍሪዳዎችን በጎችንም ሠውቶአል፥ የንጉሡንም ልጆች ሁሉ፥ ካህኑንም አብያታርን፥ የሠራዊቱንም አለቃ ኢዮአብን ጠርቶአል፤ ባሪያህን ሰሎሞንን ግን አልጠራውም።
20፤ አሁንም፥ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በኋላ በጌታዬ በንጉሥ ዙፋን ላይ የሚቀመጠውን ትነግራቸው ዘንድ የእስራኤል ሁሉ ዓይን ይመለከትሃል።
21፤ ይህ ባይሆን፥ ጌታዬ ከአባቶችህ ጋር ባንቀላፋህ ጊዜ እኔና ልጄ ሰሎሞን እንደ ኃጢአተኞች እንቈጠራለን።
22፤ እነሆም፥ ለንጉሡ ስትናገር ነቢዩ ናታን ገባ።
23፤ ለንጉሡም። እነሆ፥ ነቢዩ ናታን መጥቶአል ብለው ነገሩት፤ እርሱም ወደ ንጉሡ ፊት በገባ ጊዜ በግምባሩ በምድር ላይ ተደፍቶ ለንጉሡ እጅ ነሣ።
24፤ ናታንም አለ። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ አንተ። ከእኔ በኋላ አዶንያስ ይነግሣል፥ በዙፋኔም ላይ ይቀመጣል ብለሃልን?
25፤ እርሱ ዛሬ ወርዶ ብዙ በሬዎችንና ፍሪዳዎችን በጎችንም ሠውቶአል፥ የንጉሡንም ልጆች ሁሉ፥ የሠራዊትንም አለቃ ኢዮአብን፥ ካህኑንም አብያታርን ጠርቶአል፤ እነሆም፥ በፊቱ እየበሉና እየጠጡ። አዶንያስ ሺህ ዓመት ይንገሥ ይላሉ።
26፤ ነገር ግን እኔን ባሪያህን፥ ካህኑንም ሳዶቅን፥ የዮዳሄንም ልጅ በናያስን፥ ባሪያህንም ሰሎሞንን አልጠራም።
27፤ በውኑ ይህ ነገር ከጌታዬ ከንጉሡ የተደረገ ነውን? ለባሪያህም ከአንተ በኋላ በጌታዬ በንጉሡ ዙፋን ላይ የሚቀመጠውን አልነገርህምን?
28፤ ንጉሡም ዳዊት። ቤርሳቤህን ጥሩልኝ ብሎ መለሰ። ወደ ንጉሡም ገባች፥ በንጉሡም ፊት ቆመች።
29፤ ንጉሡም። ነፍሴን ከመከራ ሁሉ ያዳነኝ ሕያው እግዚአብሔርን!
30፤ በእውነት። ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፥ በእኔም ፋንታ በዙፋኔ ላይ ይቀመጣል ብዬ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር እንደ ማልሁልሽ፥ እንዲሁ ዛሬ በእውነት አደርጋለሁ ብሎ ማለ።
31፤ ቤርሳቤህም በግምባርዋ በምድር ላይ ተደፍታ ለንጉሡ እጅ ነሣችና። ጌታዬ ንጉሥ ዳዊት ለዘላለም በሕይወት ይኑር አለች።
32፤ ንጉሡም ዳዊት። ካህኑን ሳዶቅንና ነቢዩን ናታንን የዮዳሄንም ልጅ በናያስን ጥሩልኝ አለ። ወደ ንጉሡም ፊት ገቡ።
33፤ ንጉሡም አላቸው። የጌታችሁን ባሪያዎች ይዛችሁ ሂዱ፥ ልጄንም ሰሎሞንን በበቅሎዬ ላይ አስቀምጡት፥ ወደ ግዮንም አውርዱት፤
34፤ በዚያም ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርገው ይቅቡት፤ ቀንደ መለከትም ነፍታችሁ። ሰሎሞን ሺህ ዓመት ይንገሥ በሉ።
35፤ በኋላውም ተከትላችሁ ውጡ፤ እርሱም መጥቶ በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ፥ በእኔም ፋንታ ይንገሥ፤ በእስራኤልና በይሁዳም ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ አዝዣለሁ።
36፤ የዮዳሄም ልጅ በናያስ መልሶ ለንጉሡ አለ፥ ያበጅ ያድርግ፤ የጌታዬም የንጉሥ አምላክ ይህን ይናገር።
37፤ እግዚአብሔር ከጌታዬ ከንጉሥ ጋር እንደ ነበረ እንዲሁ ከሰሎሞን ጋር ይሁን፥ ዙፋኑንም ከጌታዬ ከንጉሡ ዳዊት ዙፋን የበለጠ ያድርግ።
38፤ ካህኑም ሳዶቅና ነቢዩ ናታን የዮዳሄም ልጅ በናያስ ከሊታውያንና ፈሊታውያንም ወረዱ፥ ሰሎሞንንም በንጉሡ በዳዊት በቅሎ ላይ አስቀምጠው ወደ ግዮን አመጡት።
39፤ ካህኑም ሳዶቅ ከድንኳኑ የቅብዓቱን ቀንድ ወስዶ ሰሎሞንን ቀባ፤ ቀንደ መለከትም ነፉ፤ ሕዝቡም ሁሉ። ሰሎሞን ሺህ ዓመት ይንገሥ አሉ።
40፤ ሕዝቡም ሁሉ እርሱን ተከትለው ወጡ፥ ሕዝቡም ዘፈን ይዘፍኑ ነበር፥ በታላቅም ደስታ ደስ አላቸው፤ ከጩኸታቸውም የተነሣ ምድር ተናወጠች።
41፤ አዶንያስና እርሱም የጠራቸው ሁሉ መብሉና መጠጡ ተፈጽሞ ሳለ ሰሙ፤ ኢዮአብም የቀንደ መለከት ጽምፅ በሰማ ጊዜ። ይህ በከተማ ውስጥ ያለ የሽብር ድምፅ ምንድር ነው? አለ።
42፤ እርሱም ይህን ሲናገር የካህኑ የአብያታር ልጅ ዮናታን መጣ፤ አዶንያስም። አንተ መልካም ሰው ነህና፥ መልካም ታወራልናለህና ግባ አለ።
43፤ ዮናታንም ለአዶንያስ እንዲህ ብሎ መለሰ። በእውነት ጌታችን ንጉሥ ዳዊት ሰሎሞንን አነገሠው።
44፤ ንጉሡም ከእርሱ ጋር ካሁኑን ሳዶቅንና ነቢዩን ናታንን የዮዳሄንም ልጅ በናያስን ከሊታውያንንና ፈሊታውያንንም ሰደደ፥ በንጉሡም በቅሎ ላይ አስቀመጡት።
45፤ ካህኑም ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በግዮን ንጉሥ አድርገው ቀቡት፤ ከዚያም ደስ ብሎአቸው ወጡ፥ ከተማይቱም አስተጋባች፤ የሰማችሁትም ድምፅ ይህ ነው።
46፤ ደግሞም ሰሎሞን በመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦአል።
47፤ የንጉሡም ባሪያዎች ገብተው። እግዚአብሔር የሰሎሞንን ስም ከስምህ ዙፋኑንም ከዙፋንህ የበለጠ ያድርግ ብለው ጌታችንን ንጉሡን ዳዊትን ባረኩ፤ ንጉሡም በአልጋው ላይ ሆኖ ሰገደ።
48፤ ንጉሡም ደግሞ። ዓይኔ እያየ ዛሬ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጠውን የሰጠኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን አለ።
49፤ አዶንያስም የጠራቸው ሁሉ ፈሩ፥ ተነሥተውም እያንዳንዳቸው በየመንገዳቸው ሄዱ።
50፤ አዶንያስም ሰሎሞንን ፈራ፥ ተነሥቶም ሄደ፥ የመሠዊያውንም ቀንድ ያዘ።
51፤ ለሰሎሞንም። እነሆ፥ አዶንያስ ንጉሡን ሰሎሞንን ፈርቶ። ንጉሡ ሰሎሞን ባሪያውን በሰይፍ እንዳይገድለኝ ዛሬ ይማልልኝ ብሎ የመሠዊያውን ቀንድ ይዞአል አሉት።
52፤ ሰሎሞንም። እርሱ አካሄዱን ያሳመረ እንደ ሆነ ከእርሱ አንዲት ጠጕር እንኳ በምድር ላይ አትወድቅም፤ ነገር ግን ክፋት የተገኘበት እንደ ሆነ ይሞታል አለ።
53፤ ንጉሡ ሰሎሞንም ላከ፥ ከመሠዊያውም አወረዱት፤ መጥቶም ለንጉሡ ለሰሎሞን እጅ ነሣ፥ ሰሎሞንም። ወደ ቤትህ ሂድ አለው።
ምዕራፍ 2

1፤ ዳዊትም የሚሞትበት ቀን ቀረበ፤ ልጁንም ሰሎሞንን እንዲህ ሲል አዘዘው።
2፤ እኔ የምድሩን ሁሉ መንገድ እሄዳለሁ፤
3፤ በርታ ሰውም ሁን፤ የምታደርገውንና የምትሄድበትን ሁሉ ታከናውን ዘንድ፥ በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈ ሥርዓቱንና ትእዛዛቱን ፍርዱንና ምስክሩንም ትጠብቅ ዘንድ፥ በመንገዱም ትሄድ ዘንድ፥ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቅ።
4፤ ይኸውም ደግሞ እግዚአብሔር ስለ እኔ። ልጆችህ መንገዳቸውን ቢጠብቁ፥ በፊቴም በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው በእውነት ቢሄዱ ከእስራኤል ዙፋን ሰው አይቈረጥብህም ብሎ የተናገረውን ቃል ያጸና ዘንድ ነው።
5፤ አንተም ደግሞ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ፥ ሁለቱን የእስራኤልን ጭፍራ አለቆች የኔር ልጅ አበኔርን የዬቴሩንም ልጅ አሜሳይን ገድሎ፥ በእኔ ላይ ያደረገውን ታውቃለህ፤ የሰልፉንም ደም በሰላም አፈሰሰ፥ በወገቡም ባለው ድግና በእግሩ ባለው ጫማ ንጹሕ ደም አኖረ።
6፤ አንተም እንደ ጥበብህ አድርግ፥ ሽበቱንም በሰላም ወደ መቃብር አታውርደው።
7፤ ከወንድምህ ከአቤሴሎም ፊት በሸሸሁ ጊዜ ቀርበውኛልና ለገለዓዳዊው ለቤርዜሊ ልጆች መልካም ቸርነት አድርግላቸው፥ በማዕድህም ከሚበሉት መካከል ይሁኑ።
8፤ እኔም ወደ መሃናይም በሄድሁ ጊዜ ብርቱ እርግማን የረገመኝ የብራቂም አገር ሰው የብንያማዊው የጌራ ልጅ ሳሚ፥ እነሆ፥ በአንተ ዘንድ ነው፤ እርሱ ግን ዮርዳኖስን በተሻገርሁ ጊዜ ሊቀበለኝ ወረደ፥ እኔም። በሰይፍ አልገድልህም ብዬ በእግዚአብሔር ምዬለታለሁ።
9፤ አንተ ግን ጥበበኛ ሰው ነህና ያለ ቅጣት አትተወው፤ የምታደርግበትንም አንተ ታውቃለህ፥ ሽበቱንም ከደም ጋር ወደ መቃብር አውርድ።
10፤ ዳዊትም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ።
11፤ ዳዊትም በእስራኤል ላይ የነገሠው ዘመን አርባ ዓመት ነበረ። በኬብሮን ሰባት ዓመት ነገሠ፤ በኢየሩሳሌምም ሠላሳ ሦስት ዓመት ነገሠ።
12፤ ሰሎሞንም በአባቱ በዳዊት ዙፋን ተቀመጠ፤ መንግሥቱም እጅግ ጸና።
13፤ የአጊት ልጅ አዶንያስም ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ መጣ፤ እርስዋም። ወደ እኔ መምጣትህ በሰላም ነውን? አለች፤
14፤ እርሱም። በሰላም ነው አለ። ደግሞም። ከአንቺ ጋር ጉዳይ አለኝ አለ፤ እርስዋም። ተናገር አለች።
15፤ እርሱም። መንግሥቱ ለእኔ እንደ ነበረ፥ እስራኤልም ሁሉ ንጉሥ እሆን ዘንድ ፊታቸውን ወደ እኔ አድርገው እንደ ነበረ አንቺ ታውቂያለሽ፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆኖለታልና መንግሥቱ ከእኔ አልፎ ለወንድሜ ሆኖአል።
16፤ አሁንም አንዲት ልመና እለምንሻለሁ፤ አታሳፍሪኝ አለ። እርስዋም። ተናገር አለችው።
17፤ እርሱም። አያሳፍርሽምና ሱነማይቱን አቢሳን ይድርልኝ ዘንድ ለንጉሡ ለሰሎሞን እንድትነግሪው እለምንሻለሁ አለ።
18፤ ቤርሳቤህም። መልካም ነው፥ ስለ አንተ ለንጉሡ እነግረዋለሁ አለች።
19፤ ቤርሳቤህም የአዶንያስን ነገር ትነግረው ዘንድ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ገባች፤ ንጉሡም ሊቀበላት ተነሣ ሳማትም፥ በዙፋኑም ተቀመጠ፤ ለንጉሡም እናት ወንበር አስመጣላት፥ በቀኙም ተቀመጠች።
20፤ እርስዋም። አንዲት ታናሽ ልመና እለምንሃለሁ፤ አታሳፍረኝ አለች። ንጉሡም። እናቴ ሆይ፥ አላሳፍርሽምና ለምኝ አላት።
21፤ እርስዋም። ሱነማይቱ አቢሳ ለወንድምህ ለአዶንያስ ትዳርለት አለች።
22፤ ንጉሡም ሰሎሞን ለእናቱ መልሶ። ሱነማይቱን አቢሳን ለአዶንያስ ለምን ትለምኝለታለሽ? ታላቅ ወንድሜ ነውና መንግሥትን ደግሞ ለምኚለት፤ ካህኑም አብያታርና የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ ደግሞ ከእርሱ ጋር ናቸው አላት።
23፤ ንጉሡም ሰሎሞን። አዶንያስ ይህን ቃል በሕይወቱ ላይ አለመናገሩ እንደ ሆነ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፥ ይህንም ይጨምርብኝ።
24፤ አሁንም ያጸናኝ፥ በአባቴም በዳዊት ዙፋን ላይ ያስቀመጠኝ፥ እንደ ተናገረውም ቤትን የሠራልኝ ሕያው እግዚአብሔርን! ዛሬ አዶንያስ ፈጽሞ ይገደላል ብሎ በእግዚአብሔር ማለ።
25፤ ንጉሡም ሰሎሞን የዮዳሄን ልጅ በናያስን ላከ፤ እርሱም ወደቀበት፥ ሞተም።
26፤ ንጉሡም ካህኑን አብያታርን። አንተ ዛሬ የሞት ሰው ነበርህ፤ ነገር ግን የአምላክን የእግዚአብሔርን ታቦት በአባቴ በዳዊት ፊት ስለ ተሸከምህ፥ አባቴም የተቀበለውን መከራ ሁሉ አንተ ስለ ተቀበልህ አልገድልህምና በዓናቶት ወዳለው ወደ እርሻህ ሂድ አለው።
27፤ በሴሎም በዔሊ ቤት ላይ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ ሰሎሞን አብያታርን ከእግዚአብሔር ክህነት አወጣው።
28፤ ለኢዮአብም ወሬ ደረሰለት፤ ኢዮአብም አቤሴሎምን አልተከተለም ነበር እንጂ አዶንያስን ተከትሎ ነበር። ኢዮአብም ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ የመሠዊያውን ቀንድ ያዘ።
29፤ ንጉሡም ሰሎሞን ኢዮአብ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ መሠዊያውን እንደ ያዘ ሰማ፤ ሰሎሞንም የዮዳሄን ልጅ በናያስን፥ ሂድ ውደቅበት ብሎ አዘዘው።
30፤ በናያስም ወደ እግዚአብሔር ድንኳን መጥቶ። ንጉሡ። ውጣ ይልሃል አለው፤ እርሱም። በዚህ እሞታለሁ እንጂ አልወጣም አለ። በናያስም። ኢዮአብ የተናገረው ቃል የመለሰልኝም እንዲህ ነው ብሎ ወደ ንጉሡ ወሬ አመጣ።
31፤ ንጉሡም አለው። እንደ ነገረህ አድርግ፤ ኢዮአብም በከንቱ ያፈሰሰውን ደም ከእኔና ከአባቴ ቤት ታርቅ ዘንድ ገድለህ ቅበረው።
32፤ አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ከእርሱ የሚሻሉትን ሁለቱን ጻድቃን ሰዎች፥ የእስራኤልን ሠራዊት አለቃ የኔርን ልጅ አበኔርን፥ የይሁዳንም ሠራዊት አለቃ የዬቴርን ልጅ አሜሳይን፥ በሰይፍ ገድሎአልና እግዚአብሔር ደሙን በራሱ ላይ ይመልሰው።
33፤ ደማቸውም በኢዮአብ ራስና በዘሩ ራስ ላይ ለዘላለም ይመለስ፤ ለዳዊት ግን ለዘሩና ለቤቱ ለዙፋኑም የእግዚአብሔር ሰላም ለዘላለም ይሁን።
34፤ የዮዳሄም ልጅ በናያስ ወጥቶ ወደቀበት ገደለውም፤ በምድረ በዳም ባለው በቤቱ ተቀበረ።
35፤ ንጉሡም በእርሱ ፋንታ የዮዳሄን ልጅ በናያስን የሠራዊቱ አለቃ አደረገ፤ በአብያታርም ፋንታ ካህኑን ሳዶቅን አደረገ።
36፤ ንጉሡም ልኮ ሳሚን አስጠራውና። በኢየሩሳሌም ቤት ሠርተህ ተቀመጥ፥ ወዲህና ወዲያም አትውጣ።
37፤ በወጣህበትም ቀን፥ የቄድሮንንም ፈፋ በተሻገርህበት ቀን ፈጽመህ እንድትሞት እወቅ፤ ደምህ በራስህ ላይ ይሆናል አለው።
38፤ ሳሚም ንጉሡን። ነገሩ መልካም ነው፤ ጌታዬ ንጉሥ እንደ ተናገረ ባሪያህ እንዲሁ ያደርጋል አለው፤ ሳሚም በኢየሩሳሌም ብዙ ቀን ተቀመጠ።
39፤ ከሦስት ዓመትም በኋላ ከሳሚ ባሪያዎች ሁለቱ ወደ ጌት ንጉሥ ወደ መዓካ ልጅ ወደ አንኩስ ኰበለሉ፤ ሳሚንም። እነሆ፥ ባሪያዎችህ በጌት ናቸው ብለው ነገሩት።
40፤ ሳሚም ተነሣ፥ አህያውንም ጭኖ ባሪያዎቹን ይሻ ዘንድ ወደ ጌት ወደ አንኩስ ዘንድ ሄደ፤ ሳሚም ሄዶ ባሪያዎቹን ከጌት አመጣ።
41፤ ሰሎሞንም ሳሚ ከኢየሩሳሌም ወደ ጌት ሄዶ እንደ ተመለሰ ሰማ።
42፤ ንጉሡም ልኮ ሳሚን አስጠራና። ወዲህና ወዲያ ለመሄድ በወጣህ ቀን ፈጽመህ እንድትሞት እወቅ ብዬ በእግዚአብሔር አላስማልሁህምን? ወይስ አላስመሰከርሁብህምን? አንተም። ቃሉ መልካም ነው፥ ሰምቻለሁ አልኸኝ።
43፤ የእግዚአብሔርን መሐላ እኔስ ያዘዝሁህን ትእዛዝ ስለ ምን አልጠበቅህም? አለው።
44፤ ንጉሡም ደግሞ ሳሚን። አንተ በአባቴ በዳዊት ላይ የሠራኸውን ልብህም ያሰበውን ክፋት ሁሉ ታውቃለህ፤ እግዚአብሔርም ክፋትህን በራስህ ላይ ይመልሳል።
45፤ ንጉሡ ሰሎሞን ግን የተባረከ ይሆናል፥ የዳዊትም ዙፋን በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም ይጸናል አለው።
46፤ ንጉሡም የዮዳሄን ልጅ በናያስን አዘዘው፥ ወጥቶም ወደቀበት፥ ሞተም። መንግሥትም በሰሎሞን እጅ ጸና። a
ምዕራፍ 3

1፤ ሰሎሞንም ለግብጽ ንጉሥ ለፈርዖን አማች ሆነ፤ የፈርዖንን ልጅ አገባ፥ ቤቱንና የእግዚአብሔርንም ቤት በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ያለውን ቅጥር ሠርቶ እስኪፈጽም ድረስ ወደ ዳዊት ከተማ አመጣት።
2፤ እስከዚያም ቀን ድረስ ለእግዚአብሔር ስም መቅደስ አልተሠራም ነበርና ሕዝቡ በኮረብታ ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋ ነበር።
3፤ ሰሎሞንም እግዚአብሔርን ይወድድ ነበር፥ በአባቱም በዳዊት ሥርዓት ይሄድ ነበር፤ ብቻ በኮረብታ መስገጃ ይሠዋና ያጥን ነበር።
4፤ ገባዖን ዋና የኮረብታ መስገጃ ነበረችና ንጉሡ ይሠዋ ዘንድ ወደዚያ ሄደ፤ ሰሎሞንም በዚያ መሠዊያ ላይ አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ።
5፤ እግዚአብሔርም በገባዖን ለሰሎሞን በሌሊት በሕልም ተገለጠለት፤ እግዚአብሔርም። ምን እንድሰጥህ ለምን አለ።
6፤ ሰሎሞንም አለ። እርሱ በፊትህ በእውነትና በጽድቅ በልብም ቅንነት ከአንተ ጋር እንደ ሄደ፥ ከባሪያህ ከአባቴ ከዳዊት ጋር ታላቅ ቸርነት አድርገሃል፤ ዛሬ እንደ ሆነም በዙፋኑ ላይ የሚቀመጥ ልጅ ሰጥተህ ታላቁን ቸርነትህን አቆይተህለታል።
7፤ አሁንም፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ እኔን ባሪያህን በአባቴ በዳዊት ፋንታ አንግሠኸኛል፤ እኔም መውጫንና መግቢያን የማላውቅ ታናሽ ብላቴና ነኝ።
8፤ ባሪያህም ያለው አንተ በመረጥኸው ሕዝብህ ስለ ብዛቱም ይቈጠርና ይመጠን ዘንድ በማይቻል በታላቅ ሕዝብ መካከል ነው።
9፤ ስለዚህም በሕዝብህ ላይ መፍረድ ይችል ዘንድ፥ መልካሙንና ክፉውንም ይለይ ዘንድ ለባሪያህ አስተዋይ ልቡና ስጠው፤ አለዚያማ በዚህ በታላቅ ሕዝብህ ላይ ይፈድ ዘንድ ማን ይችላል?
10፤ ሰሎሞንም ይህን ነገር ስለ ለመነ፥ ነገሩ እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው።
11፤ እግዚአብሔርም አለው። ፍርድን ትለይ ዘንድ ለራስህ ማስተዋልን ለመንህ እንጂ ለራስህ ብዙ ዘመናትን ባለጠግነትንም የጠላቶችህንም ነፍስ ሳትለምን ይህን ነገር ለምነሃልና እነሆ፥
12፤ እኔ እንደ ቃል አድርጌልሃለሁ፤ እነሆ፥ ማንም የሚመስልህ ከአንተ በፊት እንደሌለ ከአንተም በኋላ እንዳይነሣ አድርጌ ጥበበኛና አስተዋይ ልቡና ሰጥቼሃለሁ።
13፤ ደግሞም ከነገሥታት የሚመስልህ ማንም እንዳይኖር ያልለመንኸውን ባለጠግነትና ክብር ሰጥቼሃለሁ።
14፤ አባትህም ዳዊት እንደ ሄደ፥ ሥርዓቴንና ትእዛዜን ትጠብቅ ዘንድ በመንገዴ የሄድህ እንደ ሆነ፥ ዕድሜህን አረዝመዋለሁ።
15፤ ሰሎሞንም ነቃ፥ እነሆም፥ ሕልም ነበረ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም መጥቶ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት ቆመ፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አሳረገ፥ የደኅንነትንም መሥዋዕት አቀረበ፥ ለባሪያዎቹም ሁሉ ግብዣ አደረገ።
16፤ በዚያን ጊዜም ሁለት ጋለሞቶች ሴቶች ወደ ንጉሡ መጥተው በፊቱ ቆሙ።
17፤ አንደኛይቱም ሴት አለች። ጌታዬ ሆይ፥ እኔና ይህች ሴት በአንድ ቤት እንኖራለን፤ እኔም ከእርስዋ ጋር በቤት ሳለሁ ወለድሁ።
18፤ እኔ ከወለድሁ ከሦስት ቀን በኋላ ይህች ሴት ደግሞ ወለደች፤ እኛ በቤት ውስጥ አብረን ነበርን፥ ከሁለታችንም በቀር ማንም በቤት ውስጥ አልነበረም።
19፤ እርስዋም በላዩ ስለ ተኛችበት የዚህች ሴት ልጅ በሌሊት ሞተ።
20፤ እርስዋም በእኩለ ሌሊት ተነሥታ፥ እኔ ባሪያህ ተኝቼ ሳለሁ፥ ልጄን ከአጠገቤ ወሰደች፥ በብብትዋም አደረገችው፥ የሞተውንም ልጅዋን በእኔ ብብት አደረገች።
21፤ ልጄንም አጠባ ዘንድ በማለዳ ብነሣ፥ እነሆ፥ ሞቶ ነበር፤ ነገር ግን ብርሃን በሆነ ጊዜ ተመለከትሁት፥ እነሆም፥ የወለድሁት ልጄ አልነበረም።
22፤ ሁለተኛይቱም ሴት። ደኅነኛው የኔ ልጅ ነው፥ የሞተውም የአንቺ ልጅ ነው እንጂ አንቺ እንደምትዪው አይደለም አለች። ይህችም። የሞተው የአንቺ ልጅ ነው፥ ደኅነኛውም የእኔ ልጅ ነው አለች፤ እንዲሁም በንጉሡ ፊት ይነጋገሩ ነበር።
23፤ በዚያን ጊዜም ንጉሡ። ይህች። ደኅነኛው የእኔ ልጅ ነው፥ የሞተውም የአንቺ ልጅ ነው ትላለች፤ ያችኛይቱም። አይደለም፥ የሞተው የአንቺ ልጅ ነው ደኅነኛውም የእኔ ልጅ ነው ትላለች አለ።
24፤ ንጉሡም። ሰይፍ አምጡልኝ አለ፤ ሰይፍም ይዘው ወደ ንጉሡ ፊት መጡ።
25፤ ንጉሡም። ደኅነኛውን ሕፃን ለሁለት ከፍላችሁ ለአንዲቱ አንዱን ክፍል፥ ለሁለተኛይቱም ሁለተኛውን ክፍል ስጡ አለ።
26፤ ደኅነኛውም የነበራት ሴት አንጀትዋ ስለ ልጅዋ ናፍቆአልና። ጌታዬ ሆይ፥ ደኀነኛውን ለእርስዋ ስጣት እንጂ አትግደል ብላ ለንጉሡ ተናገረች። ያችኛይቱ ግን። ይከፈል እንጂ ለእኔም ለአንቺም አይሁን አለች።
27፤ ንጉሡም መልሶ። ይህችኛይቱ እናቱ ናትና ደኅነኛውን ሕፃን ለእርስዋ ስጡአት እንጂ አትግደሉት አለ።
28፤ ንጉሡም የፈረደውን ፍርድ እስራኤል ሁሉ ሰሙ፤ ፍርድን ለማድረግ የእግዚአብሔር ጥበብ እንደ ነበረበት አይተዋልና ንጉሡን ፈሩ።
ምዕራፍ 4

1፤ ንጉሡም ሰሎሞን በእስራኤል ሁሉ ላይ ነግሦ ነበር።
2፤ የነበሩትም አለቆች እነዚህ ናቸው፤ የሳዶቅ ልጅ ካህኑ ዓዛርያስ፥
3፤ ጸሐፊዎቹም የሴባ ልጆች ኤልያፍና አኪያ፥ ታሪክ ጸሐፊም የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ፥
4፤ የዮዳሄም ልጅ በናያስ የሠራዊት አለቃ ነበረ፤ ሳዶቅና አብያታርም ካህናት ነበሩ፤
5፤ የናታንም ልጅ ዓዛርያስ የሹሞች አለቃ ነበረ፤ የናታንም ልጅ ዛቡድ የንጉሡ አማካሪና ወዳጅ ነበረ፤
6፤ አሒሳርም የቤት አዛዥ፥ የዓብዳም ልጅ አዶኒራም አስገባሪ ነበረ።
7፤ ለንጉሡና ለቤተ ሰቡም ቀለብ የሚሰጡ በእስራኤል ሁሉ ላይ አሥራ ሁለት ሹሞች ለሰሎሞን ነበሩት። ከዓመቱ ውስጥ አንዱን ወር እያንዳንዳቸው ይቀልቡ ነበር።
8፤ ስማቸውም ይህ ነበረ፤ በተራራማው አገር በኤፍሬም የሑር ልጅ፤
9፤ በማቃጽና በሸዓልቢም በቤትሳሚስና በኤሎንቤትሐናን የዴቀር ልጅ፤
10፤ በአሩቦት የሔሴድ ልጅ፥ ለእርሱም ሰኰትና የኦፌር አገር ሁሉ ነበረ፤
11፤ በዶር አገር ዳርቻ ሁሉ የአሚናዳብ ልጅ፥ እርሱም የሰሎሞንን ልጅ ጣፈትን አግብቶ ነበር፤
12፤ ከቤትሳን ጀምሮ እስከ አቤልምሖላና እስከ ዮቅምዓም ማዶ ድረስ በታዕናክና በመጊዶ በጸርታንም አጠገብ በኢይዝራኤል በታች ባለው በቤትሳን ሁሉ የአሒሉድ ልጅ በዓና ነበረ፤
13፤ በሬማት ዘገለዓድ የጌበር ልጅ ነበረ፥ ለእርሱም በገለዓድ ያሉት የምናሴ ልጅ የኢያዕር መንደሮች ነበሩ፤ ለእርሱም ደግሞ በባሳን በአርጎብ ዳርቻ ያሉት ቅጥርና የናስ መወረወሪያዎች የነበረባቸው ስድሳ ታላላቅ ከተሞች ነበሩበት፤
14፤ በመሃናይም የዒዶ ልጅ አሒናዳብ፤
15፤ በንፍታሌም አኪማአስ ነበረ፥ እርሱም የሰሎሞንን ልጅ ባስማትን አግብቶ ነበር፤
16፤ በአሴርና በበዓሎት የኩሲ ልጅ በዓና፤
17፤ በይሳኮር የፋሩዋ ልጅ ኢዮሣፍጥ፤
18፤ በብንያም የኤላ ልጅ ሳሚ፤
19፤ በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎንና በባሳን ንጉሥ በዐግ አገር፥ በገለዓድ አገር፥ የኡሪ ልጅ ጌበር ነበረ፤ በዚያችም ምድር ላይ እርሱ ብቻውን ሹም ነበረ።
20፤ ይሁዳና እስራኤልም እንደ ባሕር አሸዋ ብዛት ብዙ ነበሩ፤ በልተውም ጠጥተውም ደስ ብሎአቸው ነበር።
21፤ ሰሎሞንም ከወንዙ ጀምሮ እስከ ግብጽ ዳርቻ እስከ ፍልስጥኤም ድረስ በመንግሥታት ሁሉ ላይ ነግሦ ነበር፤ ግብርም ያመጡለት ነበር፥ በዕድሜውም ሙሉ ለሰሎሞን ይገዙ ነበር።
22፤ ለሰሎሞንም ለቀን ለቀኑ ቀለብ የሚሆን ሠላሳ ኮር መልካም ዱቄትና ስድሳ ኮር መናኛ ድቄት፥
23፤ ከዋላና ከሚዳቋ ከበረሀ ፍየልና ከሰቡ ወፎች በቀር አሥር ፍሪዳዎች ሀያም የተሰማሩ በሬዎች አንድ መቶም በጎች ነበረ።
24፤ ከወንዙ ወዲህ ባሉት ነገሥታት ሁሉ ከወንዙም ወዲህ ባለው አገር ሁሉ ላይ ከቲፍሳ ጀምሮ እስከ ጋዛ ድረስ ነግሦ ነበር፤ በዙሪያውም ባለው በሁሉ ወገን ሰላም ሆኖለት ነበር።
25፤ በሰሎሞንም ዘመን ሁሉ ይሁዳና እስራኤል ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ተዘልሎ ይቀመጥ ነበር።
26፤ ለሰሎሞንም በአርባ ሺህ ጋጥ የሚገቡ የሰረገላ ፈረሶች አሥራ ሁለትም ሺህ ፈረሰኞች ነበሩት።
27፤ እነዚያም ሹሞች እያንዳንዱ በየወሩ ንጉሡን ሰሎሞንንና ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ማዕድ የሚቀርቡትን ሁሉ ይቀልቡ ነበር፤ ምንም አያጎድሉም ነበር።
28፤ እያንዳንዱም እንደ ደንቡ ለፈረሶቹና ለሰጋር በቅሎች ገብስና ጭድ ወደ ስፍራቸው ያመጡ ነበር።
29፤ እግዚአብሔርም ለሰሎሞን እጅግ ብዙ ጥበብና ማስተዋል በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋት ሰጠው።
30፤ የሰሎሞንም ጥበብ በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ጥበብና ከግብጽ ጥበብ ሁሉ በለጠ።
31፤ ከሰውም ሁሉ ይልቅ ከኢይዝራኤላዊው ከኤታንና ከማሖል ልጆች ከሄማንና ከከልቀድ ከደራልም ይልቅ ጥበበኛ ነበረ። በዙሪያውም ባሉ አሕዛብ ሁሉ ዝናው ወጣ።
32፤ እርሱም ሦስት ሺህ ምሳሌዎች ተናገረ፤ መኃልዩም ሺህ አምስት ነበረ።
33፤ ስለ ዛፍም ከሊባኖስ ዝግባ ጀምሮ በቅጥር ግንብ ላይ እስከሚበቅለው እስከ ሂሶጵ ድረስ ይናገር ነበር፤ ደግሞም ስለ አውሬዎችና ስለ ወፎች ሰለተንቀሳቃሾችና ስለ ዓሣዎች ይናገር ነበር።
34፤ ከአሕዛብም ሁሉ፥ ጥበቡንም ሰምተው ከነበሩ ከምድር ነገሥታት ሁሉ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ሰዎች ይመጡ ነበር። a
ምዕራፍ 5

1፤ የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ለዳዊት በዘመኑ ሁሉ ወዳጅ ስለ ነበረ፥ ሰሎሞን በአባቱ ፋንታ ንጉሥ ለመሆን እንደ ተቀባ ሰምቶ ባሪያዎቹን ወደ ሰሎሞን ሰደደ።
2፤ ሰሎሞንም ወደ ኪራም እንዲህ ብሎ ላከ።
3፤ እግዚአብሔር ከእግሩ በታች እስኪጥልለት ድረስ በዙሪያው ስለ ነበረ ሰልፍ አባቴ ዳዊት የአምላኩን የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት እንዳልቻለ አንተ ታውቃለህ።
4፤ አሁንም አምላኬ እግዚአብሔር በዙሪያዬ ካሉት ዕረፍት ሰጥቶኛል፤ ጠላትም ክፉም ነገር የለብኝም።
5፤ እነሆም፥ እግዚአብሔር ለአባቴ ለዳዊት። በአንተ ፋንታ በዙፋንህ ላይ የማስቀምጠው ልጅህ እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል ብሎ እንደ ነገረው፥ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤት እሠራ ዘንድ አስባለሁ።
6፤ አሁንም ከወገኔ እንደ ሲዶናውያን እንጨት መቈረጥ የሚያውቅ እንደሌለ ታውቃለህና የዝግባ ዛፍ ከሊባኖስ ይቈርጡልኝ ዘንድ ባሪያዎችህን እዘዝ፤ ባሪያዎቼም ከባሪያዎችህ ጋር ይሁኑ፤ የባሪያዎችህንም ዋጋ እንደ ተናገርኸው ሁሉ እሰጥሃለሁ።
7፤ ኪራምም የሰሎሞንን ቃል ሰምቶ እጅግ ደስ አለውና። በዚህ በታላቅ ሕዝብ ላይ ጥበበኛ ልጅ ለዳዊት የሰጠ እግዚአብሔር ዛሬ ይመስገን አለ።
8፤ ኪራምም። የላክህብኝን ሁሉ ሰማሁ፤ ስለ ዝግባውና ስለ ጥዱ እንጨት ፈቃድህን ሁሉ አደርጋለሁ።
9፤ ባሪያዎቼ ከሊባኖስ ወደ ባሕር ይጐትቱታል፤ እኔም በታንኳ አድርጌ በባሕር ላይ እያንሳፈፍሁ አንተ እስከ ወሰንኸው ስፍራ ድረስ አደርስልሃለሁ፥ በዚያም እፈታዋለሁ፥ አንተም ከዚያ ታስወስደዋለህ፤ አንተም ፈቃዴን ታደርጋለህ፤ ለቤቴም ቀለብ የሚሆነውን ትሰጠኛለህ ብሎ ወደ ሰሎሞን ላከ።
10፤ እንዲሁም ኪራም የዝግባውንና የጥዱን እንጨት እንደሚሻው ያህል ሁሉ ለሰሎሞን ይሰጠው ነበር።
11፤ ሰሎሞንም ለኪራም ስለ ቤቱ ቀለብ ሀያ ሺ የቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ ሀያ ኮርም ጥሩ ዘይት ይሰጠው ነበር፤ ሰሎሞንም ለኪራም በየዓመቱ ይህን ይሰጥ ነበር።
12፤ እግዚአብሔርም እንደ ነገረው ለሰሎሞን ጥበብን ሰጠው፤ በኪራምና በሰሎሞንም መካከል ሰላም ነበረ፤ ሁለቱም ቃል ኪዳን ተጋቡ።
13፤ ሰሎሞንም ከእስራኤል ሁሉ ገባሮቹን መርጦ አወጣ፤ የገባሮቹም ቍጥር ሠላሳ ሺህ ሰዎች ነበረ።
14፤ በየወሩም እያከታተለ ወደ ሊባኖስ አሥር አሥር ሺህ ይሰድድ ነበር፤ አንድ ወርም በሊባኖስ ሁለት ወርም በቤታቸው ይቀመጡ ነበር። አዶኒራምም አስገባሪ ነበረ።
15፤ ሰሎሞንም ሰባ ሺህ ተሸካሚዎች፥ ሰማንያ ሺህም በተራራው ላይ የሚጠርቡ ጠራቢዎች ነበሩት።
16፤ ይኸውም በሠራተኛው ሕዝብ ላይ ከተሾሙት ከሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎች ሌላ ነው።
17፤ ንጉሡም ታላላቅ ምርጥ ምርጥ ድንጋዮችን ይቈፍሩና ይጠርቡ ዘንድ ለቤቱም መሠረት ይረበርቡት ዘንድ አዘዘ።
18፤ የሰሎሞንና የኪራምም አናጢዎች ጌባላውያንም ወቀሩአቸው፥ ቤቱንም ለመሥራት እንጨቱንና ድንጋዮቹን አዘጋጁ።
ምዕራፍ 6

1፤ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር ከወጡ አራት መቶ ሰማንያ ዓመት በሆነ ጊዜ፥ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ ዚፍ በሚባለው በሁለተኛው ወር የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመረ።
2፤ ንጉሡ ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር የሠራው ቤት ርዝመቱ ስድሳ ክንድ፥ ወርዱም ሀያ ክንድ፥ ቁመቱም ሠላሳ ክንድ ነበረ።
3፤ በመቅደሱም ፊት ወለል ነበረ፤ ርዝመቱም እንደ መቅደሱ ወርድ ሀያ ክንድ፥ ወርዱም ከቤቱ ወደፊት አሥር ክንድ ነበረ።
4፤ ለቤቱም በዓይነ ርግብ የተዘጉ መስኮቶች አደረገ።
5፤ በቤቱም ግንብ ዙሪያ፥ በመቅደሱና በቅድስተ ቅዱሳኑ ግንብ ዙሪያ፥ ደርብ ሠራ፥ በዙሪያውም ጓዳዎች አደረገ።
6፤ የታችኛውም ደርብ ወርዱ አምስት ክንድ፥ የመካከለኛው ደርብ ወርዱ ስድስት ክንድ፥ የሦስተኛውም ደርብ ወርዱ ሰባት ክንድ ነበረ። ሰረገሎቹ በቤቱ ግንብ ውስጥ እንዳይገቡ ከቤቱ ግንብ ውጭ ዓረፍቶች አደረገ።
7፤ ቤቱም በተሠራ ጊዜ ፈጽመው በተወቀሩ ድንጋዮች ተሠራ፤ በተሠራም ጊዜ መራጃና መጥረቢያ የብረትም ዕቃ ሁሉ በቤቱ ውስጥ አልተሰማም።
8፤ የታችኛውም ደርብ ጓዳዎች በር በቤቱ ቀኝ አጠገብ ነበረ። ከዚያም ወደ መካከለኛው ደርብ፥ ከመካከለኛውም ወደ ሦስተኛው ደርብ በመውጫ ያስወጣ ነበር።
9፤ ቤቱንም ሠርቶ ፈጸመው፤ በዝግባው ሰረገሎችና ሳንቃዎች ከደነው።
10፤ በቤቱም ሁሉ ዙሪያ ቁመታቸው አምስት አምስት ክንድ የሆነ ደርቦች ሠራ፤ ከቤቱም ጋር በዝግባ እንጨት አጋጠማቸው።
11፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ሰሎሞን መጣ እንዲህ ሲል።
12፤ ስለዚህ ስለምትሠራው ቤት በሥርዓቴ ብትሄድ፥ ፍርዴንም ብታደርግ፥ ትመላለስበትም ዘንድ ትእዛዜን ሁሉ ብትጠብቅ፥ ለአባትህ ለዳዊት የነገርሁትን ቃል ከአንተ ጋር አጸናለሁ።
13፤ በእስራኤልም ልጆች መካከል እኖራለሁ፥ ሕዝቤንም እስራኤልን አልጥልም።
14፤ ሰሎሞንም ቤቱን ሠራው፥ ፈጸመውም።
15፤ የቤቱንም ግንብ ውስጡን በዝግባ ሳንቃ ለበጠ፤ ከቤቱም መሠረት ጀምሮ እስከ ጣራው ድረስ ውስጡን በእንጨት ለበጠው፤ ደግሞም የቤቱን ወለል በጥድ እንጨት ከደነው።
16፤ በቤቱ ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳን ይሆን ዘንድ ኋለኛውን ሀያውን ክንድ በዝግባ እንጨት ጋረደው።
17፤ በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ያለውም መቅደስ ርዝመቱ አርባ ክንድ ነበረ።
18፤ የቤቱንም ውስጥ በተጐበጐበና በፈነዳ አበባ በተቀረጸ ዝግባ ለበጠው፤ ሁሉም ዝግባ ነበረ፤ ድንጋዩም አልታየም ነበር።
19፤ በዚያም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ያኖር ዘንድ በቤቱ ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳኑን አበጀ።
20፤ የቅድስተ ቅዱሳንም ርዝመት ሀያ ክንድ፥ ስፋቱም ሀያ ክንድ፥ ቁመቱም ሀያ ክንድ ነበረ፤ በጥሩ ወርቅም ለበጠው።
21፤ በቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት ከዝግባ የተሠራ መሠዊያ አደረገ፤ በጥሩ ወርቅም ለበጠው።
22፤ ቤቱንም ሁሉ ፈጽሞ በወርቅ ለበጠው፤ በቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት የነበረውን መሠዊያ ሁሉ በወርቅ ለበጠው።
23፤ በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ ቁመታቸው አሥር ክንድ የሆነ ከወይራ እንጨት ሁለት ኪሩቤል ሠራ።
24፤ የኪሩብም አንደኛው ክንፍ አምስት ክንድ፥ የኪሩብም ሁለተኛው ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፤ ከአንደኛው ክንፍ ጫፍ ጀምሮ እስክ ሁለተኛው ክንፍ ጫፍ ድረስ አሥር ክንድ ነበረ።
25፤ ሁለተኛውም ኪሩብ አሥር ክንድ ነበረ፤ ሁለቱም ኪሩቤል አንድ ልክና አንድ መልክ ነበረ።
26፤ የአንዱ ኪሩብ ቁመት አሥር ክንድ ነበረ፥ የሁለተኛውም ኪሩብ እንዲሁ ነበረ።
27፤ ኪሩቤልንም በውስጠኛው ቤት አኖራቸው፤ የኪሩቤልም ክንፎቻቸው ተዘርግተው ነበር፤ የአንዱም ኪሩብ ክንፍ አንደኛውን ግንብ ይነካ ነበር፥ የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ ሁለተኛውን ግንብ ይነካ ነበር፤ የሁለቱም ክንፎች በቤቱ መካከል እርስ በርሳቸው ይነካኩ ነበር።
28፤ ኪሩቤልንም በወርቅ ለበጣቸው።
29፤ በቤቱም ግንብ ሁሉ ዙሪያ በውስጥና በውጭ የኪሩቤልና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸ።
30፤ የቤቱንም ወለል በውስጥና በውጭ በወርቅ ለበጠ።
31፤ ለቅዱስተ ቅዱሳኑም መግቢያ ከወይራ እንጨት ደጆች ሠራ፤ መድረኩንና መቃኖቹን ደፉንም አምስት ማዕዘን አደረገ።
32፤ ሁለቱንም ደጆች ከወይራ እንጨት ሠራ፤ የኪሩቤልንና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸባቸው፥ በወርቅም ለበጣቸው፤ ኪሩቤልናና የዘንባባውን ዛፍ በወርቅ ለበጣቸው።
33፤ እንዲሁም ለመቅደሱ መግቢያ ከወይራ እንጨት አራት ማዕዘን መቃን አደረገ።
34፤ ሁለቱንም ደጆች ከጥድ እንጨት ሠራ፤ አንዱ ደጅ በማጠፊያ ከተያያዘ ከሁለት ሳንቃ ተደረገ፥ ሁለተኛውም ደጅ በማጠፊያ ከተያያዘ ከሁለት ሳንቃ ተደረገ።
35፤ የኪሩቤልንና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸባቸው፤ በተቀረጸውም ሥራ ላይ በወርቅ ለበጣቸው።
36፤ የውስጠኛውንም አደባባይ ቅጥር ሦስቱን ተራ በተጠረበ ድንጋይ፥ አንዱንም ተራ በዝግባ ሳንቃ ሠራው።
37፤ በአራተኛው ዓመት ዚፍ በሚባል ወር የእግዚአብሔር ቤት ተመሠረተ።
38፤ በአሥራ አንደኛውም ዓመት ቡል በሚባል በስምንተኛው ወር ቤቱ እንደ ክፍሎቹና እንደ ሥርዓቱ ሁሉ ተጨረሰ። በሰባትም ዓመት ውስጥ ሠራው። a
ምዕራፍ 7

1፤ ሰሎሞንም የራሱን ቤት በአሥራ ሦስት ዓመት ሠራ፥ የቤቱንም ሥራ ሁሉ ጨረሰ።
2፤ የሊባኖስ ዱር ቤት የሚባል ቤትን ሠራ፤ ርዝመቱንም መቶ ክንድ፥ ስፋቱንም አምሳ ክንድ፥ ቁመቱንም ሠላሳ ክንድ አደረገ፤ የዝግባም እንጨት በሦስት ተራ በተሠሩ አዕማድ ላይ ቆሞ ነበር፤ በአዕማዱም ላይ የዝግባ እንጨት አግዳሚ ሰረገሎች ነበሩ።
3፤ በአዕማዱም ላይ በነበሩ አግዳሚዎች ቤቱ በዝግባ ሳንቃ ተሸፍኖ ነበር፤ አዕማዱም በአንዱ ተራ አሥራ አምስት፥ በአንዱ ተራ አሥራ አምስት እየሆኑ አርባ አምስት ነበሩ።
4፤ መስኮቶቹም በሦስት ተራ ነበሩ፥ መስኮቶቹም ፊት ለፊት ይተያዩ ነበር።
5፤ ደጆቹና መስኮቶቹም ሁሉ አራት ማዕዘን ነበሩ፤ መስኮቶቹም በሦስት ተራ ሆነው ፊት ለፊት ይተያዩ ነበር።
6፤ አዕማዱም ያሉበቱን ቤት ሠራ፤ ርዝመቱም አምሳ ክንድ፥ ስፋቱም ሠላሳ ክንድ ነበረ፤ በእርሱም ፊት ደግሞ አዕማድና መድረክ ያሉበት ወለል ነበረ።
7፤ ደግሞም የሚፈርድበት ዙፋን ያለበትን የፍርድ ቤት አደረገ። ከወለሉም አንሥቶ እስከ ጣራው ድረስ በዝግባ እንጨት ተሸፍኖ ነበር።
8፤ ከፍርድ ሰቀላ ወደ ውስጥ፥ በሌላውም አደባባይ ውስጥ የነበረውን መኖሪያ ቤት እንዲሁ ሠራ። እንደዚሁም ያለ ቤት ሰሎሞን ላገባት ለፈርዖን ልጅ ቤት ሠራ።
9፤ እነዚህም ሁሉ ከመሠረቱ ጀምሮ እስከ ጕልላቱ ድረስ በጥሩ በተጠረበና በውስጥና በውጭ በልክ በተከረከመ ድንጋይ ተሠርተው ነበር፤ በውጭውም እስከ ታላቁ አደባባይ ድረስ እንዲሁ ነበረ።
10፤ መሠረቱም አሥር ወይም ስምንት ክንድ በሆነ በጥሩና በታላቅ ድንጋይ ተሠርቶ ነበር።
11፤ በላዩም ልክ ሆኖ የተከረከመ ጥሩ ድንጋይና የዝግባ ሳንቃ ነበረ።
12፤ በታላቁም አደባባይ ዙሪያ የነበረው ቅጥር እንደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ውስጠኛው አደባባይ ቅጥርና እንደ ቤቱ ወለል ሦስቱ ተራ በተጠረበ ድንጋይ አንዱም ተራ በዝግባ ሳንቃ ተሠርቶ ነበር።
13፤ ንጉሡም ሰሎሞን ልኮ ኪራምን ከጢሮስ አስመጣ።
14፤ እርሱም ከንፍታሌም ወገን የነበረች የባል አልባ ሴት ልጅ ነበረ፥ አባቱም የጢሮስ ሰው ናስ ሠራተኛ ነበረ፤ የናስንም ሥራ ሁሉ ይሠራ ዘንድ በጥበብና በማስተዋል በብልሃትም ተሞልቶ ነበር። ወደ ንጉሡም ወደ ሰሎሞን መጥቶ ሥራውን ሁሉ ሠራ።
15፤ ሁለቱን የናስ አዕማድ አደረገ፤ የአንዱም ዓምድ ቁመት አሥራ ስምንት ክንድ ነበረ፥ የዙሪያውም መጠን አሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፤ የዓምዱም ውፍረት አንድ ጋት ነበረ፥ ውስጠ ክፍትም ነበረ። ሁለተኛውም ዓምድ እንዲሁ ነበረ።
16፤ በሁለቱም አዕማድ ራስ ላይ እንዲቀመጡ ከፈሰሰ ናስ ሁለት ጕልላት ሠራ፤ የአንዱም ጕልላት ቁመት አምስት ክንድ፥ የሁለተኛውም ጕልላት ቁመት አምስት ክንድ ነበረ።
17፤ በአዕማዱም ራስ ላይ የነበሩትን ጕልላቶች ይሸፍኑ ዘንድ ሁለት እንደ መርበብ ሥራ አደረገ፤ አንዱም መርበብ ለአንዱ ጕልላት ሁለተኛውም መርበብ ለሁለተኛው ጕልላት ነበረ።
18፤ ሮማኖችንም ሠራ፤ በአንድ ጕልላት ዙሪያ በተራ ሁለት መቶ ሮማኖች ነበሩ፥ በአንድም መርበብ ላይ ሁለት ተራ ነበረ፤ እንዲሁም ለሁለተኛው ጕልላት አደረገ።
19፤ በወለሉም አዕማድ በነበሩት ጕልላቶች ላይ የሱፍ አበባ የሚመስል ሥራ አራት ክንድ አድርጎ ቀረጸ።
20፤ በሁለቱም አዕማድ በነበሩት ጕልላቶች ላይ በመርበቡ ሥራ አጠገብ ሮማኖቹን አደረገ።
21፤ አዕማዱንም በመቅደሱ ወለል አጠገብ አቆማቸው፤ የቀኙንም ዓምድ አቁሞ ያቁም ብሎ ጠራው፤ የግራውንም ዓምድ አቁሞ በለዝ ብሎ ጠራው።
22፤ በአዕማዱም ራስ ላይ የሱፍ አበባ የሚመስል ሥራ ነበረ፤ እንዲሁም የአዕማዱ ሥራ ተጨረሰ።
23፤ ከፈሰሰም ናስ ከዳር እስከ ዳር አሥር ክንድ፥ ቁመቱም አምስት ክንድ፥ በዙሪያውም ሠላሳ ክንድ የሆነ ክብ ኵሬ ሠራ።
24፤ ከከንፈሩም በታች ለአንድ ክንድ አሥር ለአንድ ክንድም አሥር ጉብጉቦች አዞረበት፤ እርሱም በቀለጠ ጊዜ ጉብጉቦቹ በሁለት ተራ ከእርሱ ጋር አብረው ቀልጠው ነበር።
25፤ ኵሬውም በአሥራ ሁለት በሬዎች ምስል ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ከእነርሱም ሦስቱ ወደ ሰሜን፥ ሦስቱም ወደ ምዕራብ፥ ሦስቱም ወደ ደቡብ፥ ሦስቱም ወደ ምሥራቅ ይመለከቱ ነበር። ኵሬውም በላያቸው ነበረ፥ የሁሉም ጀርባቸው በስተ ውስጥ ነበረ።
26፤ ውፍረቱም አንድ ጋት ነበረ፤ ከንፈሩም እንደ ጽዋ ከንፈር ተሠርቶ ነበር፤ እንደ ሱፍ አበባዎች ሆኖ ተከርክሞ ነበር። ሁለት ሺህም የባዶስ መስፈሪያ ይይዝ ነበር።
27፤ አሥርም የናስ መቀመጫዎች ሠራ፤ የአንዱም መቀመጫ ርዝመት አራት ክንድ፥ ወርዱም አራት ክንድ፥ ቁመቱም ሦስት ክንድ ነበረ።
28፤ የመቀመጫውም ሥራ እንዲህ ነበረ፤ በክፈፎችም መካከል ያለው ሰንበር ይመስል ነበር።
29፤ በክፈፎቹም መካከል በነበሩ ሰንበሮች ላይ አንበሳዎችና በሬዎች ኪሩቤልም ነበሩ፤ እንዲሁም በክፈፎቹ ላይ ነበረ፤ ከአንበሳዎቹና ከበሬዎቹ በታች ሻኵራ የሚመስል ተንጠልጥሎ ነበር።
30፤ በየመቀመጫዎቹም ሁሉ አራት የናስ መንኰራኵሮች ነበሩባቸ፤ መንኰራኵሮቹም የሚዞሩበትን የናስ ወስከምት ሠራ፤ ከመታጠቢያውም ሰን በታች በአራቱ ማዕዘን በኩል አራት በምስል የፈሰሱ እግሮች ነበሩ።
31፤ በክፈፉም ውስጥ የነበረ አንገት አንድ ክንድ ነበረ፤ አንገቱም ድቡልቡል ነበረ፥ ቁመቱም ክንድ ተኩል ነበረ። በአንገቱም ላይ ቅርጽ ነበረበት፤ ክፈፉ ግን አራት ማዕዘን ነበረ እንጂ ድቡልቡል አልነበረም።
32፤ አራቱም መንኰራኵሮች ከሰንበሮቹ በታች ነበሩ፤ የመንኰራኵሮቹም ወስከምት በመቀመጫው ውስጥ ነበረ፤ የመንኰራኵሩም ቁመት ክንድ ተኩል ነበረ።
33፤ የመንኰራኵሮቹም ሥራ እንደ ሰረገላ መንኰራኵር ነበረ፥ ወስከምቶቹና የመንኰራኵሮቹ ክፈፍ ቅትርቶቹም ወስከምቱም የሚገባበት ቧምቧ ሁሉ በምስል የፈሰሰ ነበር።
34፤ በእያንዳንዱም መቀመጫ በአራቱ ማዕዘን በኩል አራት ደገፋዎች ነበሩ፤ ደገፋዎቹም ከመቀመጫው ጋር ተገጥመው ነበር።
35፤ በመቀመጫውም ላይ ስንዝር የሚሆን ድቡልቡል ነገር ነበረ፤ በመቀመጫውም ላይ የነበሩ መያዣዎችና ሰንበሮች ከእርሱ ጋር ይጋጠሙ ነበር።
36፤ በመያዣውና በሰንበሮቹ ላይ ኪሩቤልንና አንበሳዎችን የዘንባባውንም ዛፍ እንደ መጠናችው ቀረጸ፥ በዙሪያውም ሻኵራ አደረገ።
37፤ እንዲሁ አሥሩን መቀመጫዎች ሠራ፤ ሁሉም በምስልና በመጠን በንድፍም ትክክሎች ነበሩ።
38፤ አሥሩንም የናስ መታጠቢያ ሰን ሠራ፤ አንዱ መታጠቢያ ሰን አርባ የባዶስ መስፈሪያ ያነሣ ነበር፤ እያንዳንዱም መታጠቢያ ሰን አራት ክንድ ነበረ፤ በአሥሩም መቀመጫዎች ላይ በእያንዳንዱ አንድ አንድ መታጠቢያ ሰን ይቀመጥ ነበር።
39፤ አምስቱንም መቀመጫዎች በቤቱ ቀኝ፥ አምስቱንም በቤቱ ግራ አኖራቸው፤ ኵሬውንም በቤቱ ቀኝ በአዜብ በኩል አኖረው።
40፤ ኪራምም ምንችቶችንና መጫሪያዎችን ድስቶችንም ሠራ፤ ኪራምም ለንጉሡ ለሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት የሠራውን ሥራ ሁሉ ጨረሰ።
41፤ ሁለቱም አዕማድ፥ በአዕማዱም ላይ የነበሩትን ኩብ የሚመስሉትን ጕልላቶች፥ በአዕማዱም ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጕልላቶች የሚሸፍኑትን ሁለቱን መርበቦች፥
42፤ በአዕማዱም ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጕልላቶች ይሸፍኑ ዘንድ ለእያንዳንዱ መርበብ በሁለት በሁለት ተራ አድርጎ ለሁለቱ መርበቦች አራት መቶ ሮማኖች አደረገ።
43፤ አሥሩንም መቀመጫዎች፥ በመቀመጫዎችም ላይ የሚቀመጡትን አሥሩን መታጠቢያ ሰን፥
44፤ አንዱንም ኵሬ፥ ከኵሬውም በታች የሚሆኑትን አሥራ ሁለቱን በሬዎች፥
45፤ ምንቸቶቹንም፥ መጫሪያዎቹንም፥ ድስቶቹንም አደረገ። ኪራምም ለንጉሡ ለሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት የሠራው ይህ ዕቃ ሁሉ የጋለ ናስ ነበረ።
46፤ በዮርዳኖስ ሜዳ በሱኮትና በጸርታን መካከል ባለው በወፍራሙ መሬት ውስጥ አስፈሰሰው።
47፤ ሰሎሞንም ዕቃውን ሁሉ ሳያስመዝን አኖረ፤ የናሱም ሚዛን ከብዛቱ የተነሣ አይቈጠርም ነበር።
48፤ ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን ዕቃ ሁሉ አሠራ፤ የወርቁን መሠዊያ፥ የገጹም ኅብስት የነበረበትን የወርቅ ገበታ፥
49፤ በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት አምስቱ በቀኝ አምስቱም በግራ የሚቀመጡትን ከጥሩ ወርቅ የተሠሩትንም መቅረዞች፥ የወርቁንም አበባዎችና ቀንዲሎች መኰስተሪያዎችም፥
50፤ ከጥሩ ወርቅም የተሠሩትን ጽዋዎችና ጕጠቶች፥ ድስቶቹንና ጭልፋዎቹንም፥ ማንደጃዎቹንም፥ ለውስጠኛውም ቤት ለቅድስተ ቅዱሳን ደጆች ለቤተ መቅደሱም ደጆች የሚሆኑትን የወርቅ ማጠፊያዎች አሠራ።
51፤ እንዲሁ ንጉሡ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ያሠራው ሥራ ሁሉ ተፈጸመ። አባቱም ዳዊት የቀደሰውን፥ ብርና ወርቅ ዕቃም፥ ሰሎሞን አገባ፥ በእግዚአብሔርም ቤት ውስጥ በነበሩ ግምጃ ቤቶች አኖረው።
ምዕራፍ 8

1፤ ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን ያወጡ ዘንድ የእስራኤልን ሽማግሌዎችና የነገድ አለቆችን ሁሉ፥ የእስራኤልን ልጆች የአባቶቻቸውን ቤቶች መሳፍንት፥ ንጉሡ ሰሎሞን ወዳለበት ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰባቸው።
2፤ የእስራኤልም ሰዎች ኤታኒም በሚባል በሰባተኛው ወር በበዓሉ ጊዜ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ተከማቹ።
3፤ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ፤ ካህናቱም ታቦቱን አነሡ።
4፤ የእግዚአብሔርንም ታቦት፥ የመገናኛውንም ድንኳን፥ በድንኳኑም ውስጥ የነበረውን የተቀደሰውን ዕቃ ሁሉ አመጡ፤ እነዚህንም ሁሉ ካህናቱና ሌዋውያኑ አመጡ።
5፤ ንጉሡም ሰሎሞን ከእርሱም ጋር የተሰበሰቡ የእስራኤል ማኅበር ሁሉ ከእርሱ ጋር በታቦቱ ፊት ሆነው፥ ከብዛታቸው የተነሣ የማይቈጠሩትንና የማይመጠኑትን በጎችና በሬዎች ይሠዉ ነበር።
6፤ ካህናቱም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት በቤቱ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ከኪሩቤል ክንፍ በታች ወደ ነበረው ወደ ስፍራው አመጡት።
7፤ ኪሩቤልም በታቦቱ ስፍራ ላይ ክንፎቻቸውን ዘርግተው ነበር፤ ኪሩቤልም ታቦቱንና መሎጊያዎቹን በስተ ላይ በኩል ሸፍነው ነበር።
8፤ መሎጊያዎቹም ረጃጅሞች ነበሩ፤ በቅድስተ ቅዱሳን ፊት ከመቅደሱ ውስጥ ጫፎቻቸው ይታዩ ነበር፤ በውጭ ያለ ግን አያያቸውም ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ አሉ።
9፤ በታቦቱም ውስጥ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር በወጡ ጊዜ፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ባደረገ ጊዜ፥ ሙሴ በኮሬብ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ የድንጋይ ጽላቶች በቀር ምንም አልነበረበትም።
10፤ ካህናቱም ከመቅደሱ በመጡ ጊዜ ደመናው የእግዚአብሔርን ቤት ሞላው።
11፤ የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶ ነበርና ካህናቱ ከደመናው የተነሣ ለማገልገል ይቆሙ ዘንድ አልቻሉም።
12፤ ሰሎሞንም። እግዚአብሔር። በጨለማው ውስጥ እኖራለሁ ብሎአል፤
13፤ እኔም ለዘላለም የምትኖርበት ማደሪያ ቤት በእውነት ሠራሁልህ አለ።
14፤ ንጉሡም ፊቱን ዘወር አድርጎ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ መረቀ፤ የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ቆመው ነበር።
15
16፤ እርሱም አለ። ሕዝቤን እስራኤልን ከግብፅ ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ ስሜ በዚያ ይሆን ዘንድ፥ በእርስዋም ቤት ይሠራልኝ ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ከተማ አልመረጥሁም፤ አሁን ግን ስሜ በዚያ ይሆን ዘንድ ኢየሩሳሌምን መርጫለሁ፥ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ ይሆን ዘንድ ዳዊትን መርጫለሁ ብሎ ለአባቴ ለዳዊት በአፉ የተናገረ፥ በእጁም የፈጸመ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን።
17፤ አባቴም ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ይሠራ ዘንድ በልቡ አሰበ።
18፤ እግዚአብሔርም አባቴን ዳዊትን። ለስሜ ቤት ትሠራ ዘንድ በልብህ አስበሃልና ይህን በልብህ ማሰብህ መልካም አደረግህ።
19፤ ነገር ግን ከወገብህ የሚወጣው ልጅህ እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል እንጂ ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም አለው።
20፤ እግዚአብሔርም የተናገረውን ቃል አጸና፤ እግዚአብሔርም ተስፋ እንደ ሰጠ በአባቴ በዳዊት ፋንታ ተነሣሁ፥ በእስራኤልም ዙፋን ላይ ተቀመጥሁ፥ ለእስራኤልም አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ሠራሁ።
21፤ ከግብጽም ምድር ባወጣቸው ጊዜ ከአባቶቻችን ጋር ያደረገው የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ላለበት ታቦት ስፍራ በዚያ አደረግሁለት።
22፤ የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ እያዩ ሰሎሞን በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ቆሞ እጆቹን ወደ ሰማይ ዘረጋ።
23፤ እንዲህም አለ። የእስራኤል አምላክ አቤቱ፥ በላይ በሰማይ በታችም በምድር አንተን የሚመስል አምላክ የለም፤ በፍጹም ልባቸው በፊትህ ለሚሄዱ ባሪያዎችህ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ፥
24፤ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ የጠበቅህ፤ በአፍህ ተናገርህ፥ እንደ ዛሬው ቀንም በእጅህ ፈጸምኸው።
25፤ አሁንም የእስራኤል አምላክ አቤቱ። አንተ በፊቴ እንደ ሄድህ ልጆችህ መንገዳቸውን ቢጠብቁ፥ በእስራኤል ዙፋን የሚቀመጥ ሰው በፊቴ አታጣም ብለህ ተስፋ የሰጠኸውን ለአባቴ ለዳዊት ጠብቅ።
26፤ አሁንም፥ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የተናገርኸው ቃል፥ እባክህ፥ ይጽና።
27፤ በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፥ ሰማይ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ይልቁንስ እኔ የሠራሁት ቤት እንዴት ያንስ!
28፤ ነገር ግን፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ ወደ ባሪያህ ጸሎትና ልመና ተመልከት፥ ዛሬም ባሪያህ በፊትህ የሚጸልየውን ጸሎትና ጥሪውን ስማ፤
29፤ ባሪያህ ወደዚህ ስፍራ የሚጸልየውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ። በዚያ ስሜ ይሆናል ወዳልኸው ስፍራ ወደዚህ ቤት ዓይኖችህ ሌሊትና ቀን የተገለጡ ይሁኑ።
30፤ ባሪያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ የሚጸልዩትን ልመና ስማ፤ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል።
31፤ ሰው ባልንጀራውን ቢበድል፥ በላዩም መሐላ ቢጫን፥ እርሱም መጥቶ በዚህ ቤት በመሠዊያህ ፊት ቢምል፥
32፤ በሰማይ ስማ አድርግም፤ በባሪያዎችህም ላይ ዳኛ ሁን፤ በበደለኛውም ላይ ፍረድ፥ መንገዱንም በራሱ ላይ መልስበት፤ ንጹሑን አጽድቀው፥ እንደ ጽድቁም ክፈለው።
33፤ ሕዝብህ እስራኤል አንተን ስለ በደሉ በጠላቶቻቸው ፊት ድል በተመቱ ጊዜ፥ ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ስምህንም ቢያከብሩ፥ በዚህም ቤት ቢጸልዩና ቢለምኑህ፥
34፤ አንተ በሰማይ ስማ፤ የሕዝብህንም የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፥ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠሃት ምድር መልሳቸው።
35፤ አንተን ስለ በደሉ ሰማይ በተዘጋ ጊዜ ዝናብም ባልዘነበ ጊዜ፥ ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩ፥ ስምህንም ቢያከብሩ፥ ባስጨነቅሃቸውም ጊዜ ከኃጢአታቸው ቢመለሱ፥ አንተ በሰማይ ስማ፤
36፤ የሚሄዱበትንም መልካም መንገድ በማሳየት የባሪያዎችህንና የሕዝብህን የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፤ ለሕዝብህም ርስት አድርገህ ለሰጠሃት ምድር ዝናብ ስጥ።
37፤ በምድር ላይ ራብ፥ ወይም ቸነፈር፥ ወይም ዋግ፥ ወይም አረማሞ፥ ወይም አንበጣ፥ ወይም ኩብኩባ ቢሆን፥ የሕዝብህም ጠላት የአገሩን ቀበሌዎች ከብቦ ቢያስጨንቃቸው፥ መቅሠፍትና ደዌ ሁሉ ቢሆን፥
38፤ ማናቸውም ሰው የልቡን ሕመም አውቆ ጸሎትና ልመና ቢጸልይ፥ እጆቹንም ወደዚህ ቤት ቢዘረጋ፥
39
40፤ ለአባቶቻችን በሰጠሃት ምድር ላይ በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ ይፈሩህ ዘንድ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፥ ይቅርም በል፤ አንተ ብቻ የሰውን ልጆች ሁሉ ልብ ታውቃለህና ልቡን ለምታውቀው ሰው ሁሉ እንደ መንገዱ ሁሉ መጠን ክፈለውና ስጠው።
41
42፤ ከሕዝብህም ከእስራኤል ወገን ያልሆነ እንግዳ ታላቁን ስምህን፥ ብርቱይቱንም እጅህን፥ የተዘረጋውንም ክንድህን ሰምቶ ስለ ስምህ ከሩቅ አገር በመጣ ጊዜ፥ መጥቶም ወደዚህ ቤት በጸለየ ጊዜ፥
43፤ አንተ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ ስምህን ያውቁ ዘንድ እንደ ሕዝብህም እንደ እስራኤል ይፈሩህ ዘንድ፥ በዚህም በሠራሁት ቤት ስምህ እንደተጠራ ያውቁ ዘንድ፥ እንግዳው የሚለምንህን ሁሉ አድርግ።
44፤ ሕዝብህም ጠላቶቻቸውን ለመውጋት አንተ በምትልካቸው መንገድ ቢወጡ፥ አንተም ወደ መረጥሃት ከተማ እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤት ለእግዚአብሔር ቢጸልዩ፥
45፤ ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በሰማይ ስማ፥ ፍርድንም አድርግላቸው።
46፤ የማይበድልም ሰው የለምና አንተን ቢበድሉ፥ ተቈጥተህም ለጠላቶቻቸው አሳልፈህ ብትሰጣቸው ሩቅ ወይም ቅርብ ወደ ሆነ ወደ ጠላቶች አገር ቢማረኩም፥
47፤ በተማረኩበትም አገር ሆነው በልባቸው ንስሐ ቢገቡ፥ በማራኪዎቹም አገር ሳሉ ተመልሰው። ኃጢአት ሠርተናል፥ በድለንማል፥ ክፉንም አድርገናል ብለው ቢለምኑህ፥
48፤ በማረኩአቸው በጠላቶቻቸው አገር ሳሉ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃት ወደ ምድራቸው ወደ መረጥሃትም ከተማ ለስምህም ወደ ሠራሁት ቤት ቢጸልዩ፥
49፤ ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በማደሪያህ በሰማይ ስማ፥
50፤ ፍርድንም አድርግላቸው፥ አንተንም የበደሉህን ሕዝብህን፥ በአንተም ላይ ያደረጉትን በደላቸውን ሁሉ ይቅር በል፤ ይራሩላቸውም ዘንድ በማረኩአቸው ፊት ምሕረት ስጣቸው፤
51፤ ከግብፅ ምድር ከብረት እቶን ውስጥ ያወጣሃቸው ሕዝብህና ርስትህ ናቸውና።
52፤ በጠሩህ ጊዜ ሁሉ ትሰማቸው ዘንድ ለባሪያህና ለሕዝብህ ለእስራኤል ልመና ዓይኖችህ የተገለጡ ይሁኑ።
53፤ ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አባቶቻችንን ከግብጽ ባወጣህ ጊዜ በባሪያህ በሙሴ እጅ እንደ ተናገርህ ርስት ይሆኑህ ዘንድ ከምድር አሕዛብ ሁሉ ለይተሃቸዋልና።
54፤ ሰሎሞንም ይህችን ጸሎትና ልመና ሁሉ ለእግዚአብሔር ጸልዮ በፈጸመ ጊዜ፥ በጕልበቱ ተንበርክኮ እጁንም ወደ ሰማይ ዘርግቶ ነበርና ከእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ተነሣ።
55፤ ቆሞም የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ በታላቅ ድምፅ ሲመርቅ እንዲህ አለ።
56፤ እንደ ተናገረው ተስፋ ሁሉ ለሕዝቡ ለእስራኤል ዕረፍትን የሰጠ እግዚአብሔር ይመስገን፤ በባሪያው በሙሴ ከሰጠው ከመልካም ተስፋ ሁሉ አንድ ቃል አልወደቀም።
57፤ አምላካችን እግዚአብሔር ከአባቶቻችን ጋር እንደ ነበረ ከእኛ ጋር ይሁን፤ አይተወን፥ አይጣለንም፤
58፤ በመንገዱም ሁሉ እንሄድ ዘንድ፥ ለአባቶቻችንም ያዘዛትን ሥርዓትና ፍርድ ትእዛዙንም እንጠብቅ ዘንድ፥ ልባችንን ወደ እርሱ ያዘነብል ዘንድ።
59፤ ለባሪያውና ለሕዝቡ ለእስራኤል በየዕለቱ ፍርድን ያደርግ ዘንድ ይህች በእግዚአብሔር ፊት የለመንኋት ቃል በቀንና በሌሊት ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር የቀረበች ትሁን፤
60፤ የምድር አሕዛብ ሁሉ እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ፥ ከእርሱም በቀር ሌላ እንደሌለ ያውቅ ዘንድ።
61፤ እንደ ዛሬው ቀን በሥርዓቱ ትሄዱ ዘንድ፥ ትእዛዙንም ትጠብቁ ዘንድ፥ ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ጋር ልባችሁ ፍጹም ይሁን።
62፤ ንጉሡም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕት ሠዉ።
63፤ ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ይሠዋ ዘንድ ለደኅንነት መሥዋዕት ሀያ ሁለት ሺህ በሬዎችና መቶ ሀያ ሺህ በጎች አቀረበ። ንጉሡና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ የእግዚአብሔርን ቤት ቀደሱ።
64፤ በእግዚአብሔር ፊት ያለው የናሱ መሠዊያ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቁርባን የደኅንነቱንም መሥዋዕት ስብ ይይዝ ዘንድ ታናሽ ስለ ነበረ፥ በዚያ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን የደኅንነቱንም መሥዋዕት ስብ አሳርጎአልና በእግዚአብሔር ቤት ፊት የነበረውን የአደባባዩ መካከል ንጉሡ በዚያ ቀን ቀደሰ።
65፤ በዚያም ዘመን ሰሎሞን ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ፥ ከሐማት መግቢያ ጀምሮ እስከ ግብጽ ወንዝ ድረስ ያለው ታላቅ ጉባኤ፥ በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ቀን በዓሉን አደረጉ።
66፤ በስምንተኛውም ቀን ሕዝቡን አሰናበተ፤ እነርሱም ንጉሡን መረቁ፥ እግዚአብሔርም ለባሪያው ለዳዊትና ለሕዝቡ ለእስራኤል ስላደረገው ቸርነት ሁሉ በልባቸው ተደስተው ሐሤትም አድርገው ወደ ስፍራቸው ሄዱ። a
ምዕራፍ 9

1፤ ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤት፥ የንጉሡን ቤትና ሰሎሞን የወደደውን የልቡን አሳብ ሁሉ ሠርቶ በፈጸመ ጊዜ፥
2፤ እግዚአብሔር በገባዖን ለሰሎሞን እንደ ተገለጠለት ዳግመኛ ተገለጠለት።
3፤ እግዚአብሔርም አለው። በፊቴ የጸለይኸውን ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቻለሁ፤ ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዓይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ።
4፤ ዳዊትም አባትህ በየዋህ ልብና በቅንነት እንደ ሄደ አንተ ደግሞ በፊቴ ብትሄድ፥ ያዘዝሁህንም ሁሉ ብታደርግ፥ ሥርዓቴንም ፍርዴንም ብትጠብቅ፥
5፤ እኔ። ከእስራኤል ዙፋን ከዘርህ ሰው አታጣም ብዬ ለአባትህ ለዳዊት እንደ ተናገርሁ፥ የመንግሥትህን ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ።
6፤ እናንተና ልጆቻችሁ ግን እኔን ከመከትል ብትመለሱ፥ የሰጠኋችሁንም ትእዛዜንና ሥርዓቴን ባትጠብቁ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታመልኩ፥ ብትሰግዱላቸውም፥
7፤ እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድር አጠፋቸዋለሁ፤ ለስሜም የቀደስሁትን ይህን ቤት ከፊቴ እጥለዋለሁ፤ እስራኤልም በአሕዛብ ሁሉ መካከል ምሳሌና ተረት ይሆናሉ።
8፤ ከፍ ከፍ ብሎ የነበረውም ይህ ቤት ባድማ ይሆናል፤ በዚያም የሚያልፍ ሁሉ እያፍዋጨ። እግዚአብሔር በዚህ አገርና በዚህ ቤት ስለምን እንዲህ አደረገ? ብሎ ይደነቃል።
9፤ መልሰውም። ከግብጽ ምድር አባቶቻቸውን ያወጣውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ትተው ሌሎችንም አማልክት ስለ ተከተሉ፥ ስለ ሰገዱላቸውም፥ ስለ አመለኩአቸውም፥ ስለዚህ እግዚአብሔር ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣባቸው ይላሉ።
10፤ ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤትና የንጉሡን ቤት ሁለቱን ቤቶች የሠራበት ሀያ ዓመት በተፈጸመ ጊዜ፥
11፤ ንጉሡ ሰሎሞን በገሊላ ምድር ያሉትን ሀያ ከተሞች ለኪራም ሰጠው። የጢሮስም ንጉሥ ኪራም የሚሻውን ያህል የዝግባና የጥድ እንጨት የሚሻውንም ያህል ወርቅ ሁሉ ለሰሎሞን ሰጥቶት ነበር።
12፤ ኪራምም ሰሎሞን የሰጠውን ከተሞች ያይ ዘንድ ከጢሮስ ወጣ፤ ደስም አላሰኙትም።
13፤ እርሱም። ወንድሜ ሆይ፥ የሰጠኸኝ እነዚህ ከተሞች ምንድር ናቸው? አለ። እስከ ዛሬም ድረስ የከቡል አገር ተብለው ተጠሩ።
14፤ ኪራምም መቶ ሀያ መክሊት ወርቅ ለንጉሡ ላከ።
15፤ ንጉሡም ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤትና የራሱን ቤት፥ ሚሎንም፥ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር፥ ሐጾርንም፥ መጊዶንም፥ ጌዝርንም ይሠራ ዘንድ ገባሮችን መልምሎ ነበር።
16፤ የግብጽም ንጉሥ ፈርዖን ወጥቶ ጌዝርን ይዞ ነበር፥ በእሳትም አቃጥሎ ነበር፥ በከተማም የኖሩትን ከነዓናውያን ገድሎ ነበር፤ ለልጁም ለሰሎምን ሚስት ትሎት አድርጎ ሰጥቶአት ነበር።
17፤ ሰሎሞንም ጌዝርን፥ የታችኛውንም ቤት
18፤ ሖሮን፥ ባዕላትንም፥ በምድረ በዳም አገር ያለችውን ተድሞርን፥
19፤ ለሰሎሞንም የነበሩትን የዕቃ ቤት ከተሞች ሁሉ፥ የሰረገላውንም ከተሞች፥ የፈረሰኞችንም ከተሞች፥ በኢየሩሳሌምም በሊባኖስም በመንግሥቱም ምድር ሁሉ ሰሎሞን ይሠራ ዘንድ የወደደውን ሁሉ ሠራ።
20፤ ከእስራኤልም ልጆች ዘንድ ያልነበሩትን ከአሞራውያንና ከኬጢያውያን፥ ከፌርዛውያን፥ ከኤዊያውያንና ከኢያቡሳውያን የቀሩትን፥
21፤ የእስራኤልም ልጆች ያጠፉአቸው ዘንድ ያልቻሉትን፥ በኋላቸው የቀሩትን ልጆቻቸውን፥ ሰሎሞን እስከ ዛሬ ድረስ ገባሮች አድርጎ መለመላቸው።
22፤ ሰሎሞንም ከእስራኤል ልጆች ማንንም ባሪያ አላደረገም፤ እነርሱ ግን ሰልፈኞች፥ ሎሌዎችም፥ መሳፍንትም፥ አለቆችም፥ የሰረገሎችና የፈረሶች ባልደራሶች ነበሩ።
23፤ ሰሎሞንም በሚሠራው ሥራ ላይ ሠራተኛውን ሕዝብ የሚያዝዙ አለቆች አምስት መቶ አምሳ ነበሩ።
24፤ የፈርዖንም ልጅ ከዳዊት ከተማ ሰሎሞን ወደ ሠራላት ወደ ቤትዋ ወጣች በዚያን ጊዜም ሚሎን ሠራ።
25፤ ሰሎሞንም በየዓመቱ ሦስት ጊዜ የሚቃጠለውንና የደኅንነቱን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በሠራው መሠዊያ ላይ ያሳርግ ነበር፤ በእግዚአብሔር ፊት ባለው መሠዊያ ላይ ዕጣን ያሳርግ ነበር፤ ቤቱንም ጨረሰ።
26፤ ንጉሡም ሰሎሞን በኤዶምያስ ምድር በኤርትራ ባሕር ዳር በኤሎት አጠገብ ባለችው በዔጽዮንጋብር መርከቦችን ሠራ።
27፤ ኪራምም በእነዚያ መርከቦች ከሰሎሞን ባሪያዎች ጋር የባሕሩን ነገር የሚያውቁ መርከበኞች ባሪያዎቹን ሰደደ።
28፤ ወደ ኦፊርም መጡ፥ ከዚያም አራት መቶ ሀያ መክሊተ ወርቅ ወሰዱ፥ ወደ ንጉሡም ወደ ሰሎሞን ይዘው መጡ።
ምዕራፍ 10

1፤ የሳባም ንግሥት በእግዚአብሔር ስም የወጣለትን የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች።
2፤ በግመሎችም ላይ ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ የከበረም ዕንቍ አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ገባች፤ ወደ ሰሎሞንም በመጣች ጊዜ በልብዋ ያለውን ሁሉ አጫወተችው።
3፤ ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ ፈታላት፤ ሊፈታላት ያልቻለውና ከንጉሡ የተሰወረ ነገር አልነበረም።
4፤ የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ ሁሉ፥ ሠርቶትም የነበረውን ቤት፥
5፤ የማዕዱንም መብል፥ የብላቴኖቹንም አቀማመጥ፥ የሎሌዎቹንም አሠራር አለባበሳቸውንም፥ ጠጅ አሳላፊዎቹንም፥ በእግዚአብሔርም ቤት የሚያሳርገውን መሥዋዕት ባየች ጊዜ ነፍስ አልቀረላትም።
6፤ ንጉሡንም አለችው። ስለ ነገርህና ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ዝና እውነት ነው።
7፤ እኔም መጥቼ በዓይኔ እስካይ ድረስ የነገሩኝን አላመንሁም ነበር፤ እነሆም፥ እኩሌታውን አልነገሩኝም ነበር፤ ጥበብህና ሥራህ ከሰማሁት ዝና ይበልጣል።
8፤ በፊትህ ሁልጊዜ የሚቆሙ ጥበብህንም የሚሰሙ ሰዎችህና እነዚህ ባሪያዎችህ ምስጉኖች ናቸው።
9፤ አንተን የወደደ፥ በእስራኤልም ዙፋን ያስቀመጠህ አምላክህ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን፤ እግዚአብሔር እስራኤልን ለዘላለም ወድዶታልና ስለዚህ ጽድቅና ፍርድ ታደርግ ዘንድ ንጉሥ አድርጎ አስነሣህ።
10፤ ለንጉሡም መቶ ሀያ መክሊት ወርቅ እጅግም ብዙ ሽቱ የከበረም ዕንቍ ሰጠችው፤ የሳባ ንግሥት ለንጉሡ ለሰሎሞን እንደ ሰጠችው ያለ የሽቱ ብዛት ከዚያ ወዲያ አልመጣም ነበር።
11፤ ከኦፊርም ወርቅ ያመጡ የኪራም መርከቦች እጅግ ብዙ የሰንደል እንጨትና የከበረ ዕንቍ ከኦፊር አመጡ።
12፤ ንጉሡም ከሰንደሉ እንጨት ለእግዚአብሔር ቤትና ለንጉሡ ቤት መከታ፥ ለመዘምራኑም መሰንቆና በገና አደረገ፤ እስከ ዛሬም ድረስ እንደዚያ ያለ የሰንደል እንጨት ከቶ አልመጣም አልታየምም።
13፤ ንጉሡም ሰሎሞን፥ በገዛ እጁ ከሰጣት ሌላ፥ የወደደችውን ሁሉ ከእርሱም የለመነችውን ሁሉ ለሳባ ንግሥት ሰጣት፤ እርስዋም ተመልሳ ከባሪያዎችዋ ጋር ወደ ምድርዋ ሄደች።
14
15፤ ግብርም የሚያስገብሩ ሰዎች ነጋዴዎችም የዓረብም ነገሥታት ሁሉ የምድርም ሹማምት ከሚያወጡት ሌላ፥ በየዓመቱ ለሰሎሞን የሚመጣለት የወርቅ ሚዛን ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት መክሊት ወርቅ ነበረ።
16፤ ንጉሡም ሰሎሞን ከጥፍጥፍ ወርቅ ሁለት መቶ አላበሽ አግሬ ጋሻ አሠራ፤ በአንዱም አላባሽ አግሬ ጋሻ ውስጥ የገባው ወርቅ ስድስት መቶ ሰቅል ነበረ።
17፤ ከጥፍጥፍም ወርቅ ሦስት መቶ ጋሻ አሠራ፤ በአንዱም ጋሻ የገባው ወርቅ ሦስት ምናን ነበረ፤ ንጉሡም የሊባኖስ ዱር በተባለው ቤት ውስጥ አኖራቸው።
18፤ ንጉሡም ደግሞ ከዝሆን ጥርስ ታላቅ ዙፋን አሠራ፥ በጥሩም ወርቅ ለበጠው።
19፤ ወደ ዙፋንም የሚያስሄዱ ስድስት እርከኖች ነበሩ፤ በስተ ኋላውም ያለው የዙፋኑ ራስ ክብ ነበረ፤ በዚህና በዚያ በመቀመጫው አጠገብ ሁለት የክንድ መደገፊያዎች ነበሩበት፥ በመደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር።
20፤ በስድስቱም እርከኖች ላይ በዚህና በዚያ አሥራ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር፤ በመንግሥታት ሁሉ እንዲህ ያለ ሥራ አልተሠራም።
21፤ ንጉሡም ሰሎሞን የሚጠጣበት ዕቃ ሁሉ ወርቅ ነበረ፥ የሊባኖስ ዱር የተባለውም ቤት ዕቃ ሁሉ ጥሩ ወርቅ እንጂ ብር አልነበረም። በሰሎሞን ዘመን ብር ከቶ አይቈጠርም ነበር።
22፤ ለንጉሡም ከኪራም መርከቦች ጋር የተርሴስ መርከቦች ነበሩት፤ በሦስት በሦስት ዓመትም አንድ ጊዜ የተርሴስ መርከቦች ወርቅና ብር፥ የዝሆንም ጥርስ፥ ዝንጀሮና ዝንጕርጕር ወፍ ይዘው ይመጡ ነበር።
23፤ ንጉሡም ሰሎሞን በባለጠግነትና በጥበብ ከምድር ነገሥታት ሁሉ በልጦ ነበር።
24፤ ምድርም ሁሉ እግዚአብሔር በልቡ ያኖረለትን ጥበቡን ይሰማ ዘንድ የሰሎሞንን ፊት ይመኝ ነበር።
25፤ ከእነርሱም እያንዳንዱ በዓመቱ በዓመቱ ገጸ በረከቱን፥ የብርና የወርቅ ዕቃ፥ ልብስና የጦር መሣሪያ፥ ሽቱም፥ ፈረሶችና በቅሎች እየያዘ ይመጣ ነበር።
26፤ ሰሎሞንም ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን ሰበሰበ፤ አንድ ሺህ አራት መቶ ሰረገሎች፥ አሥራ ሁለት ሺህም ፈረሰኞች ነበሩት፥ በሰረገሎችም ከተሞች ከንጉሡም ጋር በኢየሩሳሌም አኖራቸው።
27፤ ንጉሡም ብሩን በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ እንዲበዛ አደረገው፤ የዝግባም እንጨት ብዛት በቈላ እንደሚበቅል ሾላ ሆነ።
28፤ ሰሎሞንም ፈረሶችን ከግብጽና ከቀዌ አገር አስመጣ፤ የንጉሡም ነገዴዎች በገንዘብ እየገዙ ከቀዌ ያመጡአቸው ነበር።
29፤ አንዱም ሰረገላ በስድስት መቶ፥ አንዱም ፈረስ በመቶ አምሳ ብር ከግብጽ ይወጣ ነበር። እንዲሁም ለኬጢያውያንና ለሶርያ ነገሥታት ሁሉ በእጃቸው ያወጡላቸው ነበር። a
ምዕራፍ 11

1፤ ንጉሡም ሰሎሞን ከፈርዖን ልጅ ሌላ፥ በሞዓባውያንና በአሞናውያን በኤዶማውያን በሲዶናውያንና በኬጢያውያን ሴቶች፥ በብዙ እንግዶች ሴቶች ፍቅር ተነደፈ።
2፤ እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች። አምላኮቻቸውን ትከተሉ ዘንድ ልባችሁን በእውነት ያዘነብላሉና ወደ እነርሱ አትግቡ፥ እነርሱም ወደ እናንተ አይግቡ ካላቸው ከአሕዛብ፥ ከእነዚህ ጋር ሰሎሞን በፍቅር ተጣበቀ።
3፤ ለእርሱም ወይዛዝር የሆኑ ሰባት መቶ ሚስቶች ሦስት መቶም ቁባቶች ነበሩት፤ ሚስቶቹም ልቡን አዘነበሉት።
4፤ ሰሎሞንም ሲሸመግል ሚስቶቹ ሌሎችን አማልክት ይከተል ዘንድ ልቡን አዘነበሉት፤ የአባቱ የዳዊት ልብ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም እንደ ነበረ የሰሎሞን ልቡ እንዲሁ አልነበረም።
5፤ ሰሎሞንም የሲዶናውያንን አምላክ አስታሮትን፥ የአሞናውያንንም ርኵሰት ሚልኮምን፥ ተከተለ።
6፤ ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አደረገ፥ እንደ አባቱም እንደ ዳዊት እግዚአብሔርን በመከተል ፍጹም አልሆነም።
7፤ በዚያን ጊዜም ሰሎሞን ለሞዓብ ርኵሰት ለካሞሽ፥ ለአሞንም ልጆች ርኵሰት ለሞሎክ በኢየሩሳሌም ፊት ለፊት ባለው ተራራ ላይ መስገጃ ሠራ።
8፤ ለአማልክቶቻቸው ዕጣን ለሚያጥኑ መሥዋዕትም ለሚሠዉ ለእንግዶች ሚስቶቹ ሁሉ እንዲሁ አደረገ።
9
10፤ ሁለት ጊዜም ከተገለጠለት፥ ሌሎችንም አማልክት እንዳይከተል ካዘዘው ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ልቡን አርቆአልና፥ እግዚአብሔርም ያዘዘውን ነገር አልጠበቀምና እግዚአብሔር ሰሎሞንን ተቈጣ።
11፤ እግዚአብሔርም ሰሎሞንን አለው። ይህን ሠርተሃልና፥ ያዘዝሁህንም ቃል ኪዳኔንና ሥርዓቴን አልጠበቅህምና መንግሥትህን ከአንተ ቀዳድጄ ለባሪያህ እሰጠዋለሁ።
12፤ ነገር ግን ከልጅህ እጅ እቀድደዋለሁ እንጂ ስለ አባትህ ስለ ዳዊት ይህን በዘመንህ አላደርግም።
13፤ ነገር ግን ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊትና ስለ መረጥኋት ስለ ኢየሩሳሌም ለልጅህ አንድ ነገድ እሰጣለሁ እንጂ መንግሥቱን ሁሉ አልቀድድም።
14፤ እግዚአብሔርም ከኤዶምያስ ነገሥታት ዘር የኤዶምያስን ሰው ሃዳድን ጠላት አድርጎ በሰሎሞን ላይ አስነሣው።
15
16፤ ኢዮአብና እስራኤልም ሁሉ የኤዶምያስን ወንድ ሁሉ እስኪገድሉ ድረስ ስድስት ወር በዚያ ተቀምጠው ነበርና ዳዊት በኤዶምያስ በነበረ ጊዜ፥ የሠራዊቱም አለቃ ኢዮአብ ተወግተው የሞቱትን ሊቀብር በወጣ ጊዜ፥ የኤዶምያስንም ወንድ ሁሉ በገደለ ጊዜ፥
17፤ ሃዳድ ገና ብላቴና ሳለ ሃዳድና ከእርሱ ጋር ጥቂቶቹ ከኤዶምያስ ሰዎች የሆኑ የአባቱ ባሪያዎች ወደ ግብጽ ኰብልለው ነበር።
18፤ ከምድያምም ተነሥተው ወደ ፋራን መጡ፤ ከእነርሱም ጋር ከፋራን ሰዎች ወሰዱ፥ ወደ ግብጽም መጡ፥ ወደ ግብጽም ንጉሥ ወደ ፈርዖን ዘንድ ገቡ፤ እርሱም ቤት ሰጥቶ ቀለብ ዳረገው፥ ምድርም ሰጠው።
19፤ የሚስቱንም የእቴጌይቱን የቴቄምናስን እኅት እስኪያጋባው ድረስ ሃዳድ በፈርዖን ፊት እጅግ ባለምዋል ሆነ።
20፤ የቴቄምናስ እኅት ጌንባትን ወለደችለት፥ ቴቄምናስም በፈርዖን ቤት አሳደገችው፤ ጌንባትም በፈርዖን ቤት በፈርዖን ልጆች መካከል ነበረ።
21፤ ሃዳድም በግብጽ ሳለ ዳዊት ከአባቶቹ ጋር እንዳንቀላፋ፥ የሠራዊቱም አለቃ ኢዮአብ እንደ ሞተ በሰማ ጊዜ፥ ሃዳድ ፈርዖንን። ወደ አገሬ እሄድ ዘንድ አሰናብተኝ አለው።
22፤ ፈርዖንም። እነሆ፥ ከእኔ ዘንድ ወደ አገርህ መሄድ የፈለግህ ምን አጥተህ ነው? አለው። እርሱም። አንዳች አላጣሁም፤ ነገር ግን ልሂድ ብሎ መለሰ። ሃዳድም ወደ አገሩ ተመለሰ፥ ሃዳድም ያደረገው ክፉ ነገር ይህ ነው፤ እስራኤልን አስጨነቀ፥ በኤዶምያስም ላይ ነገሠ።
23፤ እግዚአብሔርም ደግሞ ከጌታው ከሱባ ንጉሥ ከአድርአዛር የኰበለለውን የኤልያዳን ልጅ ሬዞንን ጠላት አድርጎ አስነሣበት።
24፤ ዳዊትም የሱባን ሰዎች በገደለ ጊዜ ሬዞን ሰዎችን ሰብስቦ የጭፍራ አለቃ ሆነ፤ ወደ ደማስቆም ሄዱ፥ በዚያም ተቀመጡ፤ በደማስቆም ላይ አነገሡት።
25፤ ሃዳድም ካደረገው ክፋት ሌላ በሰሎሞን ዘመን ሁሉ የእስራኤል ጠላት ነበረ።
26፤ ከሳሪራ አገር የሆነ የሰሎሞን ባሪያ የኤፍሬማዊው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በንጉሡ ላይ ዐመፀ፤ እናቱም ጽሩዓ የተባለች ባልቴት ሴት ነበረች።
27፤ በንጉሡም ያመፀበት ምክንያት ይህ ነው፤ ሰሎሞን ሚሎን ሠራ፥ የአባቱንም የዳዊትን ከተማ ሰባራውን ጠገነ።
28፤ ኢዮርብዓምም ጽኑዕ ኃያል ሰው ነበረ፤ ሰሎሞንም ጕልማሳው በሥራ የተመሰገነ መሆኑን ባየ ጊዜ በዮሴፍ ነገድ ሥራ ሁሉ ላይ ሾመው።
29፤ በዚያን ጊዜም ኢዮርብዓም ከኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ ሴሎናዊው ነቢዩ አኪያ በመንገድ ላይ ተገናኘው፤ አኪያም አዲስ ልብስ ለብሶ ነበር ሁለቱም በሜዳው ለብቻቸው ነበሩ።
30፤ አኪያም የለበሰውን አዲስ ልብስ ይዞ ከአሥራ ሁለት ቈራረጠው።
31፤ ኢዮርብዓምንም አለው። አሥር ቍራጭ ውሰድ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ ከሰሎሞን እጅ መንግሥቱን እቀድዳለሁ፥ አሥሩንም ነገዶች እሰጥሃለሁ፤
32፤ ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ከእስራኤልም ነገድ ስለ መረጥኋት ከተማ ስለ ኢየሩሳሌም ግን አንድ ነገድ ይቀርለታል፤
33፤ ጥለውኛልና፥ ለሲዶናውያንም አምላክ ለአስታሮት፥ ለሞዓብም አምላክ ለካሞሽ፥ ለአሞንም ልጆች አምላክ ለሚልኮም ሰግደዋልና፥ አባቱም ዳዊት እንዳደረገ በፊቴ ቅን ነገር ያደርጉ ዘንድ፥ ሥርዓቴንና ፍርዴንም ይጠብቁ ዘንድ በመንገዴ አልሄዱምና።
34፤ መንግሥቱንም ሁሉ ከእጁ አልወስድም፤ ትእዛዜንና ሥርዓቴን ስለ ጠበቀው ስለ መረጥሁት ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ግን በዕድሜው ሁሉ አለቃ አደርገዋለሁ።
35፤ መንግሥቱንም ከልጁ እጅ እወስዳለሁ፥ ለአንተም አሥሩን ነገድ እሰጥሃለሁ።
36፤ ስሜንም ባኖርሁባት በዚያች በመረጥኋት ከተማ በኢየሩሳሌም ለባሪያዬ ለዳዊት በፊቴ ሁልጊዜ መብራት ይሆንለት ዘንድ ለልጁ አንድ ነገድ እሰጠዋለሁ።
37፤ አንተንም እወስድሃለሁ፥ ነፍስህም በወደደችው ሁሉ ላይ ትነግሣለች፥ በእስራኤልም ላይ ንጉሥ ትሆናለህ።
38፤ ባሪያዬም ዳዊት እንዳደረገ፥ ያዘዝሁህን ሁሉ ብትሰማ፥ በመንገዴም ብትሄድ፥ በፊቴም የቀናውን ብታደርግ፥ ሥርዓቴንና ትእዛዜን ብትጠብቅ፥ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ ለዳዊትም እንደ ሠራሁለት ጽኑ ቤት እሠራልሃለሁ፥ እስራኤልንም ለአንተ እሰጥሃለሁ።
39፤ ስለዚህም የዳዊትን ዘር አስጨንቃለሁ፤ ነገር ግን በዘመን ሁሉ አይደለም።
40፤ ሰሎሞንም ኢዮርብዓምን ሊገድለው ወደደ፤ ኢዮርብዓምም ተነሥቶ ወደ ግብጽ ኰበለለ፥ ወደ ግብጽም ንጉሥ ወደ ሺሻቅ መጣ፥ ሰሎሞንም እስኪሞት ድረስ በግብጽ ተቀመጠ።
41፤ የቀረውም የሰሎሞን ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ጥበቡም፥ እነሆ፥ በሰሎሞን ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል።
42፤ ሰሎሞንም በኢየሩሳሌም በእስራኤል ሁሉ ላይ የነገሠበት ዘመን አርባ ዓመት ነበረ።
43፤ ሰሎሞንም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በአባቱም በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም ሮብዓም በፋንታው ነገሠ።
ምዕራፍ 12

1፤ እስራኤል ሁሉ ያነግሡት ዘንድ ወደ ሴኬም መጥተው ነበርና ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ።
2፤ እንዲህም ሆነ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ይህን በሰማ ጊዜ፥ እርሱም ከንጉሡ ከሰሎሞን ፊት ኰብልሎ በግብጽ ተቀምጦ ነበርና፥ በግብጽም ሳለ ልከው ጠርተውት ነበርና
3፤ ኢዮርብዓምና የእስራኤል ጉባኤ ሁሉ መጥተው ለሮብዓም።
4፤ አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፤ አሁንም አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ፥ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቃልልልን፤ እኛም እንገዛልሃለን ብለው ተናገሩት።
5፤ እርሱም። ሂዱ፥ በሦስተኛውም ቀን ወደ እኔ ተመለሱ አላቸው። ሕዝቡም ሄዱ።
6፤ ንጉሡም ሮብዓም። ለዚህ ሕዝብ እመልስለት ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው? ብሎ አባቱ ሰሎሞን በሕይወቱ ሳለ በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ሽማግሌዎች ጋር ተማከረ።
7፤ እነርሱም። ለዚህ ሕዝብ አሁን ባሪያ ብትሆን ብትገዛላቸውም፥ መልሰህም በገርነት ብትናገራቸው፥ በዘመኑ ሁሉ ባሪያዎች ይሆኑልሃል ብለው ተናገሩት።
8፤ እርሱ ግን ሽማግሌዎች የመከሩትን ምክር ትቶ ከእርሱ ጋር ካደጉትና በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ብላቴኖች ጋር ተማከረ።
9፤ እርሱም። አባትህ የጫኑብንን ቀንበር አቃልልልን ለሚሉኝ ሕዝብ እመልስላቸው ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው? አላቸው።
10፤ ከእርሱም ጋር ያደጉት ብላቴኖች። አባትህ ቀንበር አክብዶብናል፥ አንተ ግን አቃልልልን ለሚሉህ ሕዝብ። ታናሺቱ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች።
11፤ አሁንም አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችኋል፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችኋል፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ በላቸው ብለው ተናገሩት።
12፤ ንጉሡም። በሦስተኛው ቀን ወደ እኔ ተመለሱ ብሎ እንደ ተናገረ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓም መጡ።
13፤ ንጉሡም ሽማግሌዎች የመከሩትን ምክር ትቶ ለሕዝቡ ጽኑ ምላሽ መለሰላቸው።
14፤ እንደ ብላቴኖችም ምክር። አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ ብሎ ተናገራቸው።
15፤ እግዚአብሔርም በሴሎናዊው በአኪያ አድርጎ ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብዓም የተናገረውን ነገር እንዲያጸና ከእግዚአብሔር ዘንድ ተመድቦ ነበርና ንጉሡ ሕዝቡን አልሰማም።
16፤ እስራኤልም ሁሉ ንጉሡ እንዳልሰማቸው ባዩ ጊዜ ሕዝቡ ለንጉሡ። በዳዊት ዘንድ ምን ክፍል አለን? በእሴይም ልጅ ዘንድ ርስት የለንም። እስራኤል ሆይ፥ ወደ ድንኳኖቻችሁ ተመለሱ፤ ዳዊት ሆይ፥ አሁን ቤትህን ተመልከት ብለው መለሱለት። እስራኤልም ወደ ድንኳኖቻቸው ሄዱ።
17፤ በይሁዳ ከተሞች በተቀመጡት በእስራኤል ልጆች ላይ ግን ሮብዓም ነገሠባቸው።
18፤ ንጉሡም ሮብዓም አስገባሪውን አዶኒራምን ሰደደ፤ እስራኤልም ሁሉ በድንጋይ ደበደቡት፥ ሞተም። ንጉሡም ሮብዓም ፈጥኖ ወደ ሰረገላው ወጣ ወደ ኢየሩሳሌምም ሸሸ።
19፤ እስራኤልም እስከ ዛሬ ድረስ ከዳዊት ቤት ሸፈተ።
20፤ እስራኤልም ሁሉ ኢዮርብዓም እንደ ተመለሰ በሰሙ ጊዜ ልከው ወደ ሸንጎአቸው ጠሩት፥ በእስራኤልም ሁሉ ላይ አነገሡት። ከብቻው ከይሁዳ ነገድ በቀረ የዳዊትን ቤት የተከተለ አንድ ሰው አልነበረም።
21፤ ሮብዓምም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፥ የእስራኤልንም ቤት ወግተው መንግሥቱን ወደ ሰሎሞን ልጅ ወደ ሮብዓም ይመልሱ ዘንድ ከይሁዳ ቤት ሁሉና ከብንያም ነገድ የተመረጡትን አንድ መቶ ሰማንያ ሺህ ሰልፈኞች ሰዎች ሰበሰበ።
22፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ሳማያ።
23፤ ለይሁዳ ንጉሥ ለሰሎሞን ልጅ ለሮብዓምና ለይሁዳ ለብንያምም ቤት ሁሉ ለቀረውም ሕዝብ ሁሉ።
24፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህ ነገር ከእኔ ዘንድ ነውና አትውጡ፥ የእስራኤልንም ልጆች ወንድሞቻችሁን አትውጉ፤ እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ይመለስ ብለህ ንገራቸው ሲል መጣ። የእግዚአብሔርንም ቃል ሰሙ፥ እንደ እግዚአብሔርም ቃል ተመልሰው ሄዱ።
25፤ ኢዮርብዓምም በተራራማው በኤፍሬም አገር ሴኬምን ሠርቶ በዚያ ተቀመጠ፤ ደግሞም ከዚያ ወጥቶ ጵኒኤልን ሠራ።
26፤ ኢዮርብዓምም በልቡ። አሁን መንግሥቱ ወደ ዳዊት ቤት ይመለሳል።
27፤ ይህ ሕዝብ በእግዚአብሔር ቤት መሥዋዕትን ያቀርብ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ቢወጣ፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ወደ ጌታቸው ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሮብዓም ይመለሳል፥ እኔንም ይገድሉኛል አለ።
28፤ ንጉሡም ተማከረ፥ ሁለትም የወርቅ ጥጆች አድርጎ። እስራኤል ሆይ፥ ወደ ኢየሩሳሌም ትወጡ ዘንድ ይበዛባችኋል፤ ከግብጽ ምድር ያወጡህን አማልክቶችህን እይ አላቸው።
29፤ አንዱን በቤቴል፥ ሁለተኛውንም በዳን አኖረ።
30፤ ለአንዱ ጥጃ ይሰግድ ዘንድ ሕዝቡ እስከ ዳን ድረስ ይሄድ ነበርና ይህ ኃጢአት ሆነ።
31፤ በኮረብቶቹም ላይ መስገጃዎች ሠራ፥ ከሌዊ ልጆች ካይደሉ ከሕዝብ ሁሉ ካህናትን አደረገ።
32፤ በስምንተኛው ወር በአሥራ አምስተኛውም ቀን በይሁዳ እንደሚደረግ በዓል ያለ በዓል አደረገ፥ በመሠዊያውም ላይ ሠዋ፤ ለሠራቸውም ጥጆች ይሠዋ ዘንድ እንዲሁ በቤቴል አደረገ፤ ለኮረብታ መስገጃዎችም የመረጣቸውን ካህናት በቤቴል አኖራቸው።
33፤ በስምንተኛውም ወር በአሥራ አምስተኛው ቀን በልቡ ባሰበው ቀን በቤቴል በሠራው መሠዊያ ላይ ሠዋ፤ ለእስራኤልም ልጆች በዓል አደረገላቸው፤ በመሠዊያውም ሠዋ፥ ዕጣንም ዐጠነ። a
ምዕራፍ 13

1፤ እነሆም፥ አንድ የእግዚአብሔር ሰው በእግዚአብሔር ቃል ከይሁዳ ወደ ቤቴል መጣ፤ ኢዮርብዓምም ዕጣን እያጠነ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ነበር።
2፤ በመሠዊያውም ላይ። መሠዊያ ሆይ፥ መሠዊያ ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ስሙ ኢዮስያስ የሚባል ልጅ ለዳዊት ቤት ይወለዳል፤ ዕጣንም የሚያጥኑብህን የኮረብታ መስገጃዎቹን ካህናት ይሠዋብሃል፥ የሰዎቹንም አጥንት ያቃጥልብሃል ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ጮኸ።
3፤ በዚያም ቀን። እግዚአብሔር የተናገረው ምልክት ይህ ነው፤ እነሆ፥ መሠዊያው ይሰነጠቃል፥ በላዩም ያለው አመድ ይፈስሳል ብሎ ምልክት ሰጠ።
4፤ ንጉሡም የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል ባለው መሠዊያ ላይ የጮኸውን ነገር በሰማ ጊዜ፥ ኢዮርብዓም እጁን ከመሠዊያው አንሥቶ። ያዙት አለ። በእርሱም ላይ የዘረጋት እጅ ደረቀች፥ ወደ እርሱም ይመልሳት ዘንድ አልተቻለውም።
5፤ የእግዚአብሔርም ሰው በእግዚአብሔር ቃል እንደ ሰጠው ምልክት መሠዊያው ተሰነጠቀ፥ አመዱም ከመሠዊያው ፈሰሰ።
6፤ ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው። አሁን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ፊት ለምን፥ እጄም ወደ እኔ ትመለስ ዘንድ ስለ እኔ ጸልይ አለው። የእግዚአብሔርም ሰው እግዚአብሔርን ለመነ፥ የንጉሡም እጅ ወደ እርሱ ተመለሰች፥ እንደ ቀድሞም ሆነች።
7፤ ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው። ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ና እንጀራም ብላ፥ በረከትም እሰጥሃለሁ አለው።
8፤ የእግዚአብሔርም ሰው ንጉሡን። የቤትህን እኩሌታ እንኳ ብትሰጠኝ ከአንተ ጋር አልገባም፥ በዚህም ስፍራ እንጀራ አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም፤
9፤ እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ፥ በመጣህበትም መንገድ አትመለስ በሚል በእግዚአብሔር ቃል ታዝዤአለሁና አለው።
10፤ በሌላም መንገድ ሄደ፥ ወደ ቤቴልም በመጣበት መንገድ አልተመለሰም።
11፤ በቤቴልም አንድ ሽማግሌ ነቢይ ይቀመጥ ነበር፤ ልጆቹም ወደ እርሱ መጥተው በዚያ ቀን የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል ያደረገውን ሥራ ሁሉ ነገሩት ደግሞም ለንጉሡ የተናገረውን ቃል ሁሉ ለአባታቸው ነገሩት።
12፤ አባታቸውም። በማናቸው መንገድ ሄደ? አላቸው። ልጆቹም ከይሁዳ የመጣው የእግዚአብሔር ሰው የሄደበትን መንገድ አመለከቱት።
13፤ ልጆቹንም። አህያውን ጫኑልኝ አላቸው፤ አህያውንም በጫኑለት ጊዜ ተቀመጠበት።
14፤ ከእግዚአብሔርም ሰው በኋላ ሄደ፤ በአድባርም ዛፍ በታች ተቀምጦ አገኘውና። ከይሁዳ የመጣህ የእግዚአብሔር ሰው አንተ ነህን? አለው። እርሱም። እኔ ነኝ አለ።
15፤ እርሱም። ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ና፥ እንጀራም ብላ አለው።
16፤ እርሱም። ከአንተ ጋር እመለስና እገባ ዘንድ አይቻለኝም፤ በዚህም ስፍራ ከአንተ ጋር እንጀራ አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም፤
17፤ በዚያ እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ፥ በመጣህበትም መንገድ አትመለስ በሚል በእግዚአብሔር ቃል ተብሎልኛልና አለ።
18፤ እርሱም። እኔ ደግሞ እንደ አንተ ነቢይ ነኝ፤ መልአክም። እንጀራ ይበላ ዘንድ ውኃም ይጠጣ ዘንድ ከአንተ ጋር ወደ ቤትህ መልሰው ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ተናገረኝ አለው። ዋሽቶም ተናገረው።
19፤ ከእርሱም ጋር ተመለሰ፥ በቤቱም እንጀራ በላ፥ ውኃም ጠጣ።
20፤ በማዕድም ተቀምጠው ሳሉ የእግዚአብሔር ቃል ወደ መለሰው ነቢይ መጣ፤
21፤ ከይሁዳም ወደ መጣው ወደ እግዚአብሔር ሰው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእግዚአብሔር አፍ ላይ ዐምፀሃልና፥ አምላክህም እግዚአብሔር ያዘዘህን ትእዛዝ አልጠበቅህምና፥
22፤ ተመልሰህም። እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ ባለህ ስፍራ እንጀራ በልተሃልና፥ ውኃም ጠጥተሃልና ሬሳህ ወደ አባቶችህ መቃብር አይደርስም ብሎ ጮኸ።
23፤ እንጀራም ከበላ፥ ውኃም ከጠጣ በኋላ አህያውን ጫነለት።
24፤ ተመልሶም በሄደ ጊዜ በመንገዱ ላይ አንበሳ አግኝቶ ገደለው፤ ሬሳውም በመንገድ ላይ ተጋድሞ ነበር፥ አህያውም በእርሱ አጠገብ ቆሞ ነበር፤ አንበሳውም ደግሞ በሬሳው አጠገብ ቆሞ ነበር።
25፤ እነሆም፥ መንገድ አላፊ ሰዎች ሬሳው በመንገዱ ወድቆ አንበሳውም በሬሳው አጠገብ ቆሞ አዩ መጥተውም ሽማግሌው ነቢይ ተቀምጦባት በነበረው ከተማ አወሩ።
26፤ ያም ከመንገድ የመለሰው ነቢይ ያን በሰማ ጊዜ። በእግዚአብሔር አፍ ላይ ያመፀ ያ የእግዚአብሔር ሰው ነው፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ቃል፥ እግዚአብሔር ለአንበሳ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ ሰብሮም ገድሎታል አለ።
27፤ ልጆቹንም። አህያ ጫኑልኝ አላቸው፤ እነርሱም ጫኑለት።
28፤ ሄደም፥ ሬሳውም በመንገድ ወድቆ፥ በሬሳውም አጠገብ አህያውና አንበሳው ቆመው፥ አንበሳው ሬሳውን ሳይበላው፥ አህያውንም ሳይሰብረው አገኘ።
29፤ ነቢዩም የእግዚአብሔርን ሰው ሬሳ አነሣ፥ በአህያውም ላይ ጭኖ መለሰው፤ ያለቅስለትና ይቀብረው ዘንድ ወደ ገዛ ከተማው ይዞት መጣ።
30፤ ሬሳውንም በገዛ መቃብሩ አኖረው፤ ዋይ ዋይ ወንድሜ ሆይ እያሉ አለቀሱለት።
31፤ ከቀበረውም በኋላ ልጆቹን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። በሞትሁ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው በተቀበረበት መቃብር ቅበሩኝ፤ አጥንቶቼንም በአጥንቶቹ አጠገብ አኑሩ፤
32፤ በቤቴል ባለው መሠዊያ ላይ፥ በሰማርያም ከተሞች ውስጥ ባሉ በኮረብታዎቹ መስገጃዎች ላይ በእግዚአብሔር ቃል የጮኸው ነገር በእውነት ይደርሳልና።
33፤ ከዚህም በኋላ ኢዮርብዓም ከክፉ መንገድ አልተመለሰም፥ ነገር ግን ለኮረብታዎቹ መስገጃዎች አብልጦ ከሕዝብ ሁሉ ካህናትን አደረገ፤ የሚወድደውንም ሁሉ ይቀድስ ነበር፥ እርሱም ለኮርብታዎቹ መስገጃዎች ካህን ይሆን ነበር።
34፤ እስኪፈርስም ከምድርም እስኪጠፋ ድረስ ይህ ነገር ለኢዮርብዓም ቤት ኃጢአት ሆነ።
ምዕራፍ 14

1፤ በዚያም ወራት የኢዮርብዓም ልጅ አብያ ታመመ።
2፤ ኢዮርብዓምም ሚስቱን። ተነሺ፥ የኢዮርብዓምም ሚስት እንደ ሆንሽ እንዳትታወቂ ልብስሽን ለውጪና ወደ ሴሎ ሂጂ፤ እነሆ፥ በዚህ ሕዝብ ላይ እንድነግሥ የነገረኝ ነቢዩ አኪያ በዚያ አለ።
3፤ በእጅሽም አሥር እንጀራና እንጎቻዎች አንድም ምንቸት ማር ይዘሽ ወደ እርሱ ሂጂ፤ በልጁም የሚሆነውን ይነግርሻል አላት።
4፤ የኢዮርብዓምም ሚስት እንዲሁ አደረገች፥ ተነሥታም ወደ ሴሎ ሄደች፤ ወደ አኪያም ቤት መጣች። አኪያም ስለ መሸምገሉ ዓይኖቹ ፈዝዘው ነበርና፤ ማየት አልቻለም።
5፤ እግዚአብሔርም አኪያን። እነሆ፥ ስለ ታመመው ልጅዋ ትጠይቅህ ዘንድ የኢዮርብዓም ሚስት ትመጣለች፤ ሌላ ሴትም መስላ ተሰውራለችና በገባች ጊዜ እንዲህና እንዲህ በላት አለው።
6፤ እርስዋም በደጅ ስትገባ አኪያ የእግርዋን ኮቴ ሰማ፥ እንዲህም አለ። የኢዮርብዓም ሚስት ሆይ፥ ግቢ፤ ስለ ምንስ ሌላ ሴት መሰልሽ? እኔም ብርቱ ወሬ ይዤ ተልኬልሻለሁ።
7፤ ሂጂ፥ ለኢዮርብዓምም እንዲህ በዪው። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከሕዝብ መካከል ለይቼ ከፍ አድርጌህ ነበር፥ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ አለቃ አድርጌህ ነበር፥
8፤ ከዳዊትም ቤት መንግሥቱን ቀድጄ ሰጥቼህ ነበር፤ ነገር ግን በፍጹም ልቡ እንደ ተከተለኝ፥ በፊቴም ቅን ነገር ብቻ እንዳደረገ፥ ትእዛዜንም እንደ ጠበቀ እንደ ባሪያዬ እንደ ዳዊት አልሆንህም።
9፤ ከአንተም አስቀድመው ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ክፉ ሠራህ፤ ታስቈጣኝም ዘንድ ሄደህ ሌሎችን አማልክትና ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎች አደረግህ፥ ወደ ኋላህም ጣልኸኝ።
10፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ በኢዮርብዓም ቤት ላይ መከራ አመጣለሁ፥ ከኢዮርብአምም በእስራኤል ዘንድ የታሰረውንና የተለቀቀውን ወንድ ሁሉ እቈርጣለሁ፤ ሰውም ፋንድያን እስኪጠፋ ድረስ እንደሚጠርግ እኔ የኢዮርብዓምን ቤት ፈጽሜ እጠርጋለሁ።
11፤ ከኢዮርብዓምም ወገን በከተማይቱ ውስጥ የሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳውም የሞተውን የሰማይ ወፎች ይበሉታል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና።
12፤ እንግዲህ ተነሥተሽ ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ እግርሽም ወደ ከተማ በገባ ጊዜ ልጁ ይሞታል።
13፤ እስራኤልም ሁሉ ያለቅሱለታል፥ ይቀብሩትማል፤ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ዘንድ በኢዮርብዓም ቤት በዚህ ልጅ መልካም ነገር ተገኝቶበታልና ከኢዮርብዓም እርሱ ብቻ ይቀበራል።
14፤ እግዚአብሔርም ደግሞ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ያስነሣል፤ እርሱም በዚያ ዘመን የኢዮርብዓምን ቤት ያጠፋል።
15፤ በዚያ ጊዜም ሸምበቆ በውኃ ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ እግዚአብሔር እንዲሁ እስራኤልን ይመታል፤ እግዚአብሔርንም ያስቈጡ ዘንድ የማምለኪያ ዐፀድ ተክለዋልና ለአባቶቻቸው ከሰጣቸው ከዚች ከመልካሚቱ ምድር እስራኤልን ይነቅላል፥ በወንዙም ማዶ ይበትናቸዋል።
16፤ ስለ በደለውና እስራኤልንም ስላሳተበት ስለ ኢዮርብዓም ኃጢአት እስራኤልን ይጥላል።
17፤ የኢዮርብዓምም ሚስት ተነሥታ ሄደች፥ ወደ ቴርሳ መጣች፤ ወደ ቤቱም መድረክ በገባች ጊዜ ልጁ ሞተ።
18፤ በባሪያውም በነቢዩ በአኪያ እንደ ተነገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል እስራኤል ሁሉ ቀበሩት አለቀሱለትም።
19፤ የቀረውም የኢዮርብዓም ነገር፥ እንዴት እንደ ተዋጋ፥ እንዴትም እንደ ነገሠ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል።
20፤ ኢዮርብዓምም የነገሠበት ዘመን ሀያ ሁለት ዓመት ነበረ፤ ከአባቶቹም ጋር አንቀላፋ፥ ልጁም ናዳብ በፋንታው ነገሠ።
21፤ የሰሎሞንም ልጅ ሮብዓም በይሁዳ ነገሠ፤ ሮብዓምም ንጉሥ በሆነ ጊዜ የአርባ አንድ ዓመት ጉልማሳ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ስሙን ያኖርባት ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ በመረጣት ከተማ በኢየሩሳሌም አሥራ ሰባት ዓመት ነገሠ፤ የእናቱም ስም ናዕማ ነበረ፤ እርስዋም አሞናዊት ነበረች።
22፤ ይሁዳም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሠራ፤ አባቶቻቸውም ከሠሩት ሁሉ ይልቅ አብዝተው በሠሩት ኃጢአት አስቈጡት።
23፤ እነርሱም ደግሞ ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ ላይ፥ ቅጠሉ ከለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች መስገጃዎችንና ሐውልቶችን የማምለኪያ ዐፀዶችንም ለራሳቸው ሠሩ።
24፤ በምድርም ውስጥ ሰዶማውያን ነበሩ፤ ከእስራኤልም ልጆች ፊት እግዚአብሔር ያሳደዳቸውን የአሕዛብን ርኵሰት ሁሉ ያደርጉ ነበር።
25፤ ሮብዓምም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ መጣ።
26፤ የእግዚአብሔርም ቤት መዛግብትንና የንጉሥ ቤት መዛግብትን ወሰደ፤ ሁሉንም ወሰደ፤ ሰሎሞንም የሠራውን የወርቁን ጋሻ ሁሉ ወሰደ።
27፤ ንጉሡም ሮብዓም በፋንታው የናስ ጋሾችን ሠራ፥ የንጉሥንም ቤት ደጅ በሚጠብቁ በዘበኞች አለቆች እጅ አኖራቸው።
28፤ ንጉሡም ዘወትር ወደ እግዚአብሔር ቤት ሲገባ ዘበኞች ይሸከሙአቸው ነበር፤ መልሰውም በዘበኞች ቤት ውስጥ ያኖሩአቸው ነበር።
29፤ የቀረውም የሮብዓም ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
30፤ በዘመኑም ሁሉ በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል ሰልፍ ነበረ።
31፤ ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ። ልጁም አብያም በፋንታው ነገሠ። a
ምዕራፍ 15

1፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በነገሠ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት አብያም በይሁዳ ላይ ንጉሥ ሆነ።
2፤ በኢየሩሳሌምም ሦስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም መዓካ የተባለች የአቤሴሎም ልጅ ነበረች።
3፤ ከእርሱ አስቀድሞ ባደረገው በአባቱ ኃጢአት ሁሉ ሄደ፤ ልቡም እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ልብ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም አልነበረም።
4፤ ነገር ግን ልጁን ከእርሱ በኋላ ያስነሣ ዘንድ፥ ኢየሩሳሌምንም ያጸና ዘንድ አምላኩ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት በኢየሩሳሌም መብራት ሰጠው፤
5፤ ዳዊት በዘመኑ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አድርጎ ነበርና፥ ካዘዘውም ነገር ሁሉ ፈቀቅ አላለም ነበርና።
6፤ በኢዮርብዓምና በሮብዓም ልጅ በአብያም መካከል በዘመኑ ሁሉ ጠብ ነበረ።
7፤ የቀረውም የአብያም ነገር፥ ያደርገውም ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? በአብያምና በኢዮርብዓምም መካከል ሰልፍ ነበረ።
8፤ አብያምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት። ልጁም አሳ በፋንታው ነገሠ።
9፤ በእስራኤል ንጉሥ በኢዮርብዓም በሀያኛውም ዓመት አሳ በይሁዳ ላይ ነገሠ።
10፤ በኢየሩሳሌምም አርባ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም መዓካ የተባለች የአቤሴሎም ልጅ ነበረች።
11፤ አሳ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ።
12፤ ከአገሩም ሰዶማውያንን አስወገደ፥ አባቶቹም ያደረጉትን ጣዖታትን ሁሉ አራቀ።
13፤ በማምለኪያ ዐፀድ ጣዖት ስለሠራች እናቱን መዓካን እቴጌ እንዳትሆን ሻራት፤ ጣዖትዋንም ሰበረው፥ በቄድሮንም ፈፋ አጠገብ አቃጠለው።
14፤ ነገር ግን በኮረብቶች ላይ ያሉትን መስገጃዎች አላራቀም፤ የአሳ ልብ ግን በዘመኑ ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም ነበረ።
15፤ አባቱ የቀደሰውንና እርሱም የቀደሰውን ወርቅና ብር ዕቃውንም ወደ እግዚአብሔር ቤት አገባው።
16፤ በአሳና በእስራኤል ንጉሥ በባኦስ መካከል በዘመናቸው ሁሉ ሰልፍ ነበረ።
17፤ የእስራኤልም ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ወጣ፤ ከይሁዳ ንጉሥ ከአሳ ዘንድ ማንም እንዳይወጣ ወደ እርሱም ማንም እንዳይገባ አድርጎ ራማን ሠራ።
18፤ አሳም በእግዚአብሔር ቤትና በንጉሥ ቤት መዛግብት የቀረውን ብርና ወርቅ ሁሉ ወስዶ በባሪያዎቹ እጅ ሰጣቸው፤ ንጉሡም አሳ በደማስቆ ለተቀመጠው ለአዚን ልጅ ለጠብሪሞን ልጅ ለሶርያ ንጉሥ ለወልደ አዴር።
19፤ በእኔና በአንተ መካከል በአባቴና በአባትህም መካከል ቃል ኪዳን ጸንቶአል፤ እነሆ፥ ብርና ወርቅ ገጸ በረከት ሰድጄልሃለሁ፤ እርሱ ከእኔ ዘንድ እንዲርቅ ሄደህ ከእስራኤል ንጉሥ ከባኦስ ጋር ያለህን ቃል ኪዳን አፍርስ ብሎ ሰደደ።
20፤ ወልደ አዴርም ለንጉሡ ለአሳ እሺ አለው፤ የሠራዊቱንም አለቆች በእስራኤል ከተሞች ላይ ሰድዶ ዒዮንንና ዳንን፥ አቤልቤት መዓካንና ኪኔሬትን ሁሉ የንፍታሌምንም አገር ሁሉ መታ።
21፤ ባኦስም ያን በሰማ ጊዜ ራማን መሥራት ትቶ በቴርሳ ተቀመጠ።
22፤ ንጉሡም አሳ በይሁዳ ሁሉ ላይ አዋጅ ነገረ፤ ማንም ነጻ አልነበረም፤ ባኦስም የሠራበትን የራማን ድንጋይና እንጨት ወሰዱ፥ ንጉሡም አሳ የብንያምን ጌባንና ምጽጳን ሠራበት።
23፤ የቀረውም የአሳ ነገር ሁሉ፥ ጭከናውም ሁሉ፥ ያደረገውም ሁሉ፥ የሠራቸውም ከተሞች፥ በይሁዳ ነገሥት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ነገር ግን በሸመገለ ጊዜ እግሮቹ ታመሙ።
24፤ አሳም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በአባቱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ። ልጁም ኢዮሣፍጥ በፋንታው ነገሠ።
25፤ በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሁለተኛው ዓመት የኢዮርብዓም ልጅ ናዳብ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በእስራኤልም ላይ ሁለት ዓመት ነገሠ።
26፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፥ በአባቱም መንገድ እስራኤልንም ባሳተበት ኃጢአት ሄደ።
27፤ ከይሳኮርም ቤት የሆነ የአኪያ ልጅ ባኦስ ተማማለበት፤ ናዳብና እስራኤልም ሁሉ ገባቶንን ከብበው ነበርና ባኦስ በፍልስጥኤም አገር ባለው በገባቶን ገደለው።
28፤ በይሁዳ ንጉሥ በአሳ በሦስተኛው ዓመት ባኦስ ናዳብን ገደለው፥ በፋንታውም ነገሠ።
29
30፤ ንጉሥም በሆነ ጊዜ የኢዮርብዓምን ቤት ሁሉ መታ፤ ኢዮርብዓምም ስለ ሠራው ኃጢአት፥ እስራኤልንም ስላሳተበት፥ የእስራኤልንም አምላክ እግዚአብሔርን ስላስቈጣበት ማስቈጫ፥ በባሪያው በሴሎናዊው በአኪያ እጅ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል፥ እስኪያጠፋው ድረስ ከኢዮርብዓም አንድ ትንፋሽ ያለው አላስቀረም።
31፤ የቀረውም የናዳብ ነገርና ያደረገው ሁሉ፥ (
32፤) በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
33፤ በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሦስተኛው ዓመት የአኪያ ልጅ ባኦስ በእስራኤል ሁሉ ላይ በቴርሳ ንጉሥ ሆኖ ሀያ አራት ዓመት ነገሠ።
34፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፥ በኢዮርብዓምም መንገድ እስራኤልንም ባሳተበት ኃጢአት ሄደ።
ምዕራፍ 16

1፤ የእግዚአብሔርም ቃል በባኦስ ላይ እንዲህ ብሎ ወደ አናኒ ልጅ ወደ ኢዩ መጣ።
2፤ እኔ ከመሬት አስነሥቼ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ አድርጌሃለሁ፤ አንተ ግን በኢዮርብዓም መንገድ ሄደሃል፥ በኃጢአታቸውም ያስቈጡኝ ዘንድ ሕዝቤን እስራኤልን አስተሃቸዋል።
3፤ ስለዚህም፥ እነሆ፥ ባኦስንና ቤቱን ፈጽሜ እጠርጋለሁ፤ ቤትህንም እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት አደርጋለሁ።
4፤ ከባኦስም ወገን በከተማይቱ ውስጥ የሚሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳውም የሚሞተውን የሰማይ ወፎች ይበሉታል።
5፤ የቀረውም የባኦስ ነገር፥ ሥራውና ጭከናውም፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
6፤ ባኦስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በቴርሳም ተቀበረ፤ ልጁም ኤላ በፋንታው ነገሠ።
7፤ በእጁም ሥራ ያስቈጣው ዘንድ፥ እንደ ኢዮርብዓም ቤት በእግዚአብሔር ፊት ስላደረገው ክፋት ሁሉ እርሱንም ስለ ገደለው፥ የእግዚአብሔር ቃል በባኦስና በቤቱ ላይ ወደ አናኒ ልጅ ወደ ነቢዩ ወደ ኢዩ መጣ።
8፤ በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሀያ ስድስተኛው ዓመት የባኦስ ልጅ ኤላ በእስራኤል ላይ በቴርሳ ሁለት ዓመት ነገሠ።
9፤ የእኩሌቶቹም ሰረገሎች አለቃ ዘምሪ ተማማለበት፤ ኤላም በቴርሳ ነበረ፥ በቴርሳም በነበረው በቤት አሽከሮች አለቃ በኦሳ ቤት ይሰክር ነበር።
10፤ በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሀያ ሰባተኛው ዓመት ዘምሪ ገብቶ መታው ገደለውም፥ በፋንታውም ነገሠ።
11፤ ንጉሥም በሆነ ጊዜ፥ በዙፋኑም በተቀመጠ ጊዜ፥ የባኦስን ቤት ሁሉ መታ፤ ከዘመዶችና ከወዳጆች ሁሉ አንድ ወንድ እንኳ አልቀረም።
12
13፤ ባኦስና ልጁ ኤላ ስለ ሠሩት ኃጢአት ሁሉ፥ በምናምንቴም ሥራቸው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ያስቈጡት ዘንድ እስራኤልን ስለ አሳቱበት ኃጢአት፥ በነቢዩ በኢዩ እጅ በባኦስ ላይ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ዘምሪ የባኦስን ቤት ሁሉ እንዲሁ አጠፋ።
14፤ የቀረውም የኤላ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
15፤ በይሁዳ ንጉሥ በአሳ በሀያ ሰባተኛው ዓመት ዘምሪ በቴርሳ ሰባት ቀን ነገሠ። ሕዝቡም በፍልስጥኤም አገር የነበረው ገባቶንን ከብበው ነበር።
16፤ ከተማይቱንም ከብበው የነበሩ ሕዝብ ዘምሪ እንደ ዐመፀ፥ ንጉሡንም እንደ ገደለ ሰሙ፤ እስራኤልም ሁሉ በዚያ ቀን በሰፈሩ ውስጥ የሠራዊቱን አለቃ ዘንበሪን አነገሡ።
17፤ ዘንበሪም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከገባቶን ወጥተው ቴርሳን ከበቡ።
18፤ ዘምሪም ከተማይቱ እንደ ተያዘች ባየ ጊዜ ወደ ንጉሡ ቤት ግንብ ውስጥ ገባ፥ የንጉሡንም ቤት በራሱ ላይ በእሳት አቃጠለ፤
19፤ ስላደረገውም ኃጢአት፥ እስራኤልንም ስላሳተበት ኃጢአት፥ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አድርጎአልና፥ በኢዮርብዓምም መንገድ ሄዶአልና ሞተ።
20፤ የቀረውም የዘምሪ ነገር፥ ያደረገውም ዐመፅ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
21፤ በዚያም ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ በሁለት ተከፈለ፤ የሕዝቡም እኩሌታ የጎናትን ልጅ ታምኒን ያነግሡት ዘንድ ተከተለው፤ እኩሌታውም ዘንበሪን ተከተለ።
22፤ ዘንበሪንም የተከተለ ሕዝብ የጎናትን ልጅ ታምኒን በተከተለ ሕዝብ ላይ በረታ፤ ታምኒም ሞተ፥ ዘንበሪም ነገሠ።
23፤ በይሁዳ ንጉሥ በአሳ በሠላሳ አንደኛው ዓመት ዘንበሪ በእስራኤል ላይ አሥራ ሁለት ዓመት ነገሠ። በቴርሳም ስድስት ዓመት ነገሠ።
24፤ ከሳምርም በሁለት መክሊት ብር የሰማርያን ተራራ ገዛ፤ በተራራውም ላይ ሠራ፥ የሠራውንም ከተማ በተራራው ባለቤት በሳምር ስም ሰማርያ ብሎ ጠራው።
25፤ ዘንበሪም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፥ ከእርሱም አስቀድሞ ከነበሩት ይልቅ እጅግ ከፋ።
26፤ በናባጥም ልጅ በኢዮርብዓም መንገድ ሁሉ በምናምንቴም ነገራቸው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ያስቈጡት ዘንድ እስራኤልን ባሳተበት ኃጢአት ሄደ።
27፤ የቀረውም ዘንበሪ ያደረገው ነገር፥ የሠራውም ጭከና፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
28፤ ዘንበሪም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በሰማርያም ተቀበረ፤ ልጁም አክዓብ በፋንታው ነገሠ።
29፤ በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት የዘንበሪ ልጅ አክዓብ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ የዘንበሪም ልጅ አክዓብ በእስራኤል ላይ በሰማሪያ ሀያ ሁለት ዓመት ነገሠ።
30፤ የዘንበሪም ልጅ አክዓብ ከእርሱ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።
31፤ በናባጥም ልጅ በኢዮርብዓም ኃጢአት መሄድ ታናሽ ነገር መሰለው፥ የሲዶናውያንንም ንጉሥ የኤትበኣልን ልጅ ኤልዛቤልን አገባ፥ ሄዶም በኣልን አመለከ ሰገደለትም።
32፤ በሰማርያም በሠራው በበኣል ቤት ውስጥ ለበኣል መሠዊያ አቆመ።
33፤ አክዓብም የማምለኪያ ዐፀድ ተከለ፤ አክዓብም ከእርሱ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የሚያስቈጣውን ነገር አበዛ።
34፤ በእርሱም ዘመን የቤቴል ሰው አኪኤል ኢያሪኮን ሠራ፤ በነዌም ልጅ በኢያሱ እጅ እንደ ተነገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል፥ በበኵር ልጅ በአቢሮን መሠረትዋን አደረገ፥ በታናሹ ልጁም በሠጉብ በሮችዋን አቆመ። a
ምዕራፍ 17

1፤ በገለዓድ ቴስቢ የነበረው ቴስብያዊው ኤልያስ አክዓብን። በፊቱ የቆምሁት የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! ከአፌ ቃል በቀር በእነዚህ ዓመታት ጠልና ዝናብ አይሆንም አለው።
2፤ የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ለእርሱ መጣለት።
3፤ ከዚህ ተነሥተህ ወደ ምሥራቅ ሂድ፥ በዮርዳኖስም ትይዩ ባለው በኮራት ፈፋ ውስጥ ተሸሸግ።
4፤ ከወንዙም ትጠጣለህ፥ ቍራዎችም በዚያ ይመግቡህ ዘንድ አዝዣለሁ።
5፤ ሄደም እንደ እግዚአብሔር ቃልም አደረገ። ሄዶም በዮርዳኖስ ትይዩ ባለው በኮራት ፈፋ ውስጥ ተቀመጠ።
6፤ ቍራዎቹም በየጥዋትና በየማታው እንጀራና ሥጋ ያመጡለት ነበር፤ ከወንዙም ይጠጣ ነበር።
7፤ ከብዙ ቀንም በኋላ በምድር ላይ ዝናብ አልነበረምና ወንዙ ደረቀ።
8፤ ተነሥተህም በሲዶና አጠገብ ወዳለችው ወደ ሰራፕታ ሂድ፥ በዚያም ተቀመጥ፤
9፤ እነሆም፥ ትመግብህ ዘንድ አንዲት ባልቴት አዝዣለሁ የሚል የእግዚአብሔር ቃል መጣለት።
10፤ ተነሥቶም ወደ ሰራፕታ ሄደ፤ ወደ ከተማይቱም በር በደረሰ ጊዜ አንዲት ባልቴት በዚያ እንጨት ትለቅም ነበር፤ እርሱም ጠርቶ። የምጠጣው ጥቂት ውኃ በጽዋ ታመጭልኝ ዘንድ እለምንሻለሁ አላት።
11፤ ውኃም ልታመጣለት በሄደች ጊዜ ወደ እርስዋ ጠርቶ፥ ቁራሽ እንጀራ በእጅሽ ይዘሽ ትመጭ ዘንድ እለምንሻለሁ አላት።
12፤ እርስዋም። አምላክህ ሕያው እግዚአብሔርን! በማድጋ ካለው ከእፍኝ ዱቄት፥ በማሰሮም ካለው ከጥቂት ዘይት በቀር እንጀራ የለኝም፤ እነሆም፥ ገብቼ ለእኔና ለልጄ እጋግረው ዘንድ በልተነውም እንሞት ዘንድ ጥቂት እንጨት እሰበስባለሁ አለች።
13፤ ኤልያስም አላት። አትፍሪ፤ ይልቅስ ሄደሽ እንዳልሺው አድርጊ፤ አስቀድመሽ ግን ከዱቄቱ ለእኔ ታናሽ እንጎቻ አድርገሽ አምጭልኝ፥ ከዚያም በኋላ ለአንቺና ለልጅሽ አድርጊ፤
14፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። በምድር ላይ እግዚአብሔር ዝናብ እስከሚሰጥበት ቀን ድረስ፥ ዱቄቱ ከማድጋ አይጨረስም፥ ዘይቱም ከማሰሮው አይጎድልም።
15፤ እርስዋም ሄዳ እንደ ኤልያሳ ቃል አደረገች፤ እርስዋና እርሱ ቤትዋም ብዙ ቀን በሉ።
16፤ በኤልያስም እጅ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ዱቄቱ ከማድጋው አልተጨረሰም፥ ዘይቱም ከማሰሮው አልጎደለም።
17፤ ከዚያም በኋላ የባለቤቲቱ ልጅ ታመመ፤ ትንፋሹም እስኪታጣ ድረስ ደዌው እጅግ ከባድ ነበረ።
18፤ እርስዋም ኤልያስን። የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ኃጢአቴንስ ታሳስብ ዘንድ፥ ልጄንስ ትገድል ዘንድ ወደ እኔ መጥተሃልን? አለችው።
19፤ ኤልያስም። ልጅሽን ስጪኝ አላት። ከብብትዋም ወስዶ ተቀምጦበት ወደ ነበረው ሰገነት አወጣው በአልጋውም ላይ አጋደመው።
20፤ ወደ እግዚአብሔርም። አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ ልጅዋን በመግደልህ ይህችን ትቀልበኝ የነበረቺቱን ባልቴት እንዲህ ደግሞ አስጨነቅኻትን? ብሎ ጮኸ።
21፤ በብላቴናውም ላይ ሦስት ጊዜ ተዘረጋበት፥ ወደ እግዚአብሔርም። አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ የዚህ ብላቴና ነፍስ ወደ እርሱ ትመለስ ዘንድ እለምንሃለሁ ብሎ ጮኸ።
22፤ እግዚአብሔርም የኤልያስን ቃል ሰማ፤ የብላቴናው ነፍስ ወደ እርሱ ተመለሰች፥ እርሱም ዳነ።
23፤ ኤልያስም ብላቴናውን ይዞ ከሰገነቱ ወደ ቤት አወረደው፥ ኤልያስም። እነሆ፥ ልጅሽ በሕይወት ይኖራል ብሎ ለእናቱ ሰጣት።
24፤ ሴቲቱም ኤልያስን። የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆንህ፥ የእግዚአብሔርም ቃል በአፍህ እውነት እንደ ሆነ አሁን አወቅሁ አለችው።
ምዕራፍ 18

1፤ ከብዙ ቀንም በኋላ በሦስተኛው ዓመት። ሂድ፥ ለአክዓብ ተገለጥ፥ በምድር ላይም ዝናብ እሰጣለሁ የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤልያስ መጣ።
2፤ ኤልያስም ለአክዓብ ይገለጥ ዘንድ ሄደ፤ በሰማርያም ራብ ጸንቶ ነበር።
3፤ አክዓብም የቤቱን አዛዥ አብድዩን ጠራ፤ አብድዩ እግዚአብሔርን እጅግ ይፈራ ነበር።
4፤ ኤልዛቤልም የእግዚአብሔርን ነቢያት ባስገደለች ጊዜ እርሱ መቶውን ነቢያት ወስዶ አምሳ አምሳውን በዋሻ ውስጥ ሸሽጎ እንጀራና ውኃ ይመግባቸው ነበር።
5፤ አክዓብም አብድዩን። በአገሩ መካከል ወደ ውኃው ምንጭ ሁሉና ወደ ወንዝ ሁሉ ሂድ፤ እንስሶችም ሁሉ እንዳይጠፉ ፈረሶችንና በቅሎችን የምናድንበት ሣር ምናልባት እናገኛለን አለው።
6፤ ሁለቱም የሚመለሱበትን አገር ተካፈሉ፤ አክዓብም ለብቻው በአንድ መንገድ አብድዩም ለብቻው በሌላ መንገድ ሄዱ።
7፤ አብድዩም በመንገድ ሲሄድ፥ እነሆ፥ ኤልያስ ተገናኘው፤ አብድዩም አወቀው፥ በግምባሩም ተደፍቶ። ጌታዬ ሆይ፥ ኤልያስ አንተ ነህን? አለ።
8፤ ኤልያስም። እኔ ነኝ ሄደህ ለጌታህ። ኤልያስ ተገኝቶአል በል አለው።
9፤ አብድዩም አለ። እኔን ባሪያህን እንዲገድል በአክዓብ እጅ አሳልፈህ ትሰጠኝ ዘንድ ምን ኃጢአት አድርጌአለሁ?
10፤ አምላክህ ሕያው እግዚአብሔርን! ጌታዬ ይፈልግህ ዘንድ ያልላከበት ሕዝብ ወይም መንግሥት የለም፤ ሁሉም። በዚህ የለም ባሉ ጊዜ አንተን እንዳላገኙ መንግሥቱንና ሕዝቡን አምሎአቸው ነበር።
11፤ አሁንም፥ እነሆ። ሂድ፥ ኤልያስ ተገኘ ብለህ ለጌታህ ንገር ትለኛለህ።
12፤ እኔም ከአንተ ጥቂት ራቅ ስል የእግዚአብሔር መንፈስ አንሥቶ ወደማላውቀው ስፍራ ይወስድሃል፤ እኔም ገብቼ ለአክዓብ ስናገር፥ ባያገኝህ ይገድለኛል፤ እኔም ባሪያህ ከትንሽነቴ ጀምሬ እግዚአብሔርን እፈራ ነበር።
13፤ ኤልዛቤል የእግዚአብሔርን ነቢያት ባስገደለች ጊዜ፥ መቶውን የእግዚአብሔር ነቢያት ወስጄ፥ አምሳ አምሳውንም በዋሻ ውስጥ ሸሽጌ፥ እንጀራና ውኃ የመገብኋቸው፥ ይህ ያደርግሁት ነገር በውኑ ለጌታዬ አልታወቀህምን?
14፤ አሁንም። ሄደህ ኤልያስ ተገኘ ብለህ ለጌታህ ንገር ትላለህ፤ እርሱም ይገድለኛል።
15፤ ኤልያስም። በፊቱ የቆምሁት የሠራዊት ጌታ ሕያው እግዚአብሔርን! እኔ ዛሬ ለእርሱ እገለጣለሁ አለ።
16፤ አብድዩም አክዓብን ሊገናኘው ሄደ፥ ነገረውም፤ አክዓብም ኤልያስን ሊገናኘው መጣ።
17፤ አክዓብም ኤልያስን ባየው ጊዜ። እስራኤልን የምትገለባብጥ አንተ ነህን? አለው።
18፤ ኤልያስም። እስራኤልን የምትገለባብጡ፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ በኣሊምን የተከተላችሁ፥ አንተና የአባትህ ቤት ናችሁ እንጂ እኔ አይደለሁም።
19፤ አሁንም ልከህ እስራኤልን ሁሉ፥ በኤልዛቤልም ማዕድ የሚበሉትን አራት መቶ አምሳ የበኣልን ነቢያት፥ አራት መቶም የማምለኪያ ዐፀድን ነቢያት ወደ እኔ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሰብስብ አለ።
20፤ አክዓብም ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ ልኮ ነቢያቱን ሁሉ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሰበሰበ።
21፤ ኤልያስም ወደ ሕዝቡ ሁሉ ቀርቦ። እስከ መቼ ድረስ በሁለት አሳብ ታነክሳላችሁ? እግዚአብሔር አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ፤ በኣል ግን አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ አለ። ሕዝቡም አንዲት ቃል አልመለሱለትም።
22፤ ኤልያስም ሕዝቡን አለ። ከእግዚአብሔር ነቢያት እኔ ብቻ ቀርቻለሁ፤ የበኣል ነቢያት ግን አራት መቶ አምሳ ሰዎች ናቸው።
23፤ ሁለት ወይፈኖች ይሰጡን፤ እነርሱም አንድ ወይፈን ይምረጡ፥ እየብልቱም ይቍረጡት፥ በእንጨትም ላይ ያኑሩት፥ በበታቹም እሳት አይጨምሩ፤ እኔም ሁለተኛውን ወይፈን አዘጋጃለሁ፥ በእንጨቱም ላይ አኖረዋለሁ፥ በበታቹም እሳት አልጨምርም።
24፤ እናንተም የአምላካችሁን ስም ጥሩ፥ እኔም የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁ፤ ሰምቶም በእሳት የሚመልስ አምላክ፥ እርሱ አምላክ ይሁን። ሕዝቡም ሁሉ። ይህ ነገር መልካም ነው ብለው መለሱ።
25፤ ኤልያስም የበኣልን ነቢያት። እናንተ ብዙዎች ናችሁና አስቀድማችሁ አንድ ወይፈን ምረጡና አዘጋጁ፤ የአምላካችሁንም ስም ጥሩ፥ በበታችሁም እሳት አትጨምሩ አላቸው።
26፤ ወይፈኑንም ወስደው አዘጋጁ፥ ከጠዋትም እስከ ቀትር ድረስ። በኣል ሆይ፥ ስማን እያሉ የበኣልን ስም ጠሩ። ድምፅም አልነበረም፥ የሚመልስም አልነበረም፤ በሠሩትም መሠዊያ ዙሪያ እያነከሱ ያሸበሽቡ ነበር።
27፤ በቀትርም ጊዜ ኤልያስ። አምላክ ነውና በታላቅ ቃል ጩኹ፤ ምናልባት አሳብ ይዞታል፥ ወይም ፈቀቅ ብሎአል፥ ወይም ወደ መንገድ ሄዶአል፥ ወይም ተኝቶ እንደ ሆነ መቀስቀስ ያስፈልገዋል እያለ አላገጠባቸው።
28፤ በታላቅም ቃል ይጮኹ፥ እንደ ልማዳቸውም ደማቸው እስኪፈስስ ድረስ ገላቸውን በካራና በቀጭኔ ይብዋጭሩ ነበር።
29፤ ቀትርም ካለፈ በኋላ መሥዋዕተ ሠርክ እስኪደርስ ትንቢት ይናገሩ ነበር፤ ድምፅም አልነበረም፥ የሚመልስና የሚያደምጥም አልነበረም።
30፤ ኤልያስም ሕዝቡን ሁሉ። ወደ እኔ ቅረቡ አላቸው። ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ። ፈርሶ የነበረውንም የእግዚአብሔርን መሠዊያ አበጀ።
31፤ ኤልያስም። ስምህ እስራኤል ይሆናል የሚል የእግዚአብሔር ቃል እንደ ደረሰለት እንደ ያዕቆብ ልጆች ነገድ ቍጥር አሥራ ሁለቱን ድንጋዮች ወሰደ።
32፤ ከድንጋዮችም ለእግዚአብሔር ስም መሠዊያ ሠራ፤ በመሠዊያውም ዙሪያ ሁለት መስፈሪያ እህል የሚያዝ ጕድጓድ ቈፈረ።
33፤ እንጨቱንም በተርታ አደረገ፥ ወይፈኑንም በብልት በብልቱ ቈረጠ፥ በእንጨቱም ላይ አኖረና።
34፤ አራት ጋን ውኃ ሙሉ በሚቃጠለው መሥዋዕትና በእንጨቱ ላይ አፍስሱ አሉ። ደግሞም። ድገሙ አለ፤ እነርሱም ደገሙ። እርሱም። ሦስተኛ አድርጉ አለ፤ ሦስተኛም አደረጉ።
35፤ ውኃውም በመሠዊያው ዙሪያ ፈሰሰ፤ ደግሞም ጕድጓዱን በውኃ ሞላው።
36፤ መሥዋዕተ ሠርክ በሚቀርብበት ጊዜ ነቢዩ ኤልያስ ቀርቦ። አቤቱ፥ የአብርሃምና የይስሐቅ የእስራኤልም አምላክ ሆይ፥ አንተ በእስራኤል ላይ አምላክ እንደ ሆንህ፥ እኔም ባሪያህ እንደ ሆንሁ፥ ይህንም ሁሉ በቃልህ እንዳደረግሁ ዛሬ ይገለጥ።
37፤ አንተ፥ አቤቱ፥ አምላክ እንደ ሆንህ፥ ልባቸውንም ደግሞ እንደ መለስህ ይህ ሕዝብ ያውቅ ዘንድ ስማኝ፥ አቤቱ፥ ስማኝ አለ።
38፤ የእግዚአብሔርም እሳት ወደቀች፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕቱንም እንጨቱንም ድንጋዮቹንም አፈሩንም በላች፥ በጕድጓዱም ውስጥ ያለውን ውኃ ላሰች።
39፤ ሕዝቡም ሁሉ ያንን ባዩ ጊዜ በግምባራቸው ተደፍተው። እግዚአብሔር እርሱ አምላክ ነው አሉ።
40፤ ኤልያስም። ከበኣል ነቢያት አንድ ሰው እንዳያመልጥ ያዙ አላቸው። ያዙአቸውም፤ ኤልያስም ወደ ቂሶን ወንዝ ወስዶ በዚያ አሳረዳቸው።
41፤ ኤልያስም አክዓብን። የዝናቡ ውሽንፍር እጅግ ነውና ተነሥተህ ውጣ፥ ብላም ጠጣም አለው።
42፤ አክዓብም ሊበላና ሊጠጣ ወጣ፤ ኤልያስም ወደ ቀርሜሎስ አናት ወጣ፤ ፊቱንም በጕልበቱ መካከል አድርጎ በግምባሩ ተደፋ።
43፤ ብላቴናውንም። ወጥተህ ወደ ባሕሩ ተመልከት አለው። ወጥቶም ተመልክቶም። ምንም የለም አለ። እርሱም። ሰባት ጊዜ ተመላለስ አለው። ብላቴናውም ሰባት ጊዜ ተመላለሰ።
44፤ በሰባተኛውም ጊዜ። እነሆ፥ የሰው እጅ የምታህል ታናሽ ደመና ከባሕር ወጥች አለ። እርሱም። ወጥተህ አክዓብን። ዝናብ እንዳይከለክልህ ሰረገላን ጭነህ ውረድ በለው አለ።
45፤ ከጥቂትም ጊዜ በኋላ ሰማዩ ከደመናውና ከነፋሱ የተነሣ ጨለመ፥ ብዙም ዝናብ ሆነ፤ አክዓብም በሰረገላው ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ።
46፤ የእግዚአብሔርም እጅ በኤልያስ ላይ ነበረች፤ ወገቡንም አሸንፍጦ ወደ ኢይዝራኤል እስኪገባ ድረስ በአክዓብ ፊት ይሮጥ ነበር።
ምዕራፍ 19

1፤ አክዓብም ኤልያስ ይህን ሁሉ እንዳደረገ፥ ነቢያትንም ሁሉ በሰይፍ እንደ ገደለ ለኤልዛቤል ነገራት።
2፤ ኤልዛቤልም። ነገ በዚህ ጊዜ ነፍስህን ከእነዚህ እንደ አንዲቱ ነፍስ ባላደርጋት፥ አማልክት ይህን ያድርጉብኝ ይህንም ይጨምሩብኝ ብላ ወደ ኤልያስ መልእክተኛ ላከች።
3፤ ኤልያስም ፈርቶ ተነሣ፥ ነፍሱንም ሊያድን ሄደ፥ በይሁዳም ወዳለው ወደ ቤርሳቤህ መጥቶ ብላቴናውን በዚያ ተወ።
4፤ እርሱም አንድ ቀን የሚያህል መንገድ በምድረ በዳ ሄደ፤ መጥቶም ከክትክታ ዛፍ በታች ተቀመጠና። ይበቃኛል፤ አሁንም፥ አቤቱ፥ እኔ ከአባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ ብሎ እንዲሞት ለመነ።
5፤ በክትክታውም ዛፍ በታች ተጋደመ እንቅልፍም አንቀላፋ፤ እነሆም፥ መልአክ ዳሰሰውና። ተነሥተህ ብላ አለው።
6፤ ሲመለከትም፥ እነሆ፥ በራሱ አጠገብ የተጋገረ እንጎቻና በማሰሮ ውኃ አገኘ። በላም ጠጣም፥ ተመልሶም ተኛ።
7፤ የእግዚአብሔር መልአክ ደግሞ ሁለተኛ ጊዜ መጥቶ ዳሰሰውና። የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ነውና ተነሥተህ ብላ አለው።
8፤ ተነሥቶም በላ ጠጣም፤ በዚያም ምግብ ኃይል እስከ እግዚአብሔር ተራራ እስከ ኮሬብ ድረስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሄደ።
9፤ እዚያም ወዳለ ዋሻ መጣ፥ በዚያም አደረ፤ እነሆም። ኤልያስ ሆይ፥ በዚህ ምን ታደርጋለህ? የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ።
10፤ እርሱም። ለሠራዊት አምላክ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋልና፥ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋልና፥ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ አለ።
11፤ እርሱም። ውጣ፥ በተራራውም ላይ በእግዚአብሔር ፊት ቁም አለ። እነሆም፥ እግዚአብሔር አለፈ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ትልቅና ብርቱ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጠቀ ዓለቶቹንም ሰባበረ፥ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም። ከነፋሱም በኋላ የምድር መናወጥ ሆነ፥ እግዚአብሔር ግን በምድር መናወጥ ውስጥ አልነበረም።
12፤ ከምድር መናወጥ በኋላ እሳት ሆነ፥ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም። ከእሳቱም በኋላ ትንሽ የዝምታ ድምፅ ሆነ።
13፤ ኤልያስም ያን በሰማ ጊዜ ፊቱን በመጐናጸፊያው ሸፈነ፥ ወጥቶም በዋሻው ደጃፍ ቆመ። እነሆ። ኤልያስ ሆይ፥ በዚህ ምን ታደርጋለህ? የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ።
14፤ እርሱም። ለሠራዊት አምላክ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋልና፥ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋልና፥ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ አለ።
15፤ እግዚአብሔርም አለው። ሂድ፥ በመጣህበትም መንገድ በምድረ በዳ ወደ ደማስቆ ተመለስ፤ ከዚያም በደረስህ ጊዜ በሶርያ ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ አዛሄልን ቅባው፤
16፤ በእስራኤልም ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ የናሜሲን ልጅ ኢዩን ቅባው፤ በፋንታህም ነቢይ ይሆን ዘንድ የአቤልምሖላን ሰው የሣፋጥን ልጅ ኤልሳዕን ቅባው ከአዛሄልም ሰይፍ ያመለጠውን ሁሉ።
17፤ ኢዩ ይገድለዋል፤ ከኢዩም ሰይፍ ያመለጠውን ሁሉ ኤልሳዕ ይገድለዋል።
18፤ እኔም ከእስራኤል ጕልበታቸውን ለበኣል ያላንበረከኩትን ሁሉ፥ በአፋቸውም ያልሳሙትን ሁሉ፥ ሰባት ሺህ ሰዎች ለእኔ አስቀራለሁ።
19፤ ከዚያም ሄደ፥ የሣፋጥንም ልጅ ኤልሳዕን በአሥራ ሁለት ጥማድ በሬዎች ሲያርስ፥ እርሱም ከአሥራ ሁለተኛው ጋር ሆኖ አገኘው። ኤልያስም ወደ እርሱ አልፎ መጐናጸፊያውን ጣለበት።
20፤ በሬዎቹንም ተወ፥ ከኤልያስም በኋላ ሮጦ። አባቴንና እናቴን እስማቸው ዘንድ፥ እባክህ፥ ተወኝ፥ ከዚያም በኋላ እከተልሃለሁ አለው። እርሱም። ሂድና ተመለስ፤ ምን አድርጌልሃለሁ? አለው።
21፤ ከእርሱም ዘንድ ተመልሶ ሁለቱን በሬዎች ወስዶ አረዳቸው፥ ሥጋቸውንም በበሬዎቹ ዕቃ ቀቀለው፥ ለሕዝቡም ሰጣቸው፥ በሉም፤ እርሱም ተነሥቶ ኤልያስን ተከትሎ ሄደ፥ ያገለግለውም ነበር።
ምዕራፍ 20

1፤ የሶርያም ንጉሥ ወልደ አዴር ጭፍራውን ሁሉ ሰበሰበ፤ ከእርሱም ጋር ሠላሳ ሁለት ነገሥት ነበሩ፥ ፈረሶችና ሰረገሎችም ነበሩ፤ ወጥቶም ሰማርያን ከበበ፥ ወጋትም።
2፤ ወደ እስራኤልም ንጉሥ ወደ አክዓብ።
3፤ ወልደ አዴር እንዲህ ይላል። ብርህና ወርቅህ ለእኔ ነው፤ ሴቶችህና መልካካሞቹም ልጆችህ ለእኔ ናቸው ብሎ ወደ ከተማይቱ መልእክተኞችን ላከ።
4፤ የእስራኤልም ንጉሥ መልሶ። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ አንተ እንዳልህ ነው፤ እኔ ለእኔም የሆነው ሁሉ የአንተ ነው አለ።
5፤ ደግሞም መልእክተኞች ተመልሰው። ወልደ አዴር እንዲህ ይላል። ቀድሞ ብርህንና ወርቅህን ሴቶችህንና ልጆችህንም ትሰጠኛለህ ብዬ ልኬብህ ነበር፤
6፤ ነገም በዚህ ጊዜ ባሪያዎቼን እልክብሃለሁ፥ ቤትህንም የባሪያዎችህንም ቤቶች ይበረብራሉ፤ ደስ የሚያሰኛቸውንም ሁሉ በእጃቸው አድርገው ይወስዳሉ አሉ።
7፤ የእስራኤልም ንጉሥ የአገሩን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠርቶ። ተመልከቱ፥ ይህም ሰው ክፉ እንዲሻ እዩ፤ ስለ ሴቶቼ ስለ ልጆቼ ስለ ብሬና ወርቄም ላከብኝ፥ እንቢም አላልሁም አለ።
8፤ ሽማግሌዎችም ሁሉ ሕዝቡም ሁሉ። አትስማው፥ እሺም አትበለው አሉት።
9፤ ለወልደ አዴርም መልእክተኞች። ለጌታዬ ለንጉሥ። ለእኔ ለባሪያህ በመጀመሪያ የላክህብኝ ሁሉ አደርጋለሁ፤ ይህን ግን አደርገው ዘንድ አይቻለኝም በሉት አላቸው። መልእክተኞችም ተመልሰው ይህን አወሩለት።
10፤ ወልደ አዴርም። ለሚከተለኝ ሕዝብ የሰማርያ ትቢያ ጭብጥ ጭብጥ ይበቃው እንደ ሆነ፥ አማልክት ይህን ያድርጉብኝ ይህን ይጨምሩብኝ ብሎ ላከበት።
11፤ የእስራኤልም ንጉሥ መልሶ። በቃ፤ ለሰልፍ የሚታጠቅ ጋሻ ጦሩን እንደሚያወልቅ አይመካ አለው።
12፤ ወልደ አዴርም ያን ነገር በሰማ ጊዜ ከነገሥታቱ ጋር በድንኳኑ ውስጥ ይጠጣ ነበር፤ ባሪያዎቹንም። ተሰለፉ አላቸው፤ እነርሱም በከተማይቱ ትይዪ ተሰለፉ።
13፤ እነሆም፥ ነቢይ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ አክዓብ ቀርቦ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህን ብዙ ጭፍራ ሁሉ ታያለህን? እነሆ፥ ዛሬ በእጅህ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃለህ አለ።
14፤ አክዓብም። በማን? አለ፤ እርሱም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በአውራጆቹ አለቆች ጕልማሶች አለ፤ እርሱም። ሰልፉን ማን ይጀምራል? አለ፤ እርሱም። አንተ አለው።
15፤ የአውራጆቹንም አለቆች ጕልማሶች ቈጠረ፥ ሁለት መቶም ሠላሳ ሁለት ነበሩ፤ ከእነርሱም በኋላ ሕዝቡን ሁሉ፥ የእስራኤልን ልጆች ሁሉ፥ ቈጠረ፥ ሰባትም ሺህ ነበሩ።
16፤ ቀትርም በሆነ ጊዜ ወጡ፤ ወልደ አዴር ረዳቶቹም ሠላሳ ሁለቱ ነገሥታት እየጠጡ በድንኳን ውስጥ ይሰክሩ ነበር።
17፤ የአውራጆቹም አለቆች ጕልማሶች አስቀድመው ወጡ፤ ወልደ አዴርም መልእክተኞችን ላከ፥ እነርሱም። ሰዎች ከሰማርያ ወጥተዋል ብለው ነገሩት።
18፤ እርሱም። ለዕርቅ ወይም ለሰልፍ መጥተው እንደ ሆነ በሕይወታቸው ያዙአቸው አለ።
19፤ እነዚህም የአውራጆች አለቆች ጕልማሶች ከከተማይቱ ወጡ፥ ሠራዊትም ተከተላቸው።
20፤ ሁሉም በእያንዳንዱ በፊቱ የነበረውን ሰው ገደለ፥ ሶርያውያንም ሸሹ፤ እስራኤልም አሳደዱአቸው፥ የሶርያም ንጉሥ ወልደ አዴር በፈረሱ አመለጠ።
21፤ የእስራኤል ንጉሥም ወጥቶ ፈረሶቹንና ሰረገሎቹን ያዘ፥ ሶርያውያንንም በታላቅ ውጊት ገደላቸው።
22፤ ነቢዩም ወደ እስራኤል ንጉሥ ቀርቦ። የሶርያ ንጉሥ በሚመጣው ዓመት ይመጣብሃልና ሂድ፥ በርታ፥ የምታደርገውንም ተመልከትና እወቅ አለው።
23፤ የሶርያም ንጉሥ ባሪያዎች እንዲህ አሉት። አምላካቸው የተራሮች አምላክ ነው፤ ስለዚህ በርትተውብን ነበር፤ ነገር ግን በሜዳ ላይ ከእነርሱ ጋር ብንዋጋ በእርግጥ እንበረታባቸዋለን።
24፤ ይህንም አድርግ፤ ከጭፍሮችህ ነገሥታቱን አርቅ፥ በፋንታቸውም አለቆችን ሹም።
25፤ አንተም ቀድሞ እንደ ጠፋብህ ሠራዊት፥ ፈረሱን በፈረስ ፋንታ፥ ሰረገላውንም በሰረገላ ፋንታ፥ ሠራዊትን ቍጠር፤ በሜዳም ላይ ከእነርሱ ጋር እንዋጋለን፥ በእርግጥም እንበረታባቸዋለን። ምክራቸውንም ሰማ፥ እንዲሁም አደረገ። ፕ
26፤ በሚመጣውም ዓመት ወልደ አዴር ሶርያውያንን አሰለፈ፥ ከእስራኤልም ጋር ይዋጋ ዘንድ ወደ አፌቅ ወጣ።
27፤ የእስራኤልም ልጆች ተሰለፉ፥ ሊገጥሙአቸውም ወጡ፤ የእስራኤልም ልጆች እንደ ሁለት ትናንሾች የፍየል መንጋዎች ሆነው በፊታቸው ሰፈሩ፤ ሶርያውያን ግን ምድሩን ሞልተው ነበር።
28፤ የእግዚአብሔርም ሰው ቀርቦ የእስራኤልን ንጉሥ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሶርያውያን። እግዚአብሔር የተራሮች አምላክ ነው እንጂ የሸለቆ አምላክ አይደለም ብለዋልና ይህን ታላቅ ጭፍራ ሁሉ በእጅህ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ አለው።
29፤ እነዚህም በእነዚያ ትይዩ ሰባት ቀን ያህል ሰፈሩ፤ በሰባተኛውም ቀን ተጋጠሙ፥ የእስራኤልም ልጆች ከሶርያውያን በአንድ ቀን መቶ ሺህ እግረኛ ገደሉ።
30፤ የቀሩትም ወደ አፌቅ ወደ ከተማይቱ ውስጥ ሸሹ፤ ቅጥሩም በቀሩት በሀያ ሰባት ሺህ ሰዎች ላይ ወደቀ። ወልደ አዴርም ሸሽቶ ወደ ከተማይቱ ወደ እልፍኙ ውስጥ ገባ።
31፤ ባሪያዎቹም። እነሆ፥ የእስራኤል ቤት ነገሥታት መሐሪዎች እንደ ሆኑ ሰምተናል፤ በወገባችን ማቅ እንታጠቅ፥ በራሳችንም ገመድ እንጠምጥም፥ ወደ እስራኤልም ንጉሥ እንውጣ፤ ምናልባት ነፍስህን ይምራታል አሉት።
32፤ ወገባቸውንም በማቅ ታጠቁ፥ በራሳቸውም ገመድ ጠመጠሙ፥ ወደ እስራኤልም ንጉሥ መጥተው። ባሪያህ ወልደ አዴር። ነፍሴን ትምራት ዘንድ እለምንሃለሁ ብሎአል አሉት። እርሱም። ገና በሕይወቱ አለን? ወንድሜ ነው አለ።
33፤ ሰዎቹም የደግ ምልክት አደረጉትና ቃሉን ከአፉ ተቀብለው። ወንድምህ ወልደ አዴር አለ አሉት። እርሱም። ሂዱ፥ አምጡት አለ። ወልደ አዴርም ወደ እርሱ ወጣ፥ በሰረገላውም ላይ አስቀመጠው።
34፤ ወልደ አዴርም። አባቴ ከአባትህ የወሰዳቸውን ከተሞች እመልስልሃለሁ፤ አባቴ በሰማርያ እንዳደረገ አንተ በደማስቆ ገበያ ታደርጋለህ አለው። አክዓብም። እኔም በዚህ ቃል ኪዳን እሰድድሃለሁ አለ። ከእርሱም ጋር ቃል ኪዳን አድርጎ ሰደደው።
35፤ ከነቢያትም ወገን አንድ ሰው በእግዚአብሔር ቃል ባልንጀራውን። ምታኝ አለው። ሰውዮውም ይመታው ዘንድ እንቢ አለ።
36፤ እርሱም። የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማህምና እነሆ፥ ከእኔ በራቅህ ጊዜ አንበሳ ይገድልሃል አለው። ከእርሱም በራቀ ጊዜ አንበሳ አግኝቶ ገደለው።
37፤ ደግሞም ሌላ ሰው አግኝቶ። ምታኝ አለው። ሰውዮውም መታው፥ በመምታቱም አቈሰለው።
38፤ ነቢዩም ሄዶ በመንገድ አጠገብ ንጉሡን ቆየው፤ ዓይኖቹንም በቀጸላው ሸፍኖ ተሸሸገ።
39፤ ንጉሡም ባለፈ ጊዜ ወደ እርሱ ጮኸ። ባሪያህ ወደ ሰልፍ መካከል ወጣ፤ እነሆም፥ አንድ ሰው ፈቀቅ ብሎ ወደ እኔ አንድ ሰው አመጣና። ይህን ሰው ጠብቅ፥ ቢኰበልልም ነፍስህ በነፍሱ ፋንታ ትሆናለች፥ ወይም አንድ መክሊት ብር ትከፍላለህ አለኝ።
40፤ ባሪያህም ወዲህና ወዲያ ሲመለከት ጠፋ አለው። የእስራኤልም ንጉሥ። ፍርድህ እንዲሁ ይሆናል፤ አንተ ፈርድኸዋል አለው።
41፤ ፈጥኖም ቀጸላውን ከዓይኑ አነሣ የእስራኤልም ንጉሥ ከነቢያት ወገን እንደ ሆነ አወቀው።
42፤ እርሱም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ እርም ያልሁትን ሰው ከእጅህ አውጥተሃልና ነፍስህ በነፍሱ ፋንታ ሕዝብህም በሕዝቡ ፋንታ ይሆናሉ አለው።
43፤ የእስራኤልም ንጉሥ እየተቈጣና እየተናደደ ወደ ቤቱ ተመለሰ፥ ወደ ሰማርያም መጣ።
ምዕራፍ 21

1፤ ለኢይዝራኤላዊውም ለናቡቴ በሰማርያ ንጉሥ በአክዓብ ቤት አጠገብ የወይን ቦታ ነበረው።
2፤ አክዓብም ናቡቴን። በቤቴ አቅራቢያ ነውና የአትክልት ቦታ አደርገው ዘንድ የወይን ቦታህን ስጠኝ፤ ስለ እርሱም ከእርሱ የተሻለ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ፤ ወይም ብትወድድ ግምቱን ገንዘብ እሰጥሃለሁ ብሎ ተናገረው።
3፤ ናቡቴም አክዓብን። የአባቶቼን ርስት እሰጥህ ዘንድ እግዚአብሔር ያርቅልኝ አለው።
4፤ ኢይዝራኤላዊውም ናቡቴ። የአባቶቼን ርስት አልሰጥህም ብሎ ስለ ተናገረው አክዓብ ተቈጥቶና ተናድዶ ወደ ቤቱ ገባ። በአልጋውም ላይ ተጋድሞ ፊቱን ተሸፋፈነ፥ እንጀራም አልበላም።
5፤ ሚስቱም ኤልዛቤል ወደ እርሱ መጥታ። ልብህ የሚያዝን እንጀራስ የማትበላ ስለምንድር ነው? አለችው።
6፤ እርሱም። ኢይዝራኤላዊውን ናቡቴን። የወይንህን ቦታ በገንዘብ ስጠኝ፤ ወይም ብትወድድ በፋንታው ሌላ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ ብዬ ተናገርሁት፤ እርሱ ግን። የወይን ቦታዬን አልሰጥህም ብሎ ስለ መለሰልኝ ነው አላት።
7፤ ሚስቱም ኤልዛቤል። አንተ አሁን የእስራኤልን መንግሥት ትገዛለህን? ተነሣ እንጀራም ብላ፥ ልብህም ደስ ይበላት፤ የኢይዝራኤላዊውን የናቡቴን የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ አለችው።
8፤ በአክዓብም ስም ደብዳቤ ጻፈች፥ በማኅተሙም አተመችው፤ በከተማው ወደ ነበሩትና ከናቡቴም ጋር ወደ ተቀመጡት ሽማግሌዎችና ከበርቴዎች ደብዳቤውን ላከች።
9፤ በደብዳቤውም። ስለ ጾም አዋጅ ንገሩ፥ ናቡቴንም በሕዝቡ ፊት አስቀምጡት፤
10፤ ሁለትም ምናምንቴ ሰዎች በፊቱ አስቀምጡና። እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል ብለው ይመስክሩበት፤ አውጥታችሁም እስኪሞት ድረስ ውገሩት ብላ ጻፈች።
11፤ በከተማውም የተቀመጡት የከተማው ሰዎችና ሽማግሌዎች ከበርቴዎችም ኤልዛቤል እንዳዘዘቻቸውና ወደ እነርሱ በተላከው ደብዳቤ እንደ ተጻፈ እንዲሁ አደረጉ።
12፤ የጾም አዋጅ ነገሩ፥ ናቡቴንም በሕዝቡ ፊት አስቀመጡት።
13፤ ሁለቱም ምናምንቴ ሰዎች ገብተው በፊቱ ተቀመጡ፤ ምናምንቴዎቹ ሰዎችም በሕዝቡ ፊት። ናቡቴ እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል ብለው በናቡቴ ላይ መሰከሩ። የዚያን ጊዜም ከከተማ አውጥተው እስኪሞት ድረስ ወገሩት።
14፤ ወደ ኤልዛቤልም። ናቡቴ ተወግሮ ሞተ ብለው ላኩ።
15፤ ኤልዛቤልም ናቡቴ ተወግሮ እንደ ሞተ በሰማች ጊዜ ኤልዛቤል አክዓብን። ናቡቴ ሞቶአል እንጂ በሕይወት አይደለምና በገንዘብ ይሰጥህ ዘንድ እንቢ ያለውን የኢይዝራኤላዊውን የናቡቴን የወይን ቦታ ተነሥተህ ውረስ አለችው።
16፤ አክዓብም ናቡቴ እንደ ሞተ በሰማ ጊዜ ይወርሰው ዘንድ ወደ ኢይዝራኤላዊው ወደ ናቡቴ ወይን ቦታ ሊወርድ ተነሣ።
17፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ቴስብያዊው ወደ ኤልያስ እንዲህ ሲል መጣ።
18፤ ተነሥተህ በሰማርያ የሚኖረውን የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ትገናኝ ዘንድ ውረድ፤ እነሆ፥ ይወርሰው ዘንድ በወረደበት በናቡቴ የወይን ቦታ ውስጥ አለ።
19፤ አንተም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ገድለህ ወረስኸውን? ብለህ ንገረው። ደግሞም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ውሾች የናቡቴን ደም በላሱበት ስፍራ የአንተን ደም ደግሞ ውሾች ይልሱታል ብለህ ንገረው።
20፤ አክዓብም ኤልያስን። ጠላቴ ሆይ፥ አገኘኸኝን? አለው። እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት። አግኝቼሃለሁ፤ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ለማድረግ ራስህን ሽጠሃልና።
21፤ እነሆ፥ ክፉ ነገር አመጣብሃለሁ፥ ፈጽሞም እጠርግሃለሁ፥ ከአክዓብም በእስራኤል ዘንድ የታሰረውንና የተለቀቀውን ወንድ ሁሉ አጠፋለሁ፤
22፤ በሥራህም አስቈጥተኸኛልና፥ እስራኤልንም አስተሃልና ቤትህን እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት እንደ አኪያም ልጅ እንደ ባኦስ ቤት አደርገዋለሁ።
23፤ ደግሞ እግዚአብሔር ስለ ኤልዛቤል። በኢይዝራኤል ቅጥር አጠገብ ኤልዛቤልን ውሾች ይበሉአታል ብሎ ተናገረ።
24፤ ከአክዓብም ወገን በከተማይቱ ውስጥ የሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳውም የሞተውን የሰማይ ወፎች ይበሉታል።
25፤ በእግዚአብሔር ፊት ክፋት ለመሥራት ራሱን እንደ ሸጠ፥ ሚስቱም ኤልዛቤል እንደ ነዳችው፥ እንደ አክዓብ ያለ ሰው አልነበረም።
26፤ እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት ያጠፋቸው አሞራውያን እንደ ሠሩት ሁሉ፥ ጣዖታትን በመከተል እጅግ ርኩስ ነገር ሠራ።
27፤ አክዓብም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀድዶ ገላውን ማቅ አለበሰ፥ ጾመም፥ በማቅ ላይም ተኛ፥ ቅስስ ብሎም ሄደ።
28
29፤ ደግሞም። አክዓብ በፊቴ እንደ ተዋረደ አየህን? በፊቴ የተዋረደ ስለ ሆነ በልጁ ዘመን በቤቱ ላይ ክፉ ነገር አመጣለሁ እንጂ በእርሱ ዘመን ክፉ ነገር አላመጣም የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ ቴስብያዊው ወደ ኤልያስ መጣ።
ምዕራፍ 22

1፤ ሶርያና እስራኤልም ሳይዋጉ ሦስት ዓመት ተቀመጡ።
2፤ በሦስተኛውም ዓመት የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወረደ።
3፤ የእስራኤልም ንጉሥ ባሪያዎቹን። ሬማት ዘገለዓድ የእኛ እንደ ሆነች፥ እኛም ከሶርያ ንጉሥ እጅ ሳንወስዳት ዝም እንዳልን ታውቃላችሁን? አላቸው።
4፤ ኢዮሣፍጥንም። በሬማት ዘገለዓድ እንዋጋ ዘንድ ከእኔ ጋር ትመጣለህን? አለው። ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ። እኔ እንደ አንተ፥ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ፥ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው አለው።
5፤ ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ። የእግዚአብሔርን ቃል አስቀድመህ ትጠይቅ ዘንድ እለምንሃለሁ አለው።
6፤ የእስራኤልም ንጉሥ ነቢያቶቹን አራት መቶ የሚያህሉትን ሰዎች ሰብስቦ። ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ ልሂድን? ወይስ ልቅር? አላቸው። እነርሱም። እግዚአብሔር በንጉሥ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ውጣ አሉት።
7፤ ኢዮሣፍጥ ግን። እንጠይቀው ዘንድ ሌላ የእግዚአብሔር ነቢይ በዚህ አይገኝምን? አለ።
8፤ የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን። እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት የይምላ ልጅ ሚክያስ የሚባል አንድ ሰው አለ፤ ነገር ግን ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት አይናገርልኝምና እጠላዋለሁ አለው። ኢዮሣፍጥም። ንጉሥ እንዲህ አይበል አለ።
9፤ የእስራኤልም ንጉሥ አንዱን ጃንደረባ ጠርቶ። የይምላን ልጅ ሚክያስን ፈጥነህ አምጣ አለው።
10፤ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ልብሰ መንግሥት ለብሰው በሰማርያ በር መግቢያ አጠገብ በአደባባይ በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያቶቹም ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር።
11፤ የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ሶርያውያንን ትወጋለህ አለ።
12፤ ነቢያትም ሁሉ። እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሂድና ተከናወን እያሉ እንዲህ ትንቢት ይናገሩ ነበር።
13፤ ሚክያስንም ሊጠራ የሄደ መልእክተኛ። እነሆ፥ ነቢያት ሁሉ በአንድ አፍ ሆነው ለንጉሡ መልካምን ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ አለው።
14፤ ሚክያስም። ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር የሚነግረኝን እርሱን እናገራለሁ አለ።
15፤ ወደ ንጉሡም በመጣ ጊዜ ንጉሡ። ሚክያስ ሆይ፥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ እንሂድን? ወይስ እንቅር? አለው፤ እርሱም። ውጣና ተከናወን፤ እግዚአብሔርም በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታል ብሎ መለሰለት።
16፤ ንጉሡም። ከእውነት በቀር በእግዚአብሔር ስም እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ? አለው።
17፤ እርሱም። እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም። ለእነዚህ ጌታ የላቸውም እያንዳንዱም በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ አለ ብሎ ተናገረ።
18፤ የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን። ክፉ እንጂ መልካም እንደማይናገርልኝ አላልሁህምን? አለው።
19፤ ሚክያስም አለ። እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ።
20፤ እግዚአብሔርም። ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ ይወድቅ ዘንድ አክዓብን የሚያሳስት ማን ነው? አለ። አንዱም እንዲህ ያለ ነገር፥ ሌላውም እንዲያ የለ ነገር ተናገረ።
21፤ መንፈስም ወጣ በእግዚአብሔርም ፊት ቆሞ። እኔ አሳስተዋለሁ አለ።
22፤ እግዚአብሔርም። በምን? አለው፤ እርሱም። ወጥቼ በነቢያቶቹ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ አለ። እግዚአብሔርም። ማሳሳትስ ታሳስተዋለህ፥ ይሆንልሃልም፤ ውጣ፥ እንዲሁም አድርግ አለ።
23፤ አሁንም። እነሆ፥ እግዚአብሔር በእነዚህ በነቢያትህ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም በላይህ ክፉ ተናግሮብሃል።
24፤ የክንዓናም ልጅ ሴዴቅያስ ቀረበ፥ ሚክያስንም ጕንጩን በጥፊ መታውና። አንተን ሊናገር የእግዚአብሔር መንፈስ በምን መንገድ ከእኔ አለፈ? አለ።
25፤ ሚክያስም። እነሆ፥ በዚያ ቀን ልትሸሸግ ወደ እልፍኝህ በሄድህ ጊዜ ታያለህ አለ።
26፤ የእስራኤልም ንጉሥ። ሚክያስን ውሰዱ፥ ወደ ከተማይቱም ሹም ወደ አሞን ወደ ንጉሡም ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሳችሁ። ንጉሡ እንዲህ ይላል።
27፤ በደኅና እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው በግዞት አኑሩት፥ የመከራም እንጀራ መግቡት፥ የመከራም ውኃ አጠጡት በሉ አለ።
28፤ ሚክያስም። በደኅና ብትመለስ እግዚአብሔር በእኔ የተናገረ አይደለም አለ። ደግሞም። አሕዛብ ሁሉ ሆይ፥ ስሙኝ አለ።
29፤ የእስራኤልም ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ወጡ።
30፤ የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን። ልብሴን ለውጬ ወደ ሰልፍ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብስህን ልበስ አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ልብሱን ለውጦ ወደ ሰልፍ ገባ።
31፤ የሶርያም ንጉሥ ሠላሳ ሁለቱን የሰረገሎች አለቆች። ከእስራኤል ንጉሥ በቀር፥ ታናሽ ቢሆን ወይም ታላቅ ከማናቸውም ጋር አትግጠሙ ብሎ አዝዞ ነበር።
32፤ የሰረገሎች አለቆችም ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ። በእውነት የእስራኤል ንጉሥ ነው አሉ፤ ይገጥሙትም ዘንድ ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥም ጮኸ።
33፤ የሰረገሎች አለቆችም የእስራኤል ንጉሥ እንዳልሆነ ባዩ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ።
34፤ አንድ ሰውም ቀስቱን ድንገት ገትሮ የእስራኤልን ንጉሥ በጥሩሩ ልብስ መጋጠሚያ በኩል ወጋው፤ ሰረገለኛውንም። መልሰህ ንዳ፥ ተወግቻለሁና ከሰልፍ ውስጥ አውጣኝ አለው።
35፤ በዚያም ቀን ሰልፍ በረታ፤ ንጉሡም በሶርያውያን ፊት በሰረገላው ላይ ተደግፎ ነበር፥ ማታም ሞተ፤ የቍስሉም ደም በሰረገላው ውስጥ ፈሰሰ።
36፤ በሠራዊቱም መካከል ፀሐይ ስትገባ። ንጉሡ ሞቶአልና እያንዳንዱ ወደ ከተማው፥ እያንዳንዱም ወደ አገሩ ይሂድ የሚል ጩኸት ሆነ።
37፤ ወደ ሰማርያም መጡ፥ ንጉሡንም በሰማርያ ቀበሩት።
38፤ አመንዝሮች በታጠቡባት በሰማርያ ኵሬ ሰረገላውን አጠቡት፥ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ቃል ውሾች ደሙን ላሱት።
39፤ የቀረውም የአክዓብ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ከዝሆን ጥርስም የሠራው ቤት፥ የሠራቸውም ከተሞች ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
40፤ አክዓብም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በእርሱም ፋንታ ልጁ አካዝያስ ነገሠ።
41፤ አክዓብም በነገሠ በአራተኛው ዓመት የአሳ ልጅ ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ላይ ነገሠ።
42፤ ኢዮሣፍጥ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ አምስት ዓመት ጎበዝ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሀያ አምስት ዓመት ነገሠ። እናቱም ዓዙባ የተባለች የሺልሒ ልጅ ነበረች።
43፤ በአባቱም በአሳ መንገድ ሁሉ ሄደ፥ ከእርሱም ፈቀቅ አላለም፥ በእግዚአብሔርም ፊት ቅን አደረገ፤ ነገር ግን በኮረብቶች ላይ ያሉትን መስገጃዎች አላራቀም፤ ሕዝቡ ገና በኮረብቶቹ ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር።
44፤ ኢዮሣፍጥም ከእስራኤል ንጉሥ ጋር ታረቀ። vፕ
45፤ የቀረውም የኢዮሣፍጥ ነገር፥ የሠራውም ጭከና፥ እንዴትም እንደ ተወጋ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
46፤ ከአባቱ ከአሳ ዘመን የተረፉትን ሰዶማውያን ከምድር አጠፋ።
47፤ በኤዶምያስም ንጉሥ አልነበረም፤ ሹሙም እንደ ንጉሥ ነበረ።
48፤ ኢዮሣፍጥም ወደ ኦፊር ሄደው ወርቅ ያመጡ ዘንድ የተርሴስን መርከቦች ሠራ፤ ነገር ግን መርከቦቹ በዔጽዮንጋብር ተሰበሩ እንጂ አልሄዱም።
49፤ የአክዓብም ልጅ አካዝያስ ኢዮሣፍጥን። ባሪያዎቼ ከባሪያዎችህ ጋር በመርከብ ይሂዱ አለው፤ ኢዮሣፍጥ ግን አልወደደም።
50፤ ኢዮሣፍጥም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በአባቱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ በእርሱም ፋንታ ልጁ ኢዮራም ነገሠ።
51፤ በይሁዳም ንጉሥ በኢዮሣፍጥ በአሥራ ሰባተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ አካዝያስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ በእስራኤልም ላይ ሁለት ዓመት ነገሠ።
52፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፥ በአባቱና በእናቱም መንገድ፥ እስራኤልንም ባሳተው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም መንገድ ሄደ።
53፤ በኣልንም አመለከ ሰገደለትም፤ አባቱም እንዳደረገ ሁሉ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን አስቈጣ።